Wednesday, October 4, 2023

በጥልቀት መታደስ ጥልቀቱ ምን ድረስ ነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቀደም ሲል ሕወሓት በኋላም በኢሕአዴግ ደረጃ ደርግን የተዋጋው ድርጅት በአገሪቱ ውስጥ አሉ ያላቸውን የዴሞክራሲና የብሔር ጥያቄዎች በጥልቀት የገመገመ ነበር፡፡ የድርጅቱ የውስጥ አወቃቀር ኮሙዩኒስታዊ ገጽታ ነበረው፡፡ ዴሞክራሲያዊነቱና ሕዝባዊነቱም የሚመነጨው ከማርክስምና ሌኒኒዝም ፍልስፍና በሚቀዳ አስተሳሰብ ነበር፡፡

ሕዝቡን ከጭቆና ነፃ ለማውጣት ታጋዩም አመራሩም የታጠቀው ዋና ስንቅም ሕዝባዊነትና መስዋዕት ለመሆን ዝግጁነትን ነበር፡፡

በ1966 ዓ.ም. አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም ሆነ በደርግ ያልተመለሱ የማንነትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ለመመለስም፣ ለዘመናት የቆየውን አሃዳዊ ሥርዓት አፍርሶ በፌዴራላዊ ሥርዓት የመለወጥ ፕሮጀክትን እንደ ዓላማ የተያያዘው ነበር፡፡

ይኼ በግራ ዘመም አተያይ የተተነተነው ችግርና መፍትሔ አስፈላጊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ዓለም አቀፋዊ የርዕዮተ ዓለም ትግል መብቃት አጋጠመ፡፡ በ1980ዎቹ ውስጥ ያበቃው የምሥራቁና የምዕራቡ ዓለም ርዕዮተ ዓለም ፍጥጫ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡

የ17 ዓመታቱ የትጥቅ ትግል የርዕዮተ ዓለም ግጭት አመላካች አልነበረም፡፡ ሥልጣኑ ያበቃው ደርግም ከአሸናፊው ከኢሕአዴግ ባልተናነሰ ማርክሲስታዊ ሥርዓት ነበር፡፡ ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ ድርጅትም ራሱን ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ነበረበትና በከፊል የምዕራቡ ዓለም መመርያ የሆኑትን ነፃ ገበያ፣ ነፃ አስተሳሰብና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በመርህ ደረጃ ለመቀበል ተገዷል፡፡ የምዕራቡ ዓለም ድጋፍም ተችሮታል፡፡ ኢሕአዴግ ያልተቀበላቸው የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ የልማት መርሆች እንዳሉ ሆነው፡፡ ለብዙዎች የመጀመሪያው የድርጅቱ ህዳሴ መባል ያለበት ይኼው የርዕዮተ ዓለም ክለሳ ነበር፡፡ ዛሬም ከ25 ዓመታት በኋላ እነዚህ ጥያቄዎች በኢሕአዴግ ጠረጴዛ ላይ ናቸው፡፡

በፌዴራላዊ አስተሳሰብ የተዘጋጀው አዲሱ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸው የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ቃል ኪዳኖች ያካተተ፣ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ሕገ መንግሥት ፀድቆ ተግባር ላይ ውሏል፡፡ ተግባራዊነት ላይ ግን ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ከሕገ መንግሥቱ መረቀቅ በፊት ሥራ ላይ በዋለው የሽግግር መንግሥት ቻርተር ወቅት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ተሳትፎ ይገኝበታል፡፡ የራሱን አሻራም አሳርፏል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በቀደሙት ሥርዓቶች የማንነት ጭቆና ከደረሰባቸው መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ዛሬ ግን ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ የቅቡልነት ጥያቄ ከተነሳባቸው ክልሎች ግንባር ቀደሙ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር የተቀሰቀሰው አመፅ ለአንድ ዓመት መዝለቁ ይታወሳል፡፡ ቀጥሎም ሁለተኛው ትልቁ ክልል በሆነው ከአማራ ክልል ተመሳሳይ ሁከት ተቀስቅሶ ነበር፡፡

1993 እና 1997

በ1990 ዓ.ም. ከኤርትራ ወረራ በኋላ በተለይ ሕወሓት ውስጥ የተከሰተው ቀውስ ትልቁና ኢሕአዴግንም የነካ፣ በአጠቃላይ ለአዲሱ ሥርዓትም መነቃነቅ የፈጠረ ነበር፡፡ የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ገብሩ አሥራትንና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ስዬ አብርሃን ጨምሮ፣ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የነበሩ ከአሥር በላይ ሰዎች ከድርጅቱ እንዲወገዱ ምክንያት የሆነ መሰነጣጠቅ ነበር የተፈጠረው፡፡

በአሸናፊው (በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የሚመራ) አካልና ‹‹አንጃ›› ተብለው በተገለሉ ሰዎች መካከል ዛሬም ድረስ የመሰነጣጠቁ አጀንዳ ላይ ስምምነት የሌለ ቢሆንም፣ የኤርትራ ጉዳይና ሙስና ተደጋግመው የሚነሱ ነጥቦች ናቸው፡፡

በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው ቡድን ድርጅቱ የመበስበስ አደጋ እንደገጠመው ቦናፓርቲዝም በሚል ርዕስ ያቀረበው አጀንዳ ነበር፡፡ በአንጃነት የሚታወቁ ሰዎች ከድርጅቱ መውጣታቸውን ተከትሎ የታወጀው ህዳሴ አገሪቱ በልማት ወደፊት እንድትራመድ አስችሏል ተብሎ ይታመናል፡፡

የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች አብዮታዊ ዴሞክራሲ በመባል የሚታወቀው ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር እንደሆነና ነፃ አስተሳሰብን አይፈቅድም በማለት በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ነበር፡፡ በተለይ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ዋዜማ የታወጀው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሥርዓት በአገሪቱ ለተከታታይ ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያመጣ ቢሆንም፣ እሱን የሚመጣጠን የዴሞክራሲ ለውጥ አልመጣም ተብሎም ይተቻል፡፡

ኢሕአዴግን ከትጥቅ ትግል ጀምሮ የሚከታተሉ የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር አሌክስ ዲዋል፣ ሥርዓቱ እምብዛም ውይይት ያልተደረገበትና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በጎ ፈቃድ ላይ ብቻ መሬት የወረደ ለድርጅቱ ባዕድ አካሄድ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ እሱም ብቻ ሳይሆን ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ እንደማይሠራ፣ እንዲያውም እስከዛሬ ድርጅቱ ያስመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት ይዞ እንዳይሄድ አድርጎታል በማለት አሌክስ ዲዋል ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በተደጋጋሚ ባደረጉት ንግግርና በተለይ ደግሞ የድርጅቱ ንድፈ ሐሳብ መተንተኛ በሆነው በአዲስ ራዕይ መጽሔት ተደጋግሞ እንደተተነተነው፣ ተቃዋሚዎች የሚያራምዱት የጥፋትና የከሰረ ፖለቲካ መሆኑን፣ ኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በማሸነፍ ‹‹ልማታዊነት›› የበላይነት እንዲኖረው የተቀረፀ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

ከሥርዓቱ መታወጅ ይያያዝ አይያያዝ በቂ ማረጋገጫ ባይገኝም በአገሪቱ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የታየው የዴሞክራሲ ፍንጭ ለሁለተኛ ጊዜ አልተደገመም፡፡ የምርጫውን ቀውስ ተከትሎ በተከታታይ የታወጁ የሚዲያ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብና የፀረ ሽብር አዋጆች የአገሪቱን ፖለቲካ የማያፈናፍን አድርገውታል ተብሎ ይተቻል፡፡ በእርግጥ በሁለቱ ተከታታይ ምርጫዎች በተለይ ደግሞ ባለፈው ዓመት በተካሄደው አምስተኛ ዙር ምርጫ ኢሕአዴግና አጋሮቹ የፓርላማ መቀመጫዎችን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረውታል፡፡

የታወጀው የልማታዊ መንግሥት ሥርዓት ስዊድን፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይናን የመሳሰሉ አገሮችን በሞዴልነት የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ በእነዚህ አገሮች አንድ ፓርቲ ከ30 እስከ 60 ዓመታት በአውራነት የቆየበትና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ሽግግር መጥቷል ይላል፡፡ ተቃዋሚዎች ‹‹የአንድ ፓርቲ ሥርዓት›› በማለት የሚተቹት ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ‹‹ጤነኛና ምክንያታዊ›› ተቃዋሚዎች እስኪፈጠሩ ድረስ በ‹‹አውራ ፓርቲ›› ሥርዓት አገር የመገንባት ዓላማ እንዳለው ደጋግሞ ተናግሯል፡፡

ዴሞክራሲን የመገንባት ሒደት በተቃዋሚዎች ፓርላማ መግባትና አለመግባት እንደማይወሰን አቶ መለስ ይሞግቱ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በውስጡ የመከራከርና ሕዝብን የማሳተፍ ባህልና ስትራቴጂ እንዳለው በመናገር፡፡ በዋናነት ግን በተለይ አዲስ ራዕይ በሐምሌ – ነሐሴ 2001 ዓ.ም. ዕትሙ ‹‹የአመራር መተካካት በኢሕአዴግ›› በሚለው ዋና የትንተና ጽሑፉ፣ በመንግሥትና በድርጅት የአመራር መተካካት በትውልዶች የዱላ ቅብብል እንደሚሳካ ያትታል፡፡ ወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‹‹ሥልጣን እለቃለሁ›› በማለት ለፋይናንሻል ታይምስ የተናገሩበት ጊዜ ሲሆን፣ የአመራር መተካካት የግለሰብ የፍላጎት ሳይሆን በተለይ በትጥቅ ትግል የነበረውን አመራር በአዲስ አመራር የመተካት መርህ የተቀመጠበት ጊዜ ነበር፡፡ በሌላ ዕትም እንደተተነተነው ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻውን በራሱ አላስፈላጊ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችልና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን ላይ የወጣውን የጀርመን የናዚ ሥርዓት በምሳሌነት ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም እንደ 1997 ዓ.ም. ሕዝቡ ቀይ ካርድ ከማሳየቱ በፊት የመበስበስ አደጋ ሳይመጣ በመተካካት መርህ ዴሞክራሲያዊ የአመራር ለውጥ መፍጠር፣ በልማታዊ መንግሥት እንደ አማራጭ መንገድ የተወሰደ ይመስል ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ሬኔ ሊፎርት ይህንን የልማታዊ መንግሥትነት ሒደት በተነተኑበትና ‹‹Ethiopia’s Crisis›› በሚል ርዕስ የኢትዮጵያን ያለፈው ዓመት ቀውስ በገመገሙበት ጥናታዊ ጽሑፍ አንድ ከፍተኛ የኢሕአዴግ አመራር አነጋግረው ያገኙት ምላሽ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ካፒታሊዝም ሥርዓት ከመሸጋገሯ በፊት የብዙኃን አስተሳሰብ [የመድብለ ፓርቲ] ሥርዓት አንጫንም፡፡ የተለያዩ መደቦች ሲፈጠሩ ብቻ ራሳቸውን የሚወክል ፓርቲ ያቋቁማሉ፤›› ይላል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ እየተመኘ ያለው ልማትና ዴሞክራሲ በአንድ ጊዜ እንዲመጣ ሳይሆን፣ መጀመርያ ልማት ከዚያ ቀጥሎ ዴሞክራሲ ነው፤›› የሚል ድምዳሜ ያስቀምጣሉ ፕሮፌሰሩ፡፡     

የቀውሱ አተያይ

ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች የተዘጋጀውን የጋራ ማስተር ፕላን በመቃወም የተጀመረው አመፅ ለዘጠኝ ወራት ዘልቋል፡፡ ከኦሮሚያ ወደ አማራ ክልልም ተቀጣጥሎ ነበር፡፡ በአብዛኛው እኔ ነኝ ያለ መሪ ያልነበረው ይኼው ድንገተኛ ሁከት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመራና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ አክራሪ የፖለቲካ ኃይሎችም እጃቸውን አስገብተውበታል ተብሎ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ የኋላ ኋላም ግብፅንና ኤርትራን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ቁጥር አንድ ጠላት የተባሉ አገሮች እንደነበሩበትም በቂ መረጃዎች መገኘታቸው በስፋት ተገልጿል፡፡

ያም ሆነ ይህ መንግሥት ከመነሻው ጀምሮ የሁከቱን ምክንያት ወደ ውጭ ለመግፋት አለመሞከሩንና ከውስጥ የመነጨ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል፡፡ ከመነሻው ግን መንግሥት የተነሳውን ጥያቄ የቢሮክራሲ ማሻሻያ አድርጎ አይቶታል፡፡ ምናልባትም ቀደም ሲል በተለይ በመቐለው አሥረኛው የኢሕአዴግ ጉባዔ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሥርዓቱ አደጋ እየሆነ ነው ብሎ ከመቀበሉ፣ ከአስተዳደርና ከፍትሕ ዕጦት የመነጨ መሆኑን ከማመኑ በላይ ይዘላል ብሎ አላመነም ነበር፡፡ የሕወሓት ነባር ታጋዮችና ወታደራዊ አዛዦች ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ (የቀድሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዥር ሹም)፣ እንዲሁም ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት (የቀድሞ አየር ኃይል ዋና አዛዥ) ለረዥም ጊዜ ድምፃቸውን አጥፍተው ከቆዩ በኋላ፣ በተከሰተው ቀውስ ላይ የራሳቸውን አተያይ አስቀምጠው ነበር፡፡ ጉዳዩ የቢሮክራሲ ሳይሆን የሥርዓት ቀውስ መሆኑንና ይህንን የሚመጥን የሥርዓት ማሻሻያ እንዲደረግ መዋቅራዊ የመፍትሔ ሐሳቦች ሰንዝረዋል፡፡

ከመነሻው ከኢሕአዴግ የሐሳብ አመንጪ ሰዎች እምብዛም አወንታዊ ምላሽ ባያገኙም፣ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ተመሳሳይ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር (በአሁኑ ወቅት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል) አቶ ልደቱ አያሌው ችግሩ የሥርዓት ቀውስ ምልክት እንደሆነ፣ ድርጅቱ እሱን የሚመጥን የሥርዓት ማሻሻያ እንዲያደርግ ጠይቀው ነበር፡፡ በእርግጥ ጫፍ ድረስ ሄደው የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት የጠየቁ ሌሎችም ነበሩ፡፡

መታደስ እስከ ምን? ከማን ጋር?

ሁከቱ ከመነሳቱ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመሩት አዲሱ መንግሥት በተቋቋመ በመጀመሪያዎቹ ወራት፣ የመንግሥት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ያደረገው ጥናት ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ የሥርዓቱ ችግር በድርጅቱ ጉባዔ ከተገመገመው በላይ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ እምብዛም ሳይቆይ ሁከቱ መነሳቱ ኢሕአዴግ ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት እንደተቀደመም በአንዳንዶች ተተንትኗል፡፡

ያም ሆነ ይህ በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው ሁከት ኢሕአዴግ ሥልጣን በያዘ በ25 ዓመቱ ውስጥ ከፍተኛው ሆኗል፡፡ ሁከቱን በመደበኛ ሕግና ሥርዓት ከማስከበር በላይ በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማወጅ ተደርሷል፡፡ አዋጁ ተፈጥሮ የነበረውን ቀውስ ማስቆም የቻለ ሲሆን፣ በአገሪቱ አንዣብቦ የነበረው በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ፍራቻን በማስተካከል የአገሪቱ ሰላም ቀድሞ ወደነበረበት መመለስ ችሏል፡፡ በዚህ መሀል አንድ ነገር እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ በመንግሥትና በገዥው ፓርቲ ውስጥ የአመራር ለውጥና ማሻሻያ ማድረግ፡፡

አዋጁ ከመታወጁ ቀደም ብሎ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለሁለቱም ምክር ቤቶች ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ በመንግሥትና በድርጅቱ ውስጥ መሠረታዊ የአወቃቀር ለውጥ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በገቡት ቃል መሠረት ኢሕአዴግ ለበርካታ ሳምንታት በዝግ ከፍተኛ ግምገማ አድርጓል፡፡ በተናጠልም አባል ድርጅቶቹ በየፊናቸው ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታችኛው የአመራር እርከን ድረስ እየተገማገሙ ይገኛሉ፡፡ ከአራቱ አባል ድርጅቶች መካከል ኦሕዴድ ነባር ሊቀመናብርቱን በማሰናበት አዳዲስ አመራሮች ከማምጣቱም በላይ፣ ምሁራንና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ያልሆኑ ወደ ኃላፊነት በማምጣት ግንባር ቀደም ዕርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ ብአዴንም በብዙዎች እንደተጠበቀው ሊቀመናብርቱን ባያሰናብትም አዳዲስ ምሁራን ወደ ካቢኔ በማምጣት ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ካቢኔውን እንደ አዲስ በማዋቀር ከሚኒስትሮች መካከል ዘጠኙ ባሉበት እንዲቀጥሉ በማድረግ ለ21 አዳዲስ ሚኒስትሮች ሹመት ሰጥቷል፡፡ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ወደ ከፍተኛ ሥልጣን መምጣታቸው ሲሆን፣ በብዙዎች ዘንድ ምሁራንን አያቀርብም ተብሎ በሚታማው በኢሕአዴግ ታሪክ እንደ አዲስ ምዕራፍ ታይቷል፡፡ ተቃዋሚዎች ግን አሁንም ከአዲሱ ካቢኔ አዲስ ነገር እንደማይጠብቁ ይናገራሉ፡፡

የኢሕአዴግ ዋናው መሥራች ሕወሓት ቀደም ሲል የአመራር መተካካት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ አሁንም በከፍተኛ አመራር ደረጃ ግምገማ ተካሂዷል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሠራር በከፍተኛ ደረጃ መስፈኑን ገምግሟል፡፡ በመንግሥት ደረጃ በቅርቡ የተወሰነ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ በኢሕአዴግ ደረጃ በቀረበው በጥልቀት የመታደስ ሰነድ መሠረት እየተገማገመም ነው፡፡ የድርጅቱ መሥራችና አንጋፋ ታጋይ አምባሳደር ሥዩም መስፍን በቅርቡ ‹‹ውራይና›› ለተባለው የትግርኛ መጽሔት በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ሕወሓት ከሙስናና ከፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ጋር በተያያዘ ውስጡን መፈተሹን ተናግረዋል፡፡ እስከ ዛሬ በተለይ ምሁሩን ያገለለ አካሄድና ነፃ አስተሳሰብን የማይፈቅድ መንገድ እንደነበር መተማመን ላይ መደረሱንም አስረድተዋል፡፡

ካቢኔውን እንደ አዲስ ያዋቀረው ብአዴንም የኢሕአዴግን ሰነድ መሠረት አድርጎ ያለፉትን 15 ዓመታት የክልሉን ጉዞ መገምገሙን የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በሰፋፊ መድረኮች ከማዕከላዊ ኮሚቴ ጀምሮ እስከ ወረዳና ዞን አመራሮች ድረስ እስካሁን ድርጅቱ አለኝ የሚላቸው 7,500 የሚደርሱ አባላት ተገማግመዋል፡፡

ድርጅቱ አምስት ዋና ዋና ችግሮች ነቅሶ የለየ መሆኑንና በተለይ ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊነት፣ የሕዝቡን አንገብጋቢ ችግሮች አለማዳመጥ፣ የአባላቱ በመርህ የለሽ አመለካከትና በትምክህት የመለከፍንና ዘረኝነትን የመሳሰሉ ጉዳዮች ለይቶ ገምግሟል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቱ ቀና ሲሆን ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ ያህል ድርጅቱ ሲበላሽ ምን ያህል የጥፋት ኃይል ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለሥልጣን ያለው አመለካከትና አተያይ መዛባት›› የችግሮቹ ምንጭ አድርገውም ይመለከታሉ፡፡

ዛሬም የ‹‹አፈጻጸም›› ችግር

አቶ አለምነው እንደሚሉት ኢሕአዴግ ግምገማ የጀመረው በአፈጻጸም ችግር ላይ እንጂ የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ አልነበረም፡፡ እንደ እሳቸው እምነት የልማታዊ መንግሥት ፍኖተ ካርታና እሱን ለማስፈጸም የተቀረፁ ስትራቴጂዎች አማራጭ የላቸውም፡፡ አቶ አለምነው፣ ‹‹ያቃተን መስመሩን በተሟላ ሁኔታ ጨብጦና አምኖ የመፈጸም ችግር ነው፡፡ ይኼ መስመር የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደ ብሩህ ጎዳና መርቷቸዋል፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ይህንን መጣል ወደ ጨለማ የሚወስድ መንገድ መከተል ነው፤›› በማለት፡፡

አቶ ሔኖክ ሥዩም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዕጩ ሲሆኑ፣ ከኢሕአዴግ የሚጠበቀው የአመራር መሻሻል እንጂ የአስተሳሰብና የመስመር ለውጥ አይደለም ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሕዝቡ ጥያቄ የመንግሥት ለውጥ ነው ወይ?›› በማለት ጥያቄውን ራሳቸው ውድቅ ያደርጉታል፡፡

ህዳሴ የማድረግ ዕቅድ ቀደም ሲል ተይዞ የነበረ እንጂ ሁከቱን ተከትሎ እንዳልመጣ የአቶ አለምነውን ሐሳብ አቶ ሔኖክ ይቀበላሉ፡፡ ኢሕአዴግም ‹‹የመስመርና የርዕዮተ ዓለም ማሻሻያ ማድረግ ሳይሆን፣ የተያዘውን መስመር ለማስፈጸም የተስተካከለ ቁመና የለኝም፤›› የሚል መነሻ እንዳለው ያምናሉ፡፡ የፓርቲውን አሠራርና አመራር ለመፈተሽና ብቃት ያለው አመራር ለመፍጠር የተሰጠውን ትኩረት ይቀበላሉ፡፡ ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ በሕዝቡ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ ያገኛል ብለውም ያምናሉ፡፡ ኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ የያዙት ‹‹በጥልቀት›› የመታደስ ዘመቻ አዝማሚያ፣ በፓርቲው ውስጥ ፍተሻ የማድረግና የማጥራት እንጂ የመርህና የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት አይመስልም፡፡

‹‹የሕዝቡ ጥያቄና ቁጣ በፓርቲ የውስጥ መታደስ መልስ ያገኛል ወይ?›› የሚል ጥያቄ ከቀድሞ የሕወሓት መሥራችና አመራር እንዲሁም የዓረና ትግራይ ፓርቲ መሥራች አቶ ገብሩ አሥራት ይነሳል፡፡ አቶ ገብሩ ህዳሴው የታለመለትን ዓላማ የማሳካት ሁኔታ እንዳለው ይቀበላሉ፡፡ ሆኖም ‹‹ጊዜው የሚጠይቀው መታደስ ከሆነ›› የሚል ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ፡፡

በአንድ ወቅት በምሥራቅ አውሮፓ ከሶሻሊስት አስተሳሰብ ለመውጣት የተደረገው ‹‹ዙሪያ ምላሽ›› የአስተሳሰብ ለውጥ ፍሬያማ መሆኑ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው ቀውስ ኢሕአዴግ ከሚከተለው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ የመነጨ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ነፃ አስተሳሰብ አይቀበልም፡፡ ተቃዋሚዎችን በጠላትነት የሚፈርጅ ነው፡፡ ለመታደስ ከሆነ ከዚህ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም መውጣት ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን የመታደስ ፍንጭ የታየው በ1997 ዓ.ም. እንደሆነ የራሳቸውን ግልከታ ይገልጻሉ፡፡ አሁንም አንድ ፍንጭ ብቻ ተመልክተዋል፡፡ የምርጫ ሕጉን ለማሻሻል የተገባውን ቃል፡፡ ሆኖም እንደ አቶ ገብሩ እምነት፣ መታደስ ሌሎች በርካታ ፓኬጆችን መያዝ ነበረበት፡፡ ሙስናና ፀረ ዴሞክራሲ አስተዳደር ምንጩ የፖለቲካ ቀውስ ውጤት እንደሆኑ ያምናሉ፡፡ ግምገማውንና የካቢኔ ለውጡንም በአወንታዊ ጎኑ ይመለከቱታል፡፡ ‹‹አሁን ሕዝቡ እየጠየቀ ያለው ግን ከዚህ በላይ ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ከድሮ የተለዩ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡ በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች ‹‹ኦሮሚያ ፈርስት፣ አማራ ፈረስትና ትግራይ ፈረስት›› የሚባሉ አዝማሚያዎች አደገኛ መሆናቸው በመግለጽ፣ ኢሕአዴግ ልብ ገዝቶ ሁሉንም ያካተተና የተፈጠረውን የመበታተን አዝማሚያ ተሻግሮ የሚሄድ መንገድ እንዲቀይስ ይጠይቃሉ፡፡

ንቅናቄውን የአክራሪ ዳያስፖራ እጅ እንደተቀላቀለበት ቢያምኑም፣ በአጠቃላይ የሕዝብ ቁጣ መገለጫ መሆኑን አቶ ገብሩ ያስረዳሉ፡፡ የአንድ ፓርቲ አገዛዝና ʻሌጋሲʼ የሚሉ አስተሳሰቦች እንዲቀሩ በመጠየቅ፡፡

የኢዴፓ የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ‹‹ጥያቄው ባህሪውን ቀይሯል›› በማለት ከአቶ ገብሩ ጋር ተመሳሳይ ምልከታ አላቸው፡፡ በ1993 ዓ.ም. በተወሰነ ደረጃ ህዳሴ መካሄዱን ግን ያምናሉ፡፡ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት እየተንከባለሉ እዚህ የደረሱት የኑሮ ውድነትና የፍትሕ ዕጦት ጥያቄዎች በተለመደው አካሄድ አይፈቱም ይላሉ፡፡ ‹‹ህዳሴው የፓርቲ የውስጥ ጉዳይ እንጂ የሕዝብ አይደለም፡፡ ጥያቄው ግን የመነጨው ከሕዝብ ነው፤›› በማለት ጥልቅ ውይይት የሚያስፈልገው ከሕዝብ ጋር ነው ይላሉ፡፡ ቀጥተኛ ውይይት በማድረግና የሕዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ ብቻ መፍትሔ ይኖራልም ይላሉ፡፡ ‹‹ተሃድሶ ዕድሜ ማራዘሚያ እንዳይሆን›› በማለት እንኳን ራስን በራስ በማደስ፣ የተነሳውን ጥያቄ ከተቃዋሚዎች በመነጋገር ብቻም አይፈታም ይላሉ፡፡ ‹‹ጉዳዩ ከውክልና ወጥቷል፤›› በማለት፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በካሪኩለም የዶክትሬት ዕጩ የሆኑት አቶ አብረሃ ኃይለዝጊ በበኩላቸው፣ የተሃድሶው እንቅስቃሴ የተለየ ስሜት እንዳልፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በኢሕአዴግ ዘንድ እንደ ፋሽን አዳዲስ ቃላት መፍጠር የተለመደ ነው፤›› በማለት፡፡ ‹‹አሁን የተለየ ችግር ተፈጥሯል›› የሚሉት አቶ አብረሃ፣ የድርጅቱ አዝማሚያ ግን ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችል የተለየ መንገድ እየፈለገ እዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹አንደኛ ነገር መታደስ በዘመቻና በድንገት አይመጣም፡፡ ሁለተኛ ከልብ መታደስም ቢፈልግ ʻማን ይቀበላልʼ የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በተደጋጋሚ ብዙ ንቅናቄ ለመፍጠር ቃል ተገብቷል፡፡ ግን አላደረገም፡፡ ጭብጡ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ ማንም አያምንህም፤›› ይላሉ፡፡ አቶ አብርሃ፣ ‹‹በ1993 ዓ.ም. የተደረገው ተሃድሶ ለዚህ ቀውስ ካደረሰን ሌላ ማራዘሚያ ተሃድሶ ለምን እናደርጋለን?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

አቶ አብረሃ በኦሮማያና በአማራ ክልሎች የተደረጉ የአመራር ለውጦችን በአወንታዊ መልክ ያዩዋቸዋል፡፡ የተሃድሶ ምንጭ አድርገው ግን አይመለከቱዋቸውም፡፡ ‹‹ለእኔ ተሃድሶ መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ነው፤›› በማለት ከአቶ ገብሩና ከአቶ ሙሼ ጋር ይስማማሉ፡፡ መደረግ ነበረባቸው የሚሉዋቸው ሕገ  መንግሥቱን ማክበር፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱ የሰብዓዊ መብት ቃል ኪዳኖችን ማረጋገጥ ነበር፡፡ ‹‹አሁን ጊዜ አልፎበታል›› የሚሉት መፍትሔ ሲሆን፣ ‹‹ዛሬ ኢሕአዴግ እጅግ ከሚያምነው ሕዝብ ሳይቀር እምነት አጥቷል፡፡ ይኼ ቢደረግ የምለው መፍትሔ የለኝም፤›› በማለት በተስፋ መቁረጥ ሐሳባቸውን ይቋጫሉ፡፡

ፕሮፌሰር ሬኔ ሊፎርት በኢትዮጵያ ታሪክ የመንግሥት ለውጥ የሚመጣው በገዥው አካል ውስጥ ያፈነገጠ አካል ሲኖር እንደሆነ በመግለጽ፣ የታሰቡ የተሃድሶ እንቅስቃሴዎች ዋናውን የችግሩን ምንጭ የሚነቅሱ ባይሆኑም፣ የቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ እየገባ ቢሆንም የኢሕአዴግ ሥርዓት እንዲህ በቀላሉ አይፈርስም በማለት ይደመድማሉ፡፡ ፕሮፌሰሩ በሁከቱ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ውስጥ በመዘዋወር የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማነጋገር ካገኙት መረጃ ድምዳሜ ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል፡፡                       

 

    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -