Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየጋምቢያውያንን ሥጋት ያረገቡት ተሰናባች ፕሬዚዳንት

የጋምቢያውያንን ሥጋት ያረገቡት ተሰናባች ፕሬዚዳንት

ቀን:

የዛሬ አምስት ዓመት ነው፡፡ በወቅቱ ሥልጣን ከያዙ 17 ዓመታትን ያስቆጠሩት የጋምቢያው ፕሬዚዳንት ያህያ ጃሜ ጋምቢያን ለአንድ ቢሊዮን ዓመታት እንደሚገዙ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ተናገሩ፡፡ ይህን ንግግራቸውን የሰሙ ጋምቢያውያን በተለይም የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች ጃሜ በሰላም ሥልጣን ላይለቁ እንደሚችሉ ቢገምቱም፣ በምርጫ ከመሳተፍ አልተቆጠቡም፡፡ ባለፈው ሳምንት ማጠናቀቂያ በተካሄደው ምርጫ የተሳተፈው የሰባት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት መሪ አዳማ ባሮው በምርጫው አሸናፊ ሆኑ፡፡

ለአንድ ቢሊዮን ዓመት በሥልጣን እንደሚቆዩ ተናግረው የነበሩት ያህያ ጃሜ፣ በምርጫው ከተሸነፉ በኃላ ያሳዩት አቋም ከሕዝቡ ሥጋት፣ ከፖለቲካ ተንታኞች ትችት  የተለየ ነበር፡፡

በምርጫው ውጤት ሳቢያ በአገሪቱ ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል ተብሎ የተሠጋ ቢሆንም፣ ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ለዚህ ዕድል አልሰጡም፡፡ መንግሥታቸው በምርጫው ዕለት መራጩ ሕዝብ በስልክም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ተጠቅሞ ለብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን እንዳያስተላልፍ በመላ አገሪቱ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችም ሆኑ የኢንተርኔት አገልግሎቶች እንዲቋረጡ አድርጎ ነበር፡፡ ‹‹የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነቶችን ያቋረጥኩት በአገሪቱ በምርጫ ሰበብ ብጥብጥ እንዳይነሳ ለማረጋገጥ ነው፤›› ሲል የጋምቢያ መንግሥት አስታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ላሸነፏቸው ባሮው በሞባይል ስልክ በመደወል ደስታቸውን መግለጻቸውንና በውጤቱ ላይም ተቃውሞ እንደሌላቸው መናገራቸውም ተገልጿል፡፡

ቢቢሲ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረትን ጠቅሶ እንዳሰፈረው ለ22 ዓመታት አገሪቱን የመሩት ጃሜ በባለሀብቱ ባሮው ተሸንፈዋል፡፡ የአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽንም ባሮው 45 በመቶ ድምፅ ሲያገኙ፣ ጃሜ ደግሞ 36 በመቶ አግኝተዋል ሲል ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ አሳውቋል፡፡

‹‹ፈጣሪ የእኔ ጊዜ እንዳበቃ ነግሮኛል፡፡ ሥልጣኔን ለጋምቢያውያንና ለአንተ ክብር ስል በደስታ አስረክባለሁ፤›› በማለት በስልክ ለባሮው እንደነገሯቸው ተገልጿል፡፡

በ22 ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው ተቃዋሚዎቻቸውን በማሰቃየትና ዝም በማሰኘት የሚታወቁት ጃሜ በምርጫ መሸነፋቸው እንደተሰማ አንዳንድ ዜጎች የእሳቸው ምሥል ያለበትን ፖስተር መቅደዳቸውን፣ የመንግሥታቸው ወታደሮችም ምንም እንዳላሉ፣ አንዳንዶችም መኪና ላይ ሆነው ‹‹ነፃነት! ነፃነት!›› ሲሉ እንደነበሩ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡

እኚህ መሪ በማንኛውም ሥፍራ ሲዘዋወሩ በማይለያቸው መቁጠሪያ (በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ፀሎት በሚደረግበት ጊዜ በእጅ የሚያዝ፣ ፀሎት ባይኖርም እጅ ወይም አንገት ላይ የሚጠለቅ) እና በትር የሚታወቁ ሲሆን፣ ለየት ያሉና የሚፈልጉትን ለማግኘት ማንኛውንም ዕርምጃ የሚወስዱ ናቸው፡፡

የተወለዱት እ.ኤ.አ በ1965 ሲሆን ሥልጣን የያዙት ደግሞ በ1994 ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1984 የጋምቢያን መከላከያ ኃይል በመቀላቀል በ1989 ምክትል የመቶ አለቃ ማዕረግ ያገኙ ሲሆን፣ በ1992 የወታደራዊ ፖሊስ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡ በጋምቢያ ጎረቤት በሴኔጋል እንዲሁም በአላባማ ከፍተኛ ወታደራዊ ሥልጠና ወስደዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 መንግሥት በሙስና ተዘፍቋል በማለት ከጋምቢያ ወጣት የመከላከያ አባላት ጋር በመሆን፣ የወቅቱ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ዳውድ ጃዋራ በመፈንቅለ መንግሥት አስወግደዋል፡፡

 መፈንቅለ መንግሥቱ ያለምንም ደም መፋሰስ የተከናወነ ሲሆን፣ ከፕሬዚዳንቱ ወገንም እዚህ ግባ የሚባል ምላሽ አልገጠማቸውም ነበር፡፡ ራሱን ‹‹አርምድ ፎርስስ ፕሮቪዥናል ሩሊንግ ካውንስል (ኤኤፍፒአርሲ) እያለ የሚጠራው የመፈንቅለ መንግሥት አድራጊ ቡድኑ መሪም ነበሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ጃሜ ‹‹አሊያንስ ፎር ፓትሪዮቲክ ሪኦረንቴሽን ኤንድ ኮንስትራክሽን›› የተባለ ፓርቲ በመመሥረት እ.ኤ.አ በ1996 ምርጫ አካሂደዋል፡፡ በወቅቱ የውጭ ምርጫ ታዛቢዎች ምርጫው ነፃና ፍትሐዊ አይደለም ቢሉም፣ እ.ኤ.አ በ2001 በተደረገው ምርጫ መንግሥት በመራጮች ላይ ጣልቃ ከመግባቱ በቀር በተሻለ ሁኔታ ነፃና ፍትሐዊ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ባደረጉባቸው ላይ የዕድሜ ልክ እስራት አስፈርደዋል፡፡ በአገር ክህደት ወንጀልም ሞት የተፈረደባቸው አሉ፡፡

 ራሳቸውን ለእስልምና እምነት ማስገዛታቸውንና ብዙ ተዓምራት እንደሚያደርጉ፣ እ.ኤ.አ በ2007 ኤድስን ከዕፅ በሚቀመም በድኃኒት መፈወስ እችላለሁ በማለት የዘርፉ ተመራማሪዎችን እንዳነጋገሩና አስከትለውም የሴቶችን የመውለድ ችግር እንደሚፈቱ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ግብረ ሰዶማዊነትን አጥብቀው የሚያወግዙ ሲሆኑ፣ እ.ኤ.አ በ2014 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግርም ግብረ ሰዶማዊነት ትውልድን የሚያጠፋ ድርጊት መሆኑን በመጥቀስ፣ ምዕራባውያን ግብረ ሰዶማዊነት እንደ መብት እንዲከበር የሚያደርጉትን ጥረት አውግዘዋል፡፡ በአገራቸው ግብረ ሰዶማዊ ከተገኘም አንገቱ/ቷ እንደሚቀላ አስጠንቅቀው ነበር፡፡

የፕሬስና የሲቪል ማኅበረሰቡን የሐሳብ ነፃነት በመገደብና ነፃነትን በማፈን ከሚወቀሱት ጃሜ ሥልጣን የሚረከቡት የ51 ዓመቱ አዳማ ባሮው፣ ንብረቶችን በማስተዳደርና ሪል ስቴት በማልማት የሚታወቁ ባለሀብት ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመናቸው በመንግሥት ቢሮ ያልሠሩ ሲሆን፣ በእንግሊዝ በትምህርት ላይ በነበሩበት በ2000ዎቹ መጀመሪያ፣ በለንደን በሚገኘው አርጎስ ካታሎግ ስቶር የደኅንነት ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል፡፡

ጋምቢያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ በወጣችበት እ.ኤ.አ በ1956 የተወለዱ ሲሆን፣ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ነፃና ገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓት፣ የመገናኛ ብዙሃንና ሲቪል ማኅበረሰብ እንዲኖርና የሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

በጃሜ የሥልጣን ዘመን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ጋምቢያውያን ለሥራ ፍለጋ ተሰደዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም በሕይወት ዘመናቸው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አይተውና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሠርተው ለማያውቁት ተመራጩ ፕሬዚዳንት የቤት ሥራ ነው፡፡ ቢቢሲ እንደሚለው የአገሪቱን ዜጎች ከስደት ለመታደግ የተቀናጀ የሥራ ፈጠራ፣ እንዲሁም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ሥርዓት መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ባሮው በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከብሔርና ከሃይማኖት ጋር የተደበላለቀ መሆኑን በመናገር፣ ችግሩን የሚፈታ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የፍትሕ ሥርዓት እንደሚዘረጉ አስታውቀው ነበር፡፡ በጋምቢያ ላለፉት 22 ዓመታት የተንሰራፋውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሃይማኖትና የብሔር ጽንፈኝነትና በአድልኦ የተሸበበ የፍትሕ ሥርዓት አቃንተው የጋምቢያውያንን በነፃነት የመኖር ፍላጎት ያረኩ ይሆን? የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...