- ተጠያቂው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት ይቀርብበታል ተብሏል
በኢትዮጵያ የሚገኙ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ተቋማት በአዲስ አበባ ያሏቸውን ፕሮጀክቶች ተናበው ለማካሄድ ቢስማሙም፣ ቅንጅቱ የተሟላ ባለመሆኑ ስምምነታቸው ፈተና ገጥሞታል፡፡
ተቀናጅተው እየሠሩ ባለመሆኑ ለሚደርሰው ጉዳት ተጠያቂ የሚሆኑ ኃላፊዎች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በሚሰበስቡት ስብሰባ ሪፖርት ይቀርብባቸዋል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሠረተ ልማት ቅንጅት የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ራሱን አደራጅቶ ኃላፊነቱን እስኪረከብ ድረስ፣ በፌዴራልና በአዲስ አበባ ሥር የሚገኙ የመሠረተ ልማት ተቋማትን የማስተባበር ሥራ ለፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ተሰጥቷል፡፡
ኤጀንሲው ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ጋር ግንባታዎችን በቅንጅት ለማካሄድ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ነገር ግን ይህ ፊርማ ጥቅምት 29 ተካሂዶ በቀጣዩ ኅዳር 2010 ዓ.ም. የተካሄዱ በርካታ ፕሮጀክቶች መቀናጀት እንደተሳናቸው ታይቷል፡፡
በተለይ በአሁኑ ጊዜ እየተገነቡ ያሉ የእግረኛ መንገዶች፣ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታዎችና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች በቅንጅት እየተገነቡ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የፌዴራል የተቀናጀ መሠረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ገብረ መድኅን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራዎችን አቀናጅቶ ለማካሄድ ችግር አጋጥሟል፡፡
‹‹የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ቤተ መንግሥት አካባቢ የእግረኛ መንገድ እየሠራ ነው፡፡ ሥራው ግን ቅንጅት ይጎድለዋል፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ገልጸው፣ ‹‹ማክሰኞ ታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ የቅንጅት ችግር መኖሩን አረጋጋጠናል፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡
በሁሉም የመሠረተ ልማት ተቋማት ትልልቅ ፕሮጀክቶች በአንድ ጊዜ እየተካሄዱ ነው፡፡ ለአብነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአዲስ አበባ ያለውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለማስቀረት 126 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ መስመሮች እየዘረጋ ነው፡፡
እስካሁን 100 መስመሮች ኪሎ ሜትር የተዘረጉ ሲሆን፣ 26 ኪሎ ሜትር ደግሞ በዝርጋታ ላይ ይገኛሉ፡፡ ጎማ ቁጠባ (አምስተኛ አካባቢ) ይህ ሥራ እየተካሄደ ቢሆንም፣ የእግረኛ መንገዱ ግን ከሥር ከሥር እየተካሄደ አይደለም ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ፍሳሽ አወጋገድን ዘመናዊ ለማድረግ ቁፋሮ እያካሄደ ነው፡፡ ይህንን ቁፋሮ አገር በቀሉ አሰር ኮንስትራክሽን ኩባንያ እያከናወነ ሲሆን፣ አቶ ሰለሞን እንዳሉት ፕሮጀክቱ የቁጥጥር ማነስ ታይቶበታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአውቶቡስ ማቆሚያ ፌርማታዎች ግንባታ እየተካሄደ ነው፡፡ አቶ ሰለሞን እንዳሉት ይህ ፕሮጀክት ግንባታው እንዲካሄድ የተፈቀደው በ2008 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በበጀት አለመፈቀድ ምክንያት በዚህ ዓመት ነው ግንባታው እየተካሄደ ያለው፡፡
የቅንጅቱ ሥራ የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የቴክኒክ ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ ተጠያቂ አካል እንዲለይ ወስኗል፡፡ በዚህ መሠረት ጠቀላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ ይጠራሉ ተብሎ በሚጠበቀው ስብሰባ ላይ ሪፖርት እንደሚደረግ አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡