Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልዝክረ ፊደል ካስትሮ በ‹‹ትግላችን ሐውልት››

ዝክረ ፊደል ካስትሮ በ‹‹ትግላችን ሐውልት››

ቀን:

ኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ አራተኛውን የአብዮት በዓሏን መስከረም 2 ቀን 1971 ዓ.ም. ለማክበር የመዲናይቱ ነዋሪዎች ከመሪዋ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ አብዮት አደባባይ ከትመዋል፡፡ ርእሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የዕለቱን የክብር እንግዳቸው፣ ቁርጠኛ ወዳጃቸው የወቅቱ የኩባ ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሩዝን ሊቀበሉ በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና በታላቅ አጀብ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ደርሰው ይጠብቁ ነበር፡፡ ፊደል ካስትሮን የያዘው አደሮፕላን ግን ድምፁ አልተሰማም፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመዘግየታቸው ሊቀመንበሩ ወደ አብዮት አደባባይ ተመለሱ በአደባባዩም የሦስቱን ዓመታት ‹‹ትግልና ድል›› የሚዘክር መሰናዶ እያዩ አዲስ በታነፀው ሰገነት ላይ ሆነው ይከታተሉ ጀመር፡፡

አብዮታዊ ዲስኩራቸውን እያሰሙ ባሉበት ሰገነት ላይ አንዱ ተጠግቷቸው ፊደል ካስትሮ አዲስ አበባ መድረሳቸውን ነገራቸውና ንግግራቸው አቋርጠው ሊቀበሏቸው ቦሌ ዘለቁ፡፡ አቀባበልም ተደረገላቸው፡፡ ከቦሌ እስከ አብዮት አደባባይ ግራና ቀኝ የተሰለፉት በተለይ የከፍተኛ 18 እና ከፍተኛ 19 ነዋሪዎች አጀቡን አደመቁት፡፡ ‹‹ቪቫ መንግሥቱ ቪቫ ካስትሮ›› እየተባሉ በቅብብሎሽ ከአደባባዩ ደረሱ፡፡ ዘውዳዊ ምልክቱ በመዶሻና ማጭድ በተተካው በቀይና ግልጽ ማርቸዲስ አውቶሞቢል ቢሆንም አደባባዩን ዞሩ፡፡ ይህ ከሆነ ድፍን 38 ዓመት ሆነው፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያ ቁርጠኛ ወዳጅ፣ ከ40 ዓመት በፊት ወረራ የፈጸመችባትን ሶማሊያ ለመግታት ከ15 ሺሕ በላይ ወታደሮቿን አሰልፋ ከደም ጠብታ እስከ መስዋዕትነት የተሰለፈችው ኩባ መሪዋ ፊደል ካስትሮ ከ40 ዓመት በፊትም በ‹‹ቀውጢው ዘመን›› አዲስ አበባ ጎራ ብለው ነበር፡፡ መጋቢት 5 ቀን 1969 ዓ.ም. በወቅቱ አጠራር በኢምፔሪያሊስቶችና በአድኅሮት ያረብ አገሮች አጋፋሪነት ምሥራቅ ኢትዮጵያን ወርራ የያዘችውን የዚያድ ባሬ ሶማሊያን ሃይ ለማለት መትጋታቸው አልቀረም፡፡ የሁለቱ አገሮች ጦርነት የቀዝቃዛው ጦርነት አካል የሶቭየት ኅብረትና የአሜሪካ፣ የሶሻሊስቱና የካፒታሊስቱ ዓለም ጎራ ዐውደ ውጊያ ሆኖ የታየበት ነበር፡፡

እስከ አፍንጫዋ ታጥቃ የነበረችው የምዕራቡና የዓረቡ ዓለም ድጋፍ የነበራት ሶማሊያ፣ ከአሜሪካ ጦር መሣሪያ በገንዘቧ ገዝታ ‹‹ዓይንሽን ላፈር›› የተባለችውን ኢትዮጵያን እስከ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ ድንበር ጥሳ ወሰን አፍርሳ ሕዝብ አፈናቀለች፡፡

የፊደል ካስትሮና የኢትዮጵያ ሌላኛዋ ወዳጅ የደቡብ የመን (የመን ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ) ሶሻሊስት ፓርቲ መሪው አብዱልፈታህ እስማኤል ጭምር የተደረገው የማደራደር ጥረት አልተሳካም፡፡

ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‹‹ትግላችን›› ባሉት የመጀመሪያው መጽሐፋቸው እንደጻፉት፣ የፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮና የፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ እስማኤል የኤደን ሽምግልና ሳይሳካ ቀረ፡፡

‹‹ጓድ ፊደል ሲቀበሉን ጦርነቱን ገጥመን፣ የተሸነፍን ይመስል በማዘንና በመጨነቅ ሊያፅናኑን ሞከሩ፡፡ ሶማሊያዎች ውጊያውን ሊያሸንፉ ይችላሉ፡፡ በጦርነቱ አሸናፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው በማለት እኛ መልሰን አፅናናናቸው፡፡››

ሊቀመንበር መንግሥቱ የካስትሮ ምላሽንም በመጽሐፋቸው አስፍረውታል፡፡ ‹‹ልክ ናችሁ በጦርነት አሸናፊው አብዮት ነው፡፡ እኛ የጠላነው፣ ለአጭር ጊዜም ቢሆን መሸነፋችንን በመገመት ነው፡፡››

ጦርነቱ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ጎን በአጋርነት የተሰለፉት የኩባና የደቡብ የመን ጭምር መሆኑ ነው፡፡ አለፍ ሲልም የምዕራቡና የምሥራቁ ዓለም የአንድ ክንፍ ፍልሚያ፡፡

‹‹ተነሥ ታጠቅ ዝመት አብዮታዊት እናት አገርህ ተደፍራለች›› በሚለው ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ዘመቻ፣ የኩባም የየመንም ወታደሮች ታከሉበት፡፡ በፍልሚያው ጎራ በምሥራቅና በደቡባዊ ምሥራቅ የዘመቱት እርመኛ ወታደሮች ለአገር ነፃነት ተሰዉ፡፡

የነዚያ ጀግና ወታደሮች ልጆችም የፊደል ካስትሮዋ ኩባ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ዕድል ሰጠች፡፡ በወሳኙ የጦር ግንባር ‹‹ቆሬ›› እና በ‹‹መንግሥቱ ኃይለ ማርያም›› ስም ትምህርት ቤቶችንም መሠረተች፡፡

‹‹ፋኖ ተሰማራ ፋኖ ተሰማራ

እንደ ሆቼሚኒ እንደ ቼጉቬራ›› እያለ ያቀነቀነው ያ ትውልድ ፊደል ካስትሮም ታካዩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት በተቀጣጠለበት የሶሻሊስት ርዕዮት የሚያንፀባርቁ መጻሕፍት በየፈርጁ በተተረጐመበት ጊዜ አንዱ የኩባ አብዮት ታሪክ ነበር፡፡ የአዲስ አበባን ገበያንም ይዞት ነበር፡፡

አራተኛው አብዮት በዓል በሶማሊያ ላይ ከተገኘው ድል በኋላ የተከበረ በመሆኑ ልዩ ስፍራ ነበረው፡፡ ከ1968 እስከ 1970፣ እንዲሁም ከ1972 እስከ 1983 የአብዮት በዓል መስከረም 2 ብቻ ነበር፡፡ ፊደል ካስትሮ የተገኙበት የ1971 ዓ.ም. የአብዮት በዓል ግን በመስከረም 2 ብቻ አልተገደበም፡፡ በማግስቱ መስከረም 3 ቀን በወታደራዊ ሰልፍ መከበሩ ይታወሳል፡፡ ‹‹ትግል ድል›› የተሰኘው ታላቅ ዐውደ ርዕይም በሽሮ ሜዳ አሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት የአሁኑ የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻ ተቋም ቅጥር ግቢ ሲታይ ፊደል አካሉ ነበሩ፡፡

ኩባ ለኢትዮጵያ ከ40 ዓመት ወዲህ የደረሰች እንግዳ አልነበረችም፡፡ በታሪክ እንደሚወሳው ከ80 ዓመት በፊት ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወር ኩባዊው አልሲንዳሮ ለነፃነት ተዋግቷል፡፡ ‹‹ቀይ አንበሳ›› የተሰኘ መጽሐፉንም የዘመነ ፋሺስት ወረራን አስመልክቶ መጻፉና ወደ አማርኛም መተርጐሙ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባው መታሰቢያ

እሑድ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላይ ፖስታ ቤት ፊት ለፊት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው ‹‹ትግላችን›› ሐውልት አደባባይ የኢትዮጵያና የኩባ ሰንደቅ ዓላማዎች እየተውለበለቡ ይታያሉ፡፡ በእጅ የሚያዙትም ጭምር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ‹‹የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ›› የሚል ስያሜ በታከለበት ትግላችን ሐውልት ዋናው መግቢያ ላይ በስፓኒሽ፣ በእንግሊዝኛና በአማርኛ መግለጫ ‹‹ፊደል ለዘላለም ይኖራል!!›› የሚል በግርጌ የሰፈረበት የፊደል ካስትሮ ምስል ይታያል፡፡

‹‹ለኢትዮጵያ አንድነት ለሕዝቡና አብዮቱ ሲታገሉ ጥለው ለወደቁ የሕዝብ ልጆች የቆመው መታሰቢያ›› ላይ የኩባን አብዮት ከጫካ እስከ ከተማ ከነቼጉዌራ ጋር መርተው ለድል ያበቁት ፊደል የትግል ዘመናቸው ፎቶ ተሰቅሎበታል፡፡ ‹‹ለእኛነታችን መሠረት ነህ! እናመሰግንሃለን›› የሚል ጽሑፍና የፊደል ፎቶ ያለበት ጥቁር ካኔቴራ ያጠለቁ በኩባ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ከነልጆቻቸው ፎቶ እየተነሱ ነበር፡፡

‹‹ታማኝ›› የሚል ትርጉም ያለውን ‹‹ፊደል›› ከፊደል ካስትሮ ወስደው ለልጆቻቸው መጠርያ የሰየሙም አሉ፡፡

በተጣለው ዳስ ውስጥ የኩባ ሙዚቃ ሞገድ አሳብሮ ይደመጣል፡፡ ተወዳጁ የዚያን ዘመን አዲስ አበቤዎች የማይረሷት ‹‹ሁዋንታ ላሜራ›› የብዙዎችን ስሜት ቀስቅሳለች፡፡ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ‹‹እነሆ ጀግና›› ብሎ ባሳተመው የአገር ቤትና የውጭ አገር ጀግኖች መካከል የተወሳው ያልተረሳው ፊደል ካስትሮ ነበር፡፡

‹‹ ‘ሁዋንታ ላሜራ’ የምትባለውን መዝሙራቸውን የሰማ ሊገምት እንደሚችለው የኩባ ሕዝብ ሙዚቃና ዳንስ በጣሙን ይወዳል፡፡ በጣሙን ይችልበታል፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ ያ ሕዝብ በዚያ ቀን [በአብዮቱ የድል ቀን] መንገዶቹን ሞልቷቸው እየዘፈነ፣ እየደነሰ፣ እየተሳሳመ፡፡ አንድ ሕዝብ አንድ ባህል አንድ ቀን፡፡ ከእንግዲህ ደሞ አንድ ፓርቲ፣ አንድ መሪ ፊደል ካስትሮ፡፡››

በመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ኩባውያን፣ ዲፕሎማቶች በሐዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ሲፈርሙ፣ ከዋናው ሐውልት (ትግላችን) በተጨማሪ በግራና በቀኝ (በደቡብና በሰሜን) የተተከሉ ለኢትዮጵያ ደማቸውን ካፈሰሱ ኩባውያን ወታደሮች መካከል የ162ቱ ወታደሮች ፎቶና ስም ያለበትን ቅጥር ይጎበኙ ነበር፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ የቀድሞው ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የኢትዮጵያና ኩባ ወዳጅነት በደም የተሳሰረና ለዘላለም እንደሚቆይ ገልጸዋል፡፡

‹‹ፊደል ካስትሮ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ወቅት በነበረችበት ጊዜ ከእኛ ጋር በመሆናቸው አገራችን መቼም አትረሳቸውም፤›› ሲሉም በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡

በደም የተሳሰረው የኩባና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ለዘላለም ይኖራል ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሁዋን ማኑኤል ሮድርጌዝ ባስካስም፣ ፊደል ለኩባውያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ፍትሕ የላቀ አስተዋጽኦ ያደረጉ ነበሩ ብለዋል፡፡

ዓርብ ነሐሴ 7 ቀን 1918 ዓ.ም. ተወልደው፣ ዓርብ ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በዘጠና ዓመታቸው ያረፉት አብዮታዊው መሪ ፊደል ካስትሮ ሥርዓተ ቀብር፣ በዕለተ ሰንበት የተፈጸመው የኩባ አብዮት በተወለደባት ሳንቲያጎ ዴኩባ ከተማ ነው፡፡ ከመዲናይቱ ሃቫና ከአራት ቀናት ጉዞ በኋላ ለሥርዓተ ቀብር የበቃው አስክሬኑ ተቃጥሎ በአመድ መልክ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች መሪዎች በተገኙበት፣ ለ49 ዓመታት ኩባን የመሩት ፊደል ካስትሮ ግብአተ አመድ ሲፈጸም ለቀስተኞቹ ‹‹ፊደል ለዘለዓለም ይኑር!›› ‹‹እኔም ፊደል ነኝ!›› ሲሉ መሰማታቸው የዜና አውታሮች ዘግበዋል፡፡

ተቀጽላ – የሳርትር ምስክርነት

ሳርትር ከምዕራባዊው ሥልጣኔ ታላቅ ፊላስፋዎች አንዱ በልቦለዶቹ፣ ባጫጭር ልብ ወለዶቹ፣ በትያትሮቹ ብቃት ደሞ ከፈረንሳይ ሥነ ጽሑፍ ቁንጮዎች አንዱ ነው፡፡ የኖቤል ሽልማትን እምቢ አልቀበለውም፤ ኢምፔሪያሊዝም እኔን አይሸልመኝም ያለ ሰው ነው፡፡ በሂትለር ወረራ ዘመን ህቡዕ (ድብቅ) አርበኛ ነበረ፡፡ ሰውየው ይሁዲ ነው፡፡ አጭር ነው፣ ጠንጋራ ነው፣ ወፍራም መነፅር ያረጋል፡፡ ሴቶች በጣም ይወዱታል፡፡ ከሳርትር ምስክርነት በትንሹ እነሆ በማለት፡፡ ‹‹እነሆ ጀግና!›› ብሎ በጻፈው መጽሐፉ ያወሳው ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ነበር፡፡

‹‹እነፊደል ካስትሮ የሥራ ሰዓት የዕረፍት ሰዓት ብለው አይለዩም፡፡ ቢሮዋቸው ታጣፊ አልጋ አለ፡፡ እንቅልፍ ሲመጣ እሱ ላይ ይተኛሉ፡፡ ሲነቁ ወደ ሥራ ነው፡፡ ካስትሮን ሕዝቡ ይወደዋል፡፡ ሕዝቡና መሪው እኩል ሲዋደዱ ብዙ ጊዜ አያጋጥምም፡፡

‹‹አንድ ቀን ካስትሮ እነ ሳርትርን ሲያስጎበኝ የነሱ መኪናዎች ተከትለውት የሱ መኪና ፊት ፊት እየሄደ ወደ አንድ ጫካ ገቡ መንገዱን ተከትለው፡፡ ብዙም ሳይሄዱ አንድ በጣም ግዙፍ የሆነ ጥቁር ሰውዬ ድንገት ከጫካው ብቅ ብሎ መንገዳቸው ላይ ቆመ፡፡ መትረየስ ይዟል፡፡ ቁም! አለ፤ ቆሙ፡፡

‹‹እኔ ፊደል ካስትሮ ነኝ››

‹‹አውቅሀለሁ፡፡ በል አሁን አዙርና በመጣህበት ተመለስ››

‹‹ስማ፡፡ እነዚህ የውጭ አገር እንግዳዎቻችን ናቸው››

‹‹ይሁኑ፡፡ እነሱ ሊያልፉ ይችላሉ ከፈለጉ፡፡ አንተ ግን ትመለሳለህ››

‹‹እንትንን (የቦታ ስም) ላስጎበኛቸው እኮ ነው››

‹‹በዛኛው መንገድ ውሰዳቸው››

‹‹ያ ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም፣ ይህ አቋራጭ እያለ? ጊዜያችንን ለምን እናባክናለን?››

‹‹ይኼ ጫካ ስለሆነ፡፡ ጠላት አደጋ ሊጥልብህ ስለሚችል፡፡ አሁን እኔ ጠላት ልሆን እችል ነበር፡፡ አንተስ ሞትክ ነው አለቀልህ፤ እኛ ግን ከዚያ በኋላ ምን እንሆናለን? አታስብልንም?››

እነ ካስትሮ እነ ሳርትር አዙረው በዙሪያ ጥምጥሙ መንገድ መሄድ ግድ ሆነባቸው፡፡ ፊደል ካስትሮ የዚህ ሰውዬ ነገር ሳይከነክነው አልቀረም፡፡ ለማንኛውም ተስፋዬ ገሰሰ አጋጥሞት አይቶ የነገረኝ እነሆ፡፡ ለተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ወደ ኒውዮርክ ሲመጡ ከፕሬዚዳንቶቹ ሁሉ የማን አጀብና ጓዝ ይበዛል? የፊደል ካስትሮ፡፡ ሀርለም ውስጥ (የጥቁሮች ሰፈር) ነበር ያረፈው ካስትሮ፡፡ ሆቴሉን በሙሉ የያዙት እነካስትሮ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ካስትሮ ሲአይኤን አያምንም፡፡ ዛሬ ተበልቶ የዛሬ ወር የሚገድል መርዝ ቢያበሉትስ? ለሞትም ሳይሆን ለበሽታ ቢዳርጉትስ? ያልጠረጠረ ተመነጠረ ነው፤ ወዳጄ፡፡ ስለዚህ በግስ ዶሮስ ድንችንስ ምንስ – ካስትሮ የሚበላውና የሚጠጣው ከኩባ ይዞት የመጣውን ብቻ ነው፡፡

‹‹ካስትሮ ለሕዝቡ በሬድዮና በቴሌቪዥን ሲናገር ለሰዓታት ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከአሥር ሰዓት በላይ ተናግሯል፡፡ በሌላ ኮሚኒስት አገር ቢሆን ሕዝቡ ፈርቶና ተገዶ ነው የሚያዳምጠው፡፡ ኩባውያን ታዲያ ካስትሮ ንግግር ያደርጋል ሲባል አብዛኛውን ሌላ የግል ፕሮግራማቸውን ሰርዘው ያዳምጡታል፡፡ ብዙ ተማሪዎች እሱን ለማዳመጥ ሲሉ ከትምህርት ይቀራሉ (ይፎርፋሉ)፡፡

ብዙ ኩባውያን እንዲህ ይላሉ ‹‹የሶሻሊዝም ጎዳና ባይመችም፣ ችግር ቢበዛበትም፣ ፊደል ካስትሮ መንገዳችን ነው ብሎ እስከመረጠው ድረስ ለእኛ መንገዳችን ነው፡፡ እሱ እንሂድ እስካለ ድረስ እንሄዳለን፡፡››

ባጭሩ ፊደል ካስትሮ ነፃ አውጪ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡ ውድ መሪ ጭምር ነው፡፡

ጋዜጠኛ መቼስ እፍረት አያውቅም፡፡ አንዱ ፊደል ካስትሮን ‹‹ለምን ጢምዎን አይላጩትም?›› ብሎ ጠየቀው፡፡

መልስ ‹‹እኔ የምላጨው አገሬ ምላጭ ስታመርት ነው››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...