Wednesday, February 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከሕዝብ ፍላጎትና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ይጣጣሙ!

የአገሪቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተግባራዊ የሚደረጉት በአስፈጻሚው አካል ወይም መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ሕዝብን ሲያስተዳድር ከአገር ዘላቂ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጋር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከሕግ አውጭውና ከሕግ ተርጓሚው ጋር በመናበብ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ በአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ሕግ በማስከበር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በዲፕሎማሲ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ በመሬት አስተዳደርና ልማት፣ ወዘተ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሕዝቡን ፍላጎት ያገናዘቡና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር መጣጣም አለባቸው፡፡ ሕዝብ በአገሩ ደስተኛ የሚሆነውና የሥራ ሞራሉ የሚነሳሳው በዚህ መንገድ ነው፡፡

መንግሥት ከሕዝብ የተሰጠውን አደራ በብቃት ለመወጣት ሕዝብ የሚያምንባቸውና የሚተማመንባቸው ሹማምንት ሊኖሩት ይገባል፡፡ እነዚህ በትምህርታቸው፣ በሙያ ብቃታቸውና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው ሹማምንት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሕዝቡን ፍላጎት አውቀው ሥራቸውን በአግባቡ ሲወጡ ሁከትና ብጥብጥ ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡ ይልቁንም የሕዝብ ፍላጎት ሲከበር የሕግ የበላይነት ይረጋገጣል፡፡ ፍትሐዊ የሥልጣንና የሀብት ክፍፍል ይኖራል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች በሚገባ ይከበራሉ፡፡ ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ የሲቪክ ማኅበራት ያብባሉ፡፡ የዜጎች ተሳትፎ ይዳብራል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሠረት የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተገነባ ለሁሉም ወገን የሚበጅ የፖለቲካ ምኅዳር ይፈጠራል፡፡ ድንጋይ ወርዋሪ ሳይሆን ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ለማፍራት ይጠቅማል፡፡

አገራችንን ጨምሮ በበርካታ አገሮች በሕዝብና በመንግሥት መካከል መቃቃር የሚፈጠረው፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ ሲነጥፍና የመንግሥት የአገልጋይነት ሚና ሲኮላሽ ነው፡፡ መንግሥት የልማት ዕቅዶችን ዘርግቶ የፈለገውን ያህል ቢማስን የሕዝብ ተሳትፎ ካልታከለበት ፋይዳ አይኖረውም፡፡ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ አካል መሆኑን ማረጋገጫው የሥልጣኑ ባለቤት ለሆነው ሕዝብ በሚኖረው ታዛዥነት መጠን ነው፡፡ የመንግሥት የተለያዩ ተቋማት በየዘርፎቻቸው ከግብር ከፋዩ ሕዝብ ጋርም ሆነ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸው ግንኙነት በመተማመን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይህ መተማመን የሚፈጠረው ደግሞ የመንግሥት ተቋማቱ በአገልጋይነት መንፈስ ሥራቸውን ሲያከናውኑና ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲኖርባቸው ነው፡፡ ዘመኑ ከደረሰበት የዕድገት ግስጋሴ ጋር በመጣጣም ለተገልጋዩ ሕዝብ ከበሬታ ሰጥተው ማገልገል ሲችሉ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በልማዳዊ አሠራር ተተብትበው የትም መድረስ አይችሉም፡፡ ለአገሪቱም አይጠቅሙም፡፡

ከዘመኑ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር አመራር መስጠት የሚችሉ ብቁ ሹማምንት በየቦታው መመደብ አለባቸው፡፡ እነዚህ ሹማምንት የግድ ከገዥው ፓርቲ ብቻ መምጣት የለባቸውም፡፡ አገራቸውን በከፍተኛ ፍቅር ለማገልገል የሚፈልጉ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሠለጠኑና ልምድ ያካበቱ ዜጎች በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በብዛት አሉ፡፡ ይህ ዘመን በቴክኖሎጂ የተመነደገና በዳበሩ አስተሳሰቦች የሚመራ እንደመሆኑ መጠን፣ ከጊዜው ጋር እኩል የሚራመድ አሠራር ማስፈን ተገቢ ነው፡፡ ሥልጣን ሕዝብን ማገልገያ እንጂ በሕዝብ ላይ መገልገያ እንዳልሆነ በአንክሮ መጤን አለበት፡፡ እንኳን  ተሿሚ ግለሰቦች ይቅሩና ፓርቲዎች በሕዝብ ድምፅ ብቻ ነው ሥልጣን መያዝ ያለባቸው፡፡ እኔ ብቻ ነኝ የምችለው ከማለት ይልቅ፣ ለአገር በተሻለ የሚጠቅሙ አሉ ወይ? ብሎ ማፈላለግ ለዘላቂው የአገርና የሕዝብ ጥቅም ጥሩ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ያስከብራልም፡፡

የመልካም አስተዳደር ዕጦት አለ ሲባል፣ ፍትሕ ችግር ውስጥ ገብቷል ሲባል፣ ሙስና አገርን እንደ ሰደድ እሳት እየበላ ነው ሲባል፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ አቂሟል ሲባልና የመሳሰሉት ችግሮች በስፋት ሲስተጋቡ ግራና ቀኙን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ችግሮች ክትራቸውን ጥሰው ለአገር ህልውና ሥጋት ሲደቅኑ ዘለቄታዊ መፍትሔያቸው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የተጫረውን እሳት በጊዜያዊ ዕርምጃ አጥፍቶ መቀመጥ ሳይሆን፣ ከሕዝብ መሠረታዊ ጥቅምና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለግ ብልህነት ነው፡፡ በመንግሥት ውሳኔ አሰጣጥ ወቅት ግራና ቀኙን በሚገባ በመመርመር ከአገርና ከሕዝብ ዘላቂ ጥቅም አንፃር ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ ነው፡፡ በግዴለሽነትና በማናለብኝነት የሚወሰዱ ግብታዊ ዕርምጃዎች አገርን ለጥፋት፣ ሕዝብን ደግሞ ለእንግልት ሲዳርጉ በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በፍፁም መታረም አለበት፡፡

የአገር ሰላምና ደኅንነት በሕዝብ እርካታ ላይ ይወሰናል፡፡ ጥቂቶች እንደፈለጉ እንሁን ሲሉ ብዙኃኑ ለምን ብለው ይነሳሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥና የሕዝብ ፍላጎት ሲከበር ግን ብዙኃን ይደሰታሉ፡፡ ጥቂቶቹም ቢሆኑ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በተለይ በአገር አጠቃላይ ጉዳይ የሕዝብ ፍላጎት ገዥ መሆን አለበት፡፡ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር የተቃናና የሕዝብና የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅም የሚያስከብር ውሳኔ ቅራኔን ለማስወገድና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ይጠቅማል፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጉዳዮች  ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሕዝቡን ፍላጎት በሚገባ መረዳት አለበት፡፡ የሕዝብ ፍላጎት ሲባል ከጊዜያዊ እርካታ ጋር የተያያዘ ስሜት ሳይሆን፣ ከአገር ዘለቄታዊ ጥቅም ጋር የተቆራኘ ውሳኔ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከሕዝብ ፍላጎትና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ሊጣጣሙ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ላደረሰው ኪሳራ ክስ ተመሠረተበት

ኩባንያው በግማሽ ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል ኢትዮ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አንድ)

በጀማል ሙሀመድ ኃይሌ (ዶ/ር) "ሆድ ባዶ ይጠላል..." "ከሆድ የገባ ያገለግላል…” ከጥቂት ዓመታት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ሰላም እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲገታ ተደርጎ ጠባሳው ሳይሽር፣ አገርን ሌላ አስከፊ ቀውስ ውስጥ የሚከት የሃይማኖት ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ...

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...