በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን መራነን ቤኛቆ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ኅዳር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ በተነሳ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ፣ የ59 አባወራዎች መኖሪያ የሆኑ 73 ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ተገለጸ፡፡
የ59 አባወራዎች ወይም የ326 ቤተሰቦች መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውንና ነዋሪዎቹ በድንኳን ውስጥ እንደሚገኙ፣ የቀበሌ ሊቀመንበሩ አቶ ኢማሙ ተረፈ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ምክንያቱ ሳይታወቅ በተነሳው የእሳት አደጋ የነዋሪዎቹ ቤቶችና ቁሳቁሶቻቸው መቃጠላቸውን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ እስካሁን ቀይ መስቀል ብቻ ድንኳንና ብርድ ልብስ ከመስጠቱ በስተቀር ያገኙት ዕርዳታ እንደሌለ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ኢማም 64 የሳር ቤቶችና 11 ቆርቆሮ ቤቶች ሲቃጠሉ፣ የአካባቢው አርሶ አደሮች ዋና መተዳደሪያ የሆነው የእንሰት (ቆጮ) ተክልም በእሳት መውደሙን አስረድተዋል፡፡
አንዱ ሌላውን እንዳይረዳ የሁሉም ነዋሪዎች ንብረት መውደሙ ከፍተኛ ጉዳት ላይ እንደጣላቸው የሚናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ለወሊሶ ወረዳ አስተዳዳሪና ለወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሪፖርት ያደረጉ ቢሆንም፣ እስከ ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ምላሽ አለማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡
የተቃጠሉት ቤቶች ከፍተኛው 98,000 ብር፣ ዝቅተኛው 48,000 ብር እንደሚገመት የተናገሩት ሊቀመንበሩ አጠቃላይ ግምቱ በባለሙያ ስላልተገመተ ማወቅ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡
የእሳት አደጋው እጅግ ከፍተኛ እንደነበርና በአካባቢው የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደርሶ ባደረገላቸው ዕርዳታ ሊጠፋ እንደቻለ የተናገሩት አቶ ኢማም፣ ያ ባይሆን ኖሮ ወደ ሌላ አካባቢም ሊዛመት ይችል እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ፖሊስ በአካባቢው ደርሶ ሰፊ ምርመራ ያደረገ ቢሆንም እስካሁን የቃጠሎው ምክንያት አለመታወቁን አክለዋል፡፡
የቃጠሎው ተጎጂዎች በብዙ ነገር እየተጎዱ በመሆናቸው፣ የክልሉ መንግሥትና የፌዴራል መንግሥት እንዲደርሱላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል፣ ከወሊሶ ወረዳ አስተዳደርና ከወረዳው የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት አስተያየት ለማግኘት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡