Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

በዘጠና ዓመታቸው ላረፉት የኩባ አብዮታዊ መሪ ፊደል ካስትሮ መታሰቢያ፣ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በትግላችን ሐውልት ስር ሲከናወን፣ በኩባ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ከልጆቻቸው ጋር (ፎቶ በሔኖክ ያሬድ)

ትኩስ ፅሁፎች

    ሕይወት እንደ ታክሲ

መነሻ መድረሻ አበጅቶ

ርቀት ተመን ሰጥቶ

ቦታ አቅጣጫን ለክቶ

የጉዞ መስመሩን አጣርቶ

የተሳፋሪውን መድረሻ እየጠራ

እንደየ ጉዞው በየስፍራ

ከተሳፋሪው ላይ እንደየርቀቱ

በታሪፍ በዋጋ ተቀብሎ በጥቂቱ

መንገዱን ሾፌሩ ሒሳቡን ረዳቱ

ያደርሳሉ ካሰቡበት ቦታ

ከመድረሻው ከፌርማታ

ልክ እንደ ታክሲ የለም ተራ

ሾፌሩ አንተውነህ ሕይወት ምትመራ

ጠርቶ እሚወስድህ ካሰብክበት ስፍራ

አላማህ ነው አቅጣጫህን የሚመራ

ተስፋ ነው ረዳትህ ነዋይ እሚያፈራ

ስኬት ነው መድረሻህ ቦታ

በህልፈት ነው ጉዞው እሚገታ

የሕይወትህ ጅረት መቋጫ ፌርማታ፡፡

በታሪኩ ከበደ፣ ምክረ ሰይጣን፣ (2008)

**********************

ልጇን በማደንዘዣ ታስተኛ የነበረችው እናት ተከሰሰች

ሚቼላ ፓይክ የተባለች የ37 ዓመት እናት ከፍቅረኛዋ ጋር በመተባበር ሕፃን ልጇ ፖፒን የእንቅልፍ መድሃኒት፣ ሔሮይንና ሌሎችንም በመደባለቅ እየሰጠች ለስድስት ወራት ያህል ለማስተኛት በመሞከሯ፣ የአራት ዓመቷ ፖፒም በዚህ ምክንያት ሕይወቷ በማለፉ ክስ ተመሥርቶባት ፍርድ ቤት መቅረቧን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ ዘገባው እንደሚያመለክተው፣ እናትየው ይህን ታደርግ የነበረው ከፍቅረኛዋ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ በማሰብ ነበር፡፡ ሕፃኗ በወሰደቻቸው የመድሃኒትና የአደንዛዥ እፅ ድብልቆች በልብ ሕመም የሞተችው እ.ኤ.አ. 2013 ላይ ነው፡፡ የእናትየውን አፓርትመንት የፈተሸው ዶክተር አንድ ሺሕ የመድሃኒት እንክብሎችን ማግኘቱም ታውቋል፡፡

***********

ቤተሰቦች በራሳቸው የሚተማመኑ ልጆችን ለማፍራት ማድረግ ያለባቸውን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ጠቆሙ

በራስ መተማመን ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት፤ የሚያበረክቱት ስጦታ ነው፡፡ በልጅ አስተዳደግ ላይ 16 መጽሐፎችን የጻፉት የሥነ ልቦና ባለሙያው ካርል ፒክሀርት፣ በራስ መተማመን የሌላቸው ሕፃናት አዲስና፣ ፈታኝ ነገሮችን ብሞክር እወድቃለሁ፣ ሌሎችም ተስፋ ይቆርጡብኛል ብለው የሚፈሩ ናቸው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ በወደፊት ሕይወታቸው የተለያዩ ነገሮችን ሞክረው ስኬታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፡፡ ‹‹በራስ የመተማመን ጠላት መሳነፍና ፍርኃት ናቸው፡፡ ስለዚህም ልጆቻችሁ አዲስና ትንሽ የሚፈትናቸውን ነገር እንዲያደርጉ አበረታቷቸው›› ይላሉ፡፡

የሥነ ልቦና ባለሙያው ጠቃሚ ከሚሏቸው ነገሮች መካከል ልጆች አሸነፉ ተሸነፉም ጥረታቸውን ማድነቅ፣ ብቃታቸውን የሚያዳብሩበትን መንገድ ማበረታታት፣ ያስቸገራቸውን ነገር በራሳቸው እንዲፈቱ መተውና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

  ***********

የሰዎች የግል መረጃን መለጠፍ መቀነስ ፌስቡክን አሳስቧል

በፊት በፊት ሰዎች የግል መረጃቸውን ማለትም የግል ሕይወታቸውን የሚመለከቱና ምናልባትም በፌስቡክ አደባባይ መለጠፍ የሌለባቸውን መረጃዎች ይለጥፉ ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን ፌስቡክ ሰዎች እንደዚህ ያሉ መረጃዎችን ይበልጥ እንዲለጥፉ በሚያበረታታ መልኩ ገጹን ምቹ ቢያደርግም ሰዎች እነዚህን መረጃዎች መለጠፍ እየቀነሱ መሆኑ ፌስቡክን እንዳሳሰበ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ሰዎች ብዙ ጉዳዮችን በፌስቡክ ገጻቸው እየለጠፉ ያሉበት ጊዜ ቢሆንም፣ የሚለጠፉት ነገሮች ብዙዋቹ ስለሰዎች የግል ሕይወት ሳይሆን ስለ ዓለም ሁኔታ ናቸው፡፡ ይህ ምናልባትም ሰዎች ከመቼውም የበለጠ ግንኙነት ስላላቸው የግል መረጃቸው ለዚህ ሁሉ እንዲደርስ ካለመፈለግ ሊሆን ይችላል፡፡

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች