Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበኢትዮጵያ የተፈናቃዮች ቁጥር እያሻቀበ መምጣት ከፍተኛ ሥጋት መሆኑ ሪፖርት ቀረበ

  በኢትዮጵያ የተፈናቃዮች ቁጥር እያሻቀበ መምጣት ከፍተኛ ሥጋት መሆኑ ሪፖርት ቀረበ

  ቀን:

  – መንግሥት ሥጋት የፈጠረ መፈናቀል የለም በማለት ሪፖርቱን አጣጣለ

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአገሪቱ ተከስተው በነበሩ የእርስ በርስ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች 390,000 ሰዎች ከሚኖሩባቸው ቀዬዎች መፈናቀላቸው ተጠቆመ፡፡ ድርቅ፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጠረ ውጥረት፣ የውኃ እጥረትና የግጦሽ መሬት ችግሮች ለተመዘገበው የተፈናቃዮች ቁጥር መንስዔ መሆናቸውን ኢንተርናሽናል ዲስፕሌስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር የተባለው ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ተመልክቷል፡፡

  ‹‹በአገሪቱ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሰዎች ከቀያቸው ይፈናቀላሉ፡፡ ነገር ግን የዚህን ያህል አይደለም፡፡ ይኼ የተጋነነ ቁጥር ነው፤›› ሲሉ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ሪፖርቱን አጣጥለዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ እንደ ድርቅና ጎርፍ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ቦታው ድረስ ተሂዶ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር አለ፡፡ አደጋው በተከሰተበት አካባቢ በመድረስ ለተጎጂዎች ምግብ የማቅረብ ሥራ እንደሚሠራ፣ የጎርፍ አደጋን በተመለከተም አደጋው በተከሰተበት አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች አስፈላጊው ነገር ተሟልቶላቸው ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ እንደሚደረግ፣ ጎርፉ በሚረጋጋበት ወቅትም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱና መልሶ የማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚደረግበት አሠራር አለ ብለዋል፡፡

  ‹‹በአገሪቱ በብዛት ሰዎች የሚፈናቀሉት በጎሳዎች መካከል በሚፈጠር ግጭት ነው፡፡ ሰዎች እርስ በርስ ተቻችለው እንዲኖሩ ለማኅበረሰቡ ስለሰላም ትምህርት ይሰጣል፡፡ ከዚህ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች ሲኖሩም ተፈናቃዮች ዕርዳታ እንዲያገኙ የሚደረግበት አሠራር አለ፤›› ሲሉ በአገሪቱ ሰዎች ከቀያቸው የሚፈናቀሉባቸው አጋጣሚዎች ጠባብ መሆናቸውን በመግለጽ ሪፖርቱን አጣጥለዋል፡፡

  ምናልባት በስህተት በተደጋጋሚ ጊዜ የተቆጠሩ ተፈናቃዮች ሊኖሩ እንደሚችሉና የመረጃውን ትክክለኛነት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሆኖ ማጣራት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ይፋ የተደረገው ሪፖርቱ፣ በአፍሪካ ያለውን አጠቃላይ የተፈናቃዮች ቁጥር ከነምክንያቱ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 በእርስ በርስ ግጭቶችና በተፈጥሮ አደጋዎች ከሚኖርበት ቀዬ የተፈናቀሉ አፍሪካውያን ቁጥር 3.5 ሚሊዮን ነው፡፡ ይህም በቀን ሲሰላ 9,500 መሆኑን በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

  ከዚህ መካከል ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ነዋሪዎች መሆናቸውን፣ 30 በመቶ የሚሆነው በናይጄሪያ የተከሰተ መሆኑንና 25 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመዘገበ እንደሆነ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡

  2.4 ሚሊዮን የሚሆኑት በእርስ በርስ ግጭት የተፈናቀሉ ሲሆኑ 1.1 ሚሊዮኑ ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ በተለይም በጎርፍ የተከሰቱ መሆናቸው ተመዝግቧል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ለተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥርም በሶማሊያ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ለዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት መንስዔ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 12.4 ሚሊዮን አፍሪካዊያን በእርስ በርስ ግጭት ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በሌሎች አካባቢዎች በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡

  የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሚፈጠር ድርቅና ጎርፍ የተፈናቃዮች ቁጥር ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም ሪፖርቱ ያትታል፡፡ የኢንተርናሽናል ዲስፕሌስመንት ሞኒተሪንግ ሴንተር ዳይሬክተር አሌክሳንድራ ቢላክ፣ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱንና የመከላከል ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በእርስ በርስ ግጭቶች የሚፈናቀሉ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ የሰላም ግንባታ ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስና ሰዎች እርስ በርስ ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

  በተለያዩ አጋጣሚዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች ድንበር አቋርጠው ከአገራቸው ስለሚወጡ የስደተኞችን ያህል የሕግ ከለላ አያገኙም ብለዋል፡፡ ነዋሪውንና እነሱን ለመለየትም አስቸጋሪ በመሆኑ ተገቢውን ዕርዳታ ለመስጠት እንደማያመች ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም እንደ ምግብና መጠለያ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎታቸው ላይሟላላቸው ይችላል፡፡ የተፈናቃዮችን መብት ለማስጠበቅ በአፍሪካ ኅብረት የወጣ ካምፓላ ኮንቬንሽን የተባለ ስምምነት ነበር፡፡ ስምምነቱ ከወጣ አራት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ፀድቆ በሥራ ላይ ሊውል አልቻለም፡፡      

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img