ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቆራረጥ የነበረው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከተተከሉ 126 ዋና መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ውስጥ ከ30 በላይ የሚሆኑት ምሰሶዎች በንፋስ ኃይል በመውደቃቸው መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በተለይ ኅዳር 24 እና 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሊባል በሚችል ሁኔታ ከፍተኛ የሆነ ንፋስ በመከሰቱ ከተተከሉ ረዥም ዓመታት ያስቆጠሩ ዋና መስመር ተሸካሚ የእንጨት ምሰሶዎች ሊቋቋሙት ባለመቻላቸው፣ ተገርስሰው መውደቃቸውን የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዲስትሪቢዩሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ብርሃኔ እንደተናገሩት፣ በመላው አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ተሸካሚ የኮንክሪት ምሰሶዎች እየተገነቡ ነው፡፡ ኤስጂዲሲሲ የተባለው የቻይና መንግሥት ኩባንያ በ80 ሚሊዮን ዶላር መቐለ፣ ደሴ፣ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋን ጨምሮ በስምንት የክልል ከተሞች የኮንክሪት ማሠራጫ ግንባታ ላይ ነው፡፡ መስመር ከመለወጡ ጎን ለጎንም የትራንስፎርመር ዕድሳትም ይከናወናል ብለዋል፡፡
ዘፉ (ZHEFU) የሚባለው ሌላው የቻይና ኩባንያ በ20 ሚሊዮን ዶላር፣ ፓወር ቻይና የሚባለው ኩባንያ ደግሞ በ160 ሚሊዮን ዶላር የአዲስ አበባን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመር የመቀየርና አቅም የማሳደግ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡
ኩባንያዎቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የገቡ በመሆናቸው መንግሥት መስመር የመቀየርና አቅም የማሳደጉን ሥራ በተያዘው የበጀት ዓመት እንዲያጠናቅቁ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ይጠናቀቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ አንዱ ኩባንያ (ፓወር ቻይና) ዘግይቶ በመጀመሩ ወደ 2010 ዓ.ም. ሊተላለፍ ይችላል የሚል ግምት ቢኖራቸውም፣ ዋና ዋና ሥራዎቹን ግን በዚህ ዓመት ሊያጠናቅቅ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የመስመር ዝርጋታውና አቅም የማሳደጉ ሥራ ሲጠናቀቅ፣ የኃይል መቆራረጥም ሆነ ሌሎች ችግሮች ሊቀረፉ እንደሚችሉ አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡
ሰሞኑን የደረሰው መቆራረጥ ከኃይል አቅርቦት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ የተፈጥሮ አደጋ መሆኑን ደንበኞች ተረድተው አስፈላጊው ጥገና እስከሚደረግ እንዲታገሱ ጠይቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ 25 የማሠራጫ ጣቢያዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ መስፍን፣ በ126 ዋና መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ከማሠራጫ ጣቢያዎቹ የሚወጣው ኃይል በሁሉም የከተማው አካባቢዎች ተሠራጭቶ ተደራሽ እየሆነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ከ30 በላይ የሚሆኑ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች በመገርሰሳቸው፣ በበርካታ አካባቢዎች የኃይል መቆራረጥና መጥፋት መከሰቱን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ችግር ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች ከዓለም ባንክ፣ ከነዳጅ አቅራቢ አገሮች (OPEC) እና ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘው ከ260 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር ግንባታዎቹን እያፋጠኑ መሆናቸው ታውቋል፡፡