Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየትግራይ ክልል በርከት ያለ ምሁራን የተካተቱበት አዲስ ካቢኔ አዋቀረ

የትግራይ ክልል በርከት ያለ ምሁራን የተካተቱበት አዲስ ካቢኔ አዋቀረ

ቀን:

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በአብዛኛው የዶክተርነት ማዕረግ ባላቸው ምሁራን አዲስ ካቢኔ ለማዋቀር የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ያቀረቧቸውን ዕጩዎች አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠራው አስቸኳይ ጉባዔ ስድስት አዳዲስ የቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል፣ እንዲሁም የክልሉን ዋና ኦዲተር ኮሚሽነር ሹመት ማፅደቁን ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ዓባይ ወልዱ ተሿሚዎችን ለምክር ቤቱ ሲያቀርቡ አራት ዋና ዋና መሥፈርቶችን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሕገ መንግሥቱን በማመን በቁርጠኝነት ተግባራዊ የሚያደርጉ፣ የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ዓላማ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂን በተመለከተ ሥልጠና የወሰዱ፣ በቂ ትምህርትና የሙያ ሥልጠና ዝግጅት ለተፈለገው ዘርፍ የሚስማማና የሚመች ልምድ ያላቸው፣ እንዲሁም ታማኝነትና ከሙስና የፀዱ መሆናቸው የመምረጫ መሥፈርቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

ለቢሮ ኃላፊነት የተመረጡት ስድስቱም ተሿሚዎች በዶክትሬት ማዕረግ የሚጠሩ ሲሆን፣ ለሌሎች ተቋማት የተመረጡ ተጨማሪ ሦስት ተሿሚዎች በተመሳሳይ ማዕረግ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ 12 ተሿሚዎች ሹመታቸው ሲፀድቅ ሦስቱ በካቢኔው ውስጥ ቀድመው የነበሩ ሲሆኑ፣ በአዲሱ አወቃቀር የቢሮ ለውጥ ያደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡ ለቢሮ ኃAnchorላፊነት የተመረጡት ዶ/ር ኢንጂነር ገብረ መስቀል ካህሳይ  (የትምህርት ቢሮ ኃላፊ)፣ ዶ/ር አትንኩት መዝገበ  (የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ አንድ ዘርፍ ኃላፊ)፣ ዶ/ር ተስፋ ሚካኤል ገብረ ዮሐንስ (የውኃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ)፣ ዶ/ር አብርሃ ኪሮስ  (የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ)፣ ዶ/ር የትምወርቅ ገብረ መስቀል (የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ) እና ዶ/ር ሙሉጌታ ሀዱሽ (የቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ) ናቸው፡፡

በተጨማሪም ዶ/ር ፋና ሐጎስና አቶ አማኑኤል አሰፋ የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ተሹመዋል፡፡ እንዲሁም ዶ/ር ረዳኢ በርኼ ደግሞ የክልሉ የዋና ኦዲተር ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።

የቢሮ ለውጥ ያደረጉ አመራሮችን በተመለከተ አቶ ገብረ መስቀል ታረቀ የፀጥታና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ጎይቶም ይብራህ  የወጣቶች ጉዳይና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ በመሆን ሲሾሙ፣ ዶ/ር ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ የደቡባዊ ምሥራቅ ዞን አስተዳዳሪ ሆነዋል፡፡

በጥቅምት ወር 2009 ዓ.ም. የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ቀደም ብሎ በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ጉባዔ ላይ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች መሠረት በማድረግ ለስምንት ቀናት ስብሰባ አካሂደው ነበር፡፡ በወቅቱ የ15 ዓመታት ግምገማ በማካሄድ የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ በተመለከተ ባለ አሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡

በመግለጫውም፣ ‹‹የያዝነው ሥልጣን በዋናነት ለሕዝብ አገልግሎት አላዋልነውም፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹ወጣቶች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱና በራሳቸው አመለካከት እንዳይራመዱ መደረጋቸውንና ለዚህም ሁሉ መነሻው ፀረ ዲሞክራሲያዊ የሆነ አካሄድ በመስፈኑ ነው፤›› ተብሎ ነበር፡፡ ‹‹በእነዚህና መሰል ምክንያቶች በድርጅቱና በሕዝቡ መካከል ለዘመናት የቆየው አንድነትና መተማመን በተለያዩ ደረጃዎች ተሸርሽሯል፤›› ሲልም ጉባዔው በመግለጫው ገልጿል፡፡  

በተመሳሳይ ቀደም ብሎ የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግሥታት ካቢኔ ማዋቀራቸው ይታወሳል፡፡

የክልሎቹ አዲሱ የካቢኔ መዋቅር በፌደራል መንግሥት ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ካደረጉት አዲስ የካቢኔ ሹምሽርና ሽግሽግ ጋር መመሳሰል ይታይበታል፡፡

ነገር ግን በክልል ደረጃ ከኦሮሚያ ክልል በስተቀር የዋና አመራሮች ለውጥ አለመደረጉ ይታወቃል፡፡ የኦሮሚያ መንግሥት ዋናና ምክትል ርዕሰ መስተዳደሮችን በአዲስ ሲለውጥ፣ ቀደም ብሎም የክልሉን መንግሥት የሚያስተዳድረው ኦሕዴድም ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን እንዲሁ መለወጡ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...