Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየስምጥ ሸለቆዋ ከተማ

የስምጥ ሸለቆዋ ከተማ

ቀን:

ከአዲስ አበባ 97 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ አመሠራረቷም ከኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከተማዋ 100ኛ ዓመቷን አክብራለች፡፡ በቀደምትነት ኦሮሞዎች የመሠረቷት ሲሆን በኋላ ላይ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ሆናለች፡፡ ይህም የሥራ፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የመቻቻልና የዕድገት ከተማ አስብሏታል፡፡

የከተማዋም መሠረተ ልማት በመንገድ፣ በንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና በትምህርት ቤቶች አሸፋፈን ሲታይ ከሞላ ጎደል መልካም ነው፡፡ በተለይም በትምህርት ዘርፍ ከአፀደ ሕፃናት (ቅድመ መደበኛ ትምህርት) ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም በጤና ዘርፍ የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ከጤና ጣቢያ እስከ ሪፈራል ሆስፒታል አላት፡፡

በኢንዱስትሪውም፣ የውጭ ባለሀብቶችንም ያሳተፉ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት ናት፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ማፍራት የተቻለባት ከተማ ስትሆን፣ በተለይ ለአዲስ አበባ ቅርብና የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መሥመር መተላለፊያ መሆኗ፣ አንድ የንግድ ማዕከል ሆና እንድታገለግል አድርጓታል፡፡

- Advertisement -

ለኦሮሚያ ክልልም ሆነ በአጠቃላይ ለአገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የኮንፍረንስ ማዕከል ሆና እያገለገለችም ትገኛለች፡፡ ይሁን እንጂ ገልማ አባገዳ አዳራሽን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የሶደሬ ሪዞርት፣ ባኮ የእንፋሎት ጠበል የመሳሰሉ መስህብ ቢኖራትም፣ በቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ተሠርቷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ የሚጎበኙ ቦታዎችን ከማዘጋጀትና ከአደረጃጀት አኳያ መከናወን የሚገባቸው ሰፊ ሥራዎችም አልተነኩም፡፡

በታላቁ የስምጥ ሸለቆ ውስጥ የምትገኘው ይህች ከተማ ሞቃታማ የአየር ፀባይ ቢኖራትም፣ ለነዋሪዎቿ ምቹና ውብ፣ ዋል አደር ብሎ ለሚመለስ ወይም በአጠቃላይ ለጎብኚዎቿ ጥሩና ተስማሚ ናት፡፡ ብዙ የተዘመረለትና እየዘመነች ያለችው ይህች ከተማ አዳማ ትባላለች፡፡ በነዋሪዎቿም ዘንድ የስምጥ ሸለቆዋ እንቁ ከተማ የሚል ቅጽል ሥም አትርፋለች፡፡

የተቆረቆረችበት ስፍራ፣ ‹‹አሮጌ አዳማ›› ወይም ‹‹መልካ አዳማ ቀበሌ›› ይባላል፡፡ ቦታው ከ100 ዓመት በፊት የኢትዮ ጂቡቲ አሮጌው የባቡር ሐዲድ የተዘረጋበትና ዙሪያውም በአፋን ኦሮሞ ‹‹አዳሜ›› በአማርኛ ደግሞ ‹‹ቁልቋል›› የሚባል ተክል የበዛበት ነበር፡፡ ከተማዋም ስያሜዋን ያገኘችው ከዚሁ ቁልቋል ወይም አዳሜ እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

በአሮጌዋ አዳማ ውስጥ በርካታ አባወራዎች ይገኛሉ፡፡ ሁሉም የሚተዳደሩት በግብርና ነው፡፡ ምንም እንኳን አንድ ምዕተ ዓመት የሞላት ብትሆንም፣ እስካሁን ድረስ ክሊኒክን ጨምሮ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት የላትም፡፡ ውሃ ለማግኘት ቢያንስ እስከ ስድስት ኪሎ ሜትር ድረስ በእግር መጓዝ ግድ ይላል፡፡ ከነዋሪቿ መካከል ጥቂቶቹ የሶላር ብዙዎቹ ደግሞ የኩራዝ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

የአዳማ ከተማ ከተቆረቆረችበት ከፍታ ቦታ ላይ አሁን ወደምትገኝበት ዝቅተኛ ቦታ ላይ እንዴት ልትስፋፋ ቻለች የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ አቶ አለማየሁ ቱሉ የአዳማ ከተማ 100ኛ ዓመት አከባበር ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ይህንኑ አስመልክተው እንደገለጹት፣ የዛሬ 100 ዓመት ከፍታ ቦታ ላይ ከሚገኘው አሮጌው አዳማ ውስጥ በተዘረጋው ሃዲድ በመጓዝ ላይ የነበረ የባቡር ፉርጎ ተበጥሶ ቁልቁለቱን ይወርድና ለገሃር ይቆማል፡፡ ከዚህ በኋላ ለምን ከተማዋን በዚሁ ዝቅተኛ ሥፍራ ላይ አናደርጋትም ተብሎ አሁን በምትገኝበት ቦታ ልትስፋፋ ቻለች፡፡

በአሮጌዋ አዳማ ወይም በመልካ አዳማ ቀበሌ ነባሩ ሃዲድ ከተዘረጋ ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ቤቶች አሁንም እንዳሉ ሲሆን፣ ይህም የቱሪስት መስህብ ሆኖ ተጠብቆ እንዲቆይ ለማድረግም እየተሠራ መሆኑን አቶ አለማየሁ ይናገራሉ፡፡

የከተማዋን 100ኛ ዓመት አስመልክቶ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ እስከ ዘንድሮው ዓመት የመጀመርያ ወር ድረስ ከተካሄዱት ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞች እስከ አምስት ሚሊዮን ብር መገኘቱን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ሌላ በአንድ ጊዜ 80 ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባትና የከተማ መናፈሻ (ሲቲ ፓርክ) ለማቋቋም ታቅዷል፡፡ ለዕቅዱም እውን መሆን የስታድየሙና የመናፈሻ ዲዛይኖች ተሰርቷል፡፡ ለስታድየሙ ግንባታ የሚውል 33 ሄክታር መሬትም ተዘጋጅቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...