– 95 ስማርት ሜትር ቆጣሪዎች በአዳማ ሙከራ ሊደረግባቸው ነው
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን የኃይል ፍጆታ መጠን ከመለካት ባለፈ የኃይል ሥርጭት ብክነትን፣ ብልሽትና ሌሎችም ሆን ተብለው በኃይል ማሠራጫዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚያጋልጡ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች በዕርዳታ ተረከበ፡፡
የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገሪቱ ከሚያከናውናቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መስመሮች ማሻሻያ ሥራ ጋር በተገናኘ በተለይ በአዳማ ከተማ ተገጥመው ሙከራ እንደሚደረግባቸው የሚጠበቁና ለቤት ውስጥ፣ ለንግድና ለኢንዱስትሪዎች መገልገያነት የሚወሉ 95 ዘመናዊ ሜትር ቆጣሪዎችን ከሁዋዌና ከቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኪዩፕመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ ከተባለው ኩባንያ ተበርክተውለታል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኢነርጂ ማኔጅመንት ኃላፊ አቶ ጋሻውበዛ አበራ ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት፣ ከሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች የተበረከቱት ዘመናዊ ቆጣሪዎች ከዚህ ቀደም ቤት ለቤት እየተዞረ ይደረግ የነበረውን የቆጣሪ ንባብ ሥራን ጨምሮ፣ ደንበኞች ለተገለገሉበት የኃይል መጠን ትክክለኛውን ሒሳብ እንዲከፍሉ፣ የተጠቀሙት ትክክለኛ የኃይል መጠን ምን ያህል እንደሆነ በተጨባጭ መረጃ አስደግፈው እንደሚሰጡ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና በአገልግሎት ሒሳብ አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ብክነቶችን ጨምሮ ሌሎችም ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኙ የሚታሰቡት ዘመናዊ ቆጣሪዎቹ፣ በሁለት ወራት ውስጥ ሙከራ ተደርጎባቸው ውጤታቸው እንደሚታይ አቶ ጋሻውበዛ አስረድተዋል፡፡
ሁዋዌ ኩባንያና ቻይና ኤሌክትሪክ ፓወር ኢኪዩፕመንት ኤንድ ቴክኖሎጂ ኩባንያ የለገሱት ቆጣሪ በናይጄሪያ ተሞክሮ የኃይል ማሠራጫ ብክነት ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 11 ከመቶ እንዲቀንስ ማስቻሉ ተነግሮለታል፡፡ በተመሳሳይ የኃይል ፍጆታን ለመለካት ከሚደረገው ቆጠራ አኳያም በአማካይ ከ53 በመቶ ያላነሰ ብክነት ይታይ እንደነበርና ይህም ወደ 9.2 ከመቶ እንዲቀንስ ማስቻሉ ተነግሮለታል፡፡
በኢትዮጵያ በጠቅላላው የሚታየው የኃይል ብክነት መጠን 20 በመቶ እንደሚገመት የገለጹት አቶ ጋሻውበዛ፣ በአሜሪካው ማኬንዚ ኩባንያ አማካይነት እየተካሄደ ያለው ጥናት የብክነት መጠኑ ምን ያህል እንደሚሆን በተጨባጭ ሊያረጋግጠው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሁኑ ወቅት 2.5 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት የገለጹት የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጎሳዬ መንግሥቴ፣ ይህ ቁጥር ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሰባት ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ይሁንና በኃይል ሥርጭት፣ በአቅርቦት መጓደልና በተደጋጋሚ መቆራረጥ ምክንያት ከፍተኛ ቅሬታ የሚቀርብበት በመሆኑም የደንበኞችን ዕርካታ ለማምጣት ዘመናዊ የቆጣሪ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ሌሎችም ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡
ከቻይና ኩባንያዎች በተጨማሪ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ እንዲሁም አገር በቀሉ ዲቨንተስ ኩባንያ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ቆጣሪዎችን ገበያ ላይ ለማዋል ሙከራ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡