Thursday, May 30, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጤፍን ወደ ሜካናይዝድ እርሻ የሚያሸጋግሩ ማሽኖች አገር ውስጥ ገቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ማሽኖቹን አገር ውስጥ ለማምረት ታስቧል

በኢትዮጵያ ከ50 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በቋሚነት የሚመገበውን ጤፍ ከኋላቀር አስተራረስ አላቀው ወደ ዘመናዊ ግብርና ያሸጋግራሉ የተባሉ ማሽኖች አገር ውስጥ ገቡ፡፡ እነዚህን ማሽኖች አገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈርሟል፡፡

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና በቻይና ሜካናይዜሽን አካዳሚ ትብብር፣ እንዲሁም በሜሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ፋይናንስ አቅራቢነት የተመረቱት ማሽኖች በአሁኑ ወቅት በቻይና ተመርተው አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር የሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለጤፍ እርሻ አስፈላጊ የሆኑት እነዚህ ማሽኖች ተመርተው አገር ውስጥ መግባታቸው፣ ለኢትዮጵያ የጤፍ ግብርና እጅግ መልካም ዜና ነው፡፡

‹‹ሚኒስቴሩ የጤፍ እርሻን በሚመለከት አነስተኛ የጤፍ ፕሮጀክት ቀርፆ እየሠራ ነው፡፡ እስካሁን ትኩረት ተደርጎ የተሠራባቸው አራት ጉዳዮች ሲሆኑ እነሱም የጤፍ እርሻ ማረሻ፣ መዝሪያ፣ ማጨጃና መውቂያ ማሽኖች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ማጨጃና መውቂያ ማሽኖች ላይ ተሳክቶልናል፡፡ ማሽኖቹም አገር ውስጥ በመግባታቸው በሳምንቱ መጨረሻ ርክክብ ይደረጋል፤›› ሲሉ አቶ ታምሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ታምሩ ጨምረው እንደገለጹት አገር ውስጥ የገቡት ስምንት ማሽኖች ናቸው፡፡ ማሽኖቹ ጤፍ በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ተሞክረዋል፡፡ በቀጣይነትም ማሽኖቹ በብዛት የሚፈለጉ በመሆኑ አገር ውስጥ እንዲመረቱ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ‹‹እነዚህ ማሽኖች አገር ውስጥ ለማስመረት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ቻይና ሜካናይዜሽን አካዳሚ የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመናል፤›› ሲሉ አቶ ታምሩ አስረድተዋል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በአራቱ ትልልቅ ክልሎች በተለይ የግብርና ምርቶች በብዛት በሚመረትባቸው አካባቢዎች፣ አርሶ አደሮች ያላቸውን መሬት ድንበር አፍርሰው በጋራ አንድ ዓይነት ምርት እንዲያመርቱ ዕቅድ አውጥቷል፡፡፡

ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የግብርና ሜካናይዜሽን በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውል መመርያ ተሰጥቷል፡፡ በተያዘው ምርት ዘመን በአራት ክልሎች የሚገኙ 239 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 2.6 ሚሊዮን አርሶ አደሮች በጋራ 2.1 ሚሊዮን ሔክታር መሬት አደባልቀው እንዲያለሙ መደረጉ ታውቋል፡፡

በተለይ ጤፍ ላለፉት ዘመናት ወደ ሜካናይዜሽን መሻገር ባይችልም፣ በኢትዮጵያ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር መሬት ይለማል፡፡ ነገር ግን ጤፍ በኢትዮጵያ 50 ሚሊዮን ሕዝብ በቋሚነት የሚመገበው ዋነኛ ሰብል ቢሆንም፣ መሬት ለማረስ በአርሶ አደርና በእንስሳት ጉልበት ከስድስት ጊዜ በላይ መታረስና መለስለስ ያለበት በመሆኑ፣ ከዚህ በተጨማሪም አጨዳውና ውቂያውም እጅግ አድካሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በጤፍ ማሽን በዘመናዊ ዘዴ ለማልማት የተሞከሩ ሙከራዎች ውጤት ሳያመጡ ቆይተው በመጨረሻ ውጤት ተገኝቷል ተብሏል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ኢያሱ አብርሃ (ዶ/ር) በቅርቡ በምሥራቅ ጎጃም በተካሄደ የሜካናይዜሽን በዓል ላይ እንደተናገሩት፣ የጤፍ ማሳ ዝግጅት እጅግ አድካሚ ነው፡፡ የምርት ብክነቱም ከፍተኛ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ኋላቀር አሠራር በማስቀረት ወደ ሜካናይዜሽን እየቀየረው ነው፡፡ ይህ ሜካናይዜሽን አሠራር ከጤፍ በተጨማሪ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላና ገብስ በመሳሰሉ ሰብሎች ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች