Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊሃያ ሥራ ተቋራጮች በመንገድ ግንባታ ጨረታዎች እንዳይሳተፉ ማዕቀብ ተጣለባቸው

  ሃያ ሥራ ተቋራጮች በመንገድ ግንባታ ጨረታዎች እንዳይሳተፉ ማዕቀብ ተጣለባቸው

  ቀን:

  በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ተሳታፊ ከሆኑ 45 የአገር ውስጥና የውጭ ሥራ ተቋራጮች ውስጥ ሃያዎቹ በቀጣይ የግንባታ ጨረታዎች እንዳይሳተፉ ማዕቀብ ተጣለባቸው፡፡

  የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በተወሰኑ ወራት ልዩነቶች በሚያካሂደው የሥራ ተቅራጮች አፈጻጸም ግምገማ መሠረት እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ በተደረገ ምዘና፣ በቀጣይ ጨረታዎች መሳተፍ አይችሉም ከተባሉት ሃያዎቹ ውስጥ 12 ያህሉ የውጭ ሥራ ተቋራጮች ናቸው፡፡

  ባለሥልጣኑ ሥራ ተቋራጮች በእጃቸው ያሉትን ፕሮጀክት አፈጻጸሞች በመገምገም በሚሰጠው ውጤት ቀጣይ ግምገማ እስኪካሄድ በሚወጡ ጨረታዎች ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑ ክልከላ ካደረገባቸው ከ12ቱ የውጭ ኮንትራክተሮች ውስጥ፣ ሰባቱ የቻይና ሥራ ተቋራጮች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  እነሱም ሲኖ ኃይድሮ፣ ቻይና ኢንተርናሽናል ወተር ኤንድ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን፣ ቻይና ቁጥር 17፣ ሁናን ሁንዳ አርቢሲ፣ ቻይና ሬል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ፣ ቻይና ሃይዌ ግሩፕ፣ ቻይና ፈርስት ሃይዌ የተባሉት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሰባት የቻይና ሥራ ተቋራጮች እጅ 12 ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡

  ከአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች አፈጻጸማቸው ታይቶ በቀጣይ ጨረታ እንዳይሳተፉ ክልከላ የተጣለባቸው ናቸው ከተባሉት ስምንቱ ውስጥ፣ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንዱ ነው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ አኪር፣ መከላከያ፣ ገነት፣ ዲኖ፣ ፍሊንስቶን፣ ክፍሎምና አሰር የተባሉት ናቸው፡፡

  የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አምስት፣ አኪር ደግሞ አራት ፕሮጀክቶች በእጃቸው አሉ፡፡ እንደ ሳትኮን ያሉ ኮንትራክተሮች ደግሞ ቀደም ባሉት ጊዜያት በጨረታ ሳይሳተፉ ቆይተው አሁን ያለው አፈጻጸማቸው በመሻሻሉ፣ በአዳዲስ ጨረታዎች የመሳተፍ ዕድል እንደተሰጣቸው መረጃው ያመለክታል፡፡ ሳትኮን በአሁኑ ወቅት አምስት ፕሮጀክቶችን ይዞ እየሠራ ይገኛል፡፡

  በአንፃሩ 45 ፕሮጀክቶች ከያዙት የውጭ ሥራ ተቋራጮች ውስጥ ሲጂሲኦሲ የተባለው የቻይናው ኩባንያ ያላጠናቀቃቸው ስድስት ፕሮጀክቶች በእጁ ይገኛሉ፡፡ በባለሥልጣኑ ግምገማ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም መልካም በመሆኑ በቀጣይ ጨረታዎች እንዲሳተፍ ዕድል ተሰጥቶታል፡፡

  ሲጂሲኦሲ በእጁ የሚገኙት ስድስት ፕሮጀክቶች ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን አራት ፕሮጀክቶች በቻይና ሬልዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ እጅ ይገኛሉ፡፡

  ከቻይና ሥራ ተቋራጮች በተጨማሪ በቀጣይ ጨረታዎች ተሳታፊ መሆን አይችሉም የተባሉት አምስቱ የውጭ ኩባንያዎች ዓረብ ኮንትራክተር የተባለው የግብፅ፣ ሃዋክ ኢንተርናሽናል የተባለው የየመን፣ ሳው ኢንፍርስትራክቸር የተባለው የህንድ፣ አያቶል አስፋልት የተባለው የስፔን፣ ኤልሳሜክስ የተባለው የስፔን ሥራ ተቋራጮች ናቸው፡፡

  ከአምስቱ ሥራ ተቋራጮች ውስጥ ሦስቱ ይዘዋቸው የነበሩ ሦስት ፕሮጀክቶችን በኮንትራት ውላቸው መሠረት አላከናወኑም ተብለው ውላቸው ሙሉ በሙሉ የተሰረዘባቸው ጭምር በመሆናቸው፣ ከዚህ በኋላ አዲስ ሥራ የማግኘታቸው ዕድል የጠበበ ነው ተብሏል፡፡

  የኮንትራት ውላቸው ከፈረሰባቸው ሦስቱ ሥራ ተቋራጮች ውስጥ ሃዋክ ኢንተርናሽናል የተባለው የየመን ኮንትራክተር ተረክቦት የነበረው የሐዋሳ አገረ ማርያም (2) እና ጭኮ ይርጋ ጨፌ መንገድ ፕሮጀክት ተነጥቋል፡፡ የዚሁ መንገድ አካል የሆነውን የሐዋሳ አገረ ማርያም (1) ሐዋሳ ጨኮ መንገድ ሥራን ተረክቦ የነበረው ሳው ኢንፍራቸከርም የኮንትራት ውሉ ተቋርጧል፡፡ አያቶል አስፋልት የተባለውም የስፔን ኩባንያ ይዞት የነበረው የዱለቻ አዋሽ አርባ የመንገድ ፕሮጀክት ውል እንዲቋረጥበት በመደረጉ፣ የሦስቱ ፕሮጀክቶች ግንባታ ለሌላ ኩባንያ እንዲሰጥ ውሳኔ ተነግሯል፡፡ 

  በጥቅምት መጀመሪያ ላይ የሥራ አፈጻጸማቸው የተፈተሹት 21 የውጭና 24 የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች እጅ በጠቅላላው 85 ያህል የመንገድ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ መረጃው ያመለክታል፡፡

  እነዚህ ፕሮጀክቶች ከ85 ቢሊዮን ብር በላይ የኮንትራት ስምምነት የተፈረመባቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ከስድስት ዓመታት በላይ የዘገዩና ይጠናቀቃሉ ተብለው ከተያዘላቸው ጊዜ በላይ የቆዩ ናቸው፡፡

  ከዚህ ውስጥ 40 ፕሮጀክቶች በእጃቸው የሚገኙት 24 የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች የያዙዋቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ቁጥር የውጭ ኩባንያዎች ከያዙት በሦስት የሚበልጥ ቢሆንም፣ በ24 የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች የተያዙት ፕሮጀክቶች ጠቅላላ ዋጋ 31 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ በሃያ አንድ የውጭ ሥራ ተቋራጮች የተያዙት 45 ፕሮጀክቶች ጠቅላላ ዋጋ ግን ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከ45 ፕሮጀክቶች ውስጥ 31 በቻይና ኩባንያዎች የተያዙ ናቸው፡፡ ይህም የአገር ውስጥና የውጭ ሥራ ተቋራጮች የተረከቡዋቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ቁጥር ተቀራራቢ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ፕሮጀክቶች የውጭ ሥራ ተቋራጮች መቆጣጠራቸውን ያሳያል፡፡

  ይሁን እንጂ በሁለት ተከታታይ ግምገማዎች የውጭ ኩባንያዎች አፈጻጸም ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ያነሰ መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዲህ ያለው አፈጻጸም ክፍተት እየታየ አሁንም የውጭ በተለይ የቻይና ሥራ ተቋራጮች አዳዲስ ሥራዎችን እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡ ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ እንዲህ ዓይነት ምዘናዎች በየጊዜው የሚካሄዱ በመሆናቸው በአንድ ወቅት በተሰጠው የጊዜ ገደብ መሠረት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሆነ በቀጣይ ጨረታዎች አይሳተፍም፡፡ ይህ ማለት ግን እስከ መጨረሻው አይጫረትም ማለት ሳይሆን፣ በቀጣይ በሚደረገው ግምገማ ወቅት አፈጻጸሙ ከተሻሻለ እንደገና መሳተፍ እንዲችል ዕድል ይሰጠዋል፡፡    

  እንዲህ ያለው የውጭ ሥራ ተቋራጭ አፈጻጸም ከአገር በቀል ኩባንያዎች ጋር ያለውን አፈጻጸም በማነፃፀር ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የግንባታ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች የተሻሉ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ በአንፃሩ ግን አሁንም የውጭ ኩባንያዎች በተለይ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን እየወሰዱ፣ የአገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ዕድል እያጣበቡ መሄድ ለአገር በቀሎቹ ህልውና አስጊ እየሆነ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ብዙዎቹን ሥራ ተቋራጮች እያሳሰበ እንደሚገኝ ነው፡፡

  በተለይ የቻይና ሥራ ተቋራጮች ከመንግሥታቸው የሚያገኙትን ድጋፍ ይዘው በተለያየ ስያሜ የግንባታውን ዘርፍ እየተቆጣጠሩ መሆናቸው፣ ለአገር በቀል ኩባንያዎች ሥጋት እየፈጠረ ከመሆኑም በላይ፣ በዚህ ዘርፍ መንግሥት የተለየ አቅጣጫ መከተል እንደሚኖርበትም እየተጠቆመ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ማኅበርም በዚህ ጉዳይ ላይ እየመከረ ስለመሆኑ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img