የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት መስማት የተሳናቸውን ለማስተናገድ እንዲቻል ለፋሲሊቴሽን ሠራተኞች የምልክት ቋንቋ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረጉን አስታወቀ፡፡ ከዚህ ቀደም መስማት የተሳናቸውን ለማስተናገድ የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ ለመግባባት ችግር እንደነበር፣ ችግሩንም ለማቃለል ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለ11 የዓለም አቀፍ ኤርፖርቶች የፋሲሊቴሽን ሠራተኞች፣ ለአንድ ወር የቆየ የምልክት ቋንቋ ሥልጠና እንዲወስዱ ማድረጉን ለሪፖርተር ጋዜጣ በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡
በአገሪቱ የምልክት ቋንቋ ትምህርት ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና በቋንቋው የሚግባቡበት መስማት ከተሳናቸው፣ ከመምህራን ወይም ከአስተርጓሚዎች በስተቀር በሌላው የኅብረተሰብ ክፍል አልተለመደም፡፡ በሚኒስቴሩ የምልክት ቋንቋ ባለሙያዋ ወይዘሪት ፅጌረዳ ጌታቸው፣ መሥሪያ ቤቱ ባለው የማስተባበር ሥልጣን መሠረት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ በዚህ መሠረትም ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ ለመረጃ ዴስክ ባለሙያዎች፣ ለዓቃቢያን ሕጎች እንዲሁም ለነርሶች ሥልጠናዎችን ያዘጋጃል፡፡
ኤርፖርቶች ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መስማት ከተሳናቸው ደንበኞቻቸው ጋር ጨርሶ ያለመግባባት በየጊዜው የሚያጋጥማቸው በመሆኑ በእነዚህ ተቋማት ላይ የምልክት ቋንቋ እንዲለመድ ትኩረት እየተሰጠ ይገኛል። ግንዛቤ መፍጠርና በተወሰነ መልኩ መግባቢያ የሚሆኑ ምልክቶችን ማሳወቅ መቻሉ፣ በተወሰነ ደረጃ ችግሩን ለመቀነስ እንደሚያስችል ወይዘሪት ጽጌረዳ አስረድተዋል።
ቋንቋውን በመማር ላይ የሚገኙ የፋሲሊቴሽን ሠራተኞች በበኩላቸው፣ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ መስማት የተሳናቸው ደንበኞች የሚገጥማቸውን የመግባባት ችግር ሊፈታ እንደሚችል ገልጸዋል። በተወሰነ መልኩ ቋንቋውን ተጠቅሞ ደንበኞችን ለመርዳት ዝግጁ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።
ሥልጠናው ላይ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የፋሲሊቴሽን ሠራተኞች ከሌሎች ተቋማት ሠራተኞች ጋር የተካፈሉ ሲሆን፣ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ተሸላሚ ሆነዋል።