Monday, October 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት ዓውደ ግንባር አይሁኑ!

የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከበፊት ጀምሮ የኢትዮጵያውያን ሁነኛ መገናኛ ሥፍራ በመሆናቸው ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ›› በመባል ይታወቃሉ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀቁ ለጋ ወጣቶች ከአራቱም ማዕዘናት የሚገናኙባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ወዘተ. ተቻችለውባቸው የመማር ማስተማር መርሐ ግብራቸውን ሲያከናውኑ ነው የሚታወቁት፡፡ በዚህም ምክንያት ለዓመታት የአገር አንድነት የሚንፀባረቅባቸው፣ ተማሪዎችም ከተለያዩ ሥርዓቶች ጋር ችግር ቢኖርባቸውም በአንድነት የሚቆሙባቸው፣ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይገድባቸው በሠለጠነ መንገድ የሚወያዩባቸውና የሚከራከሩባቸው እንጂ እርስ በርስ ጎራ ለይተው የሚፋለሙባቸው ዓውደ ግንባር በመሆን አይታወቁም፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በደርግና በኢሕአዴግ ዘመን ጭምር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚታወቁት በሥርዓት ላይ በአንድነት ሲነሱ ነው፡፡ በእርግጥ ባለፉት 26 ዓመታት አልፎ አልፎ ብሔር ተኮር ግጭቶች ቢታዩም እንኳ አድማሳቸው በጣም የጠበበ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግለሰብ ግጭቶች ሳይቀሩ ወደ ብሔር እየተቀየሩ አገሪቱን ችግር ውስጥ የሚከቱ ቀውሶች እየተፈጠሩ ነው፡፡

ወጣቶች ትምህርታቸውን ለመከታተል ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ  የነገ አገር ተረካቢዎች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ በሃያዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኙ ለጋ ወጣቶች በብሔር ጎራ ለይተው እርስ በርስ ሲጠቃቁ  ግን ግራ ያጋባል፡፡ ትናንት ከትናንት ወዲያ ግንባራቸውን ለአረር እግራቸውን ለጠጠር አጋልጠው በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት መስዋዕት የሆኑ ጀግኖችን ባፈራች አገር ውስጥ፣ ለሰሚ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ በብሔርተኝነት በመቧደን ወጣቶች ሲጋጩና ለአደጋ ሲጋለጡ ማየት በእጅጉ ያሳፍራል፡፡ ይህ ትውልድ ወዴት እየሄደ ነው ከማለት በመውጣት ይህንን አደገኛና አሳፋሪ ተግባር ማስቆም የመንግሥትም ሆነ የዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻችንን ምን እያስተማርን ነው በማለት ራሳቸውን በአፅንኦት መጠየቅ ሲኖርባቸው፣ መንግሥት ደግሞ ለችግሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ብሔራዊ የመወያያ መድረክ መፍጠር ይገባዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀት መገብያ፣ የመወያያ፣ የመከራከሪያና የተለያዩ ድምፆች ማስተጋቢያ መሆን አለባቸው፡፡ ልዩነቶች የሚከበሩባቸውና በዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አመለካከቶችም የሚንፀባረቁባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ እነዚህ ተቋማት የሥልጣኔ ጮራ መሆን ሲገባቸው የግጭት መናኸሪያ ሲሆኑ ያሳዝናል፣ ያሳፍራል፡፡ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነትም አደጋ ነው፡፡

በኢሕአዴግ መሪነት የተመሠረተው የፌዴራል ሥርዓት በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች ፌዴራላዊት አገር እየተገነባች ነው ይላል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ያፀናው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ 23 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ተከብሯል፡፡ ኢሕአዴግም ከብሔር ብሔረሰቦች ብዝኃነት ጀምሮ ልዩነት ውበት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ተሰምቷል፡፡ ‹‹በልዩነት ውስጥ አንድነትን፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነትን›› መቀበል ግዴታ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሐሳብ በኢሕአዴግ ዘመን በተወለዱ ወጣቶች ዘንድ ምን ያህል ሰርጿል? በእርግጥ ልዩነትን ውበት አድርጎ በመቀበል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት የተደረገው ጥረትስ ምን ያህል ነው? ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በስፋት እየተጋተ ያደገው ይህ የኢሕአዴግ ትውልድ፣ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በብሔርተኞች እየተነዳ ጥፋት ሲፈጽም ምን ይባላል? የኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል እየደበዘዘ ብሔርተኝነት ሲገን ችግሩ ምን ይሆን መባል የለበትም? ችላ ማለት የውድቀት ምልክት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጫ የጋራ እሴቶች መካከል አንዱና ዋናው በመፈቃቀድና በመተሳሰብ አብሮ መኖር፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በጋብቻ በመተሳሰር ትልቅ አርዓያነት ያለው ተግባር መፈጸም ሆኖ ሳለ፣ ከዚህ በተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ሲፈጸሙ የአሁኑን ትውልድ ሊያሳፍር ይገባል፡፡ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እርስ በርስ ሲጠቃቁና ጉዳት ሲደርስ ማፈር ያለባቸው እነሱን ያፈራ ትውልድና መንግሥት ናቸው፡፡ በታሪክ ፊት ተጠያቂ የሚያደርግ ጥፋት እየተፈጸመ ሲሆን፣ የትውልዱን ውድቀት ማሳያም ነው፡፡

መንግሥት አገርን ሲያስተዳድር የሕዝቡን ደኅንነት የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ አገርን በሥርዓት ማስተዳደር ሲያቅተው ግን የአገር ምልክት የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የግጭት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት በተለያዩ ሥፍራዎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን ማስቆም አቅቶአቸው አገር ውጥረት ውስጥ እያለች፣ አሁን ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት ዓውደ ግንባር እየሆኑ ነው፡፡ ይኼ መንግሥትን በእጅጉ ሊያሳፍረው ይገባል፡፡ ከወላጆቻቸው ጉያ ወጥተው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ለጋ ወጣቶች የግጭቶች ሰለባ ሲሆኑ፣ መንግሥት ከማንም በላይ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ ግን አንዱ ዘንድ የፈነዳ ግጭት ሌላ ቦታ እየተደገመ ዩኒቨርሲቲዎች አስፈሪ ሆነዋል፡፡ ወላጆች ለጭንቀት ተዳርገዋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን ጉዳይ እንዳላዩ ማለፍ ያስተዛዝባል፡፡ ይልቁንም በብሔራዊ ደረጃ አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኖ በአስቸኳይ ተመክሮበት መፍትሔ መፈለግ ግድ የሚባልበት ወቅት ላይ ነን፡፡ መንግሥት ለዚህ አሳሰቢ ጉዳይ ፈጣን ምላሽ ካልሰጠ በታሪክ ይጠየቃል፡፡ አሁን የሚፈለገው መፍትሔ ብቻ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ አንዱ ዋነኛ ችግር ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው መረጃ ከመለዋወጥ ባለፈ በርካታ ምሥጉን ተግባራት የሚከናወኑበት መሆን ሲገባው፣ በአሁኗ ኢትዮጵያ ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነት ማራመጃ እየሆነ ለጋ ወጣቶች እየተመረዙ ነው፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸው ጽንፈኛ ብሔርተኞች እያንዳንዷን ነጠብጣብ እየተከታተሉ የወጣቶችን አዕምሮ ሰቅዘው በመያዝ፣ የአንዱ ብሔር ወጣት በሌላው ላይ እንዲነሳ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ግጥሞችን፣ መነባንቦችን፣ ሐሰተኛ ወሬዎችን፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የውሸት ምሥሎችን በመፈብረክ ኢትዮጵያውያን ከሚታወቁባቸው ጨዋነትና አስተዋይነት ያፈነገጡ የእርኩሰት ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዝቅጠቶች በታሪክ እንደሚያስጠይቁ ተገንዝበው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መላ መፈለግ አለበት፡፡ በዓለም ላይ አዶልፍ ሒትለርም ሆነ ቤኒቶ ሙሶሎኒ በታሪክ ፊት ጥላሸት የተቀቡት፣ በናዚዝምና በፋሽዝም የዘቀጠ አስተሳሰብ ዓለምን ለዕልቂት በመዳረጋቸው ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ውስጥ የመሸጉ ኃይሎችም ድርጊታቸው ከእነዚህ ታሪካቸው ከተበላሸ ሰዎች የማይለይ በመሆኑ ራሳቸውን በፍጥነት ሊያቅቡ ይገባል፡፡ ለጋ ወጣቶችን በማፋጀት አገር ከማፍረስ ውጪ ምንም አይገኝም፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ማፍረስ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡

በተደጋጋሚ እንደምንለው ኩሩውና ጨዋው የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ የሚታወቀው በአገር ፍቅር ስሜቱ፣ እርስ በርስ ተከባብሮና ተዋዶ በመኖሩ፣ ያለውን ተሳስቦ በመካፈሉና ለእንግዳ ባለው ልዩ አክብሮትና መስተንግዶ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ወደ ሰሜን፣ ምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ደቡብ አቅጣጫዎች ቢኬድ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ አኩሪ የጋራ እሴቱ ይታወቃል፡፡ ድንገት ግጭት ቢፈጠር እንኳን ተረባርቦ ከለላ የሚሰጠው ራቅ ካለ ሥፍራ ለመጣ ወገኑ ነው፡፡ አሁንም በየቦታው እየታየ ያለው ይኼ አኩሪ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ መሆን የሚገባውን የፖለቲካ ትግል ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚመሩ ኃይሎች ጽንፈኛ አቋም በመያዝ ወጣቶችን መጠቀሚያ እያደረጉ ነው፡፡ ለጋ ወጣቶችን በእኩዮቻቸው ላይ ያነሳሳሉ፡፡ ምንም ዓይነት ምክንያት ሳይኖር የብሔር እሳት እየጫሩ ይማግዱዋቸዋል፡፡ ይህንን አሳዛኝና ድርጊት ተግባር በአስቸኳይ የማስቆም ሙሉ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ ከዚያም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሌላው ትልቁ ተግባር በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸውን መብቶችና ነፃነቶች ማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን በተግባር ማረጋገጥ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በፍጥነት ማስቆም፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን፣ ወዘተ. በምንም ዓይነት ሁኔታ መታለፍ የለባቸውም፡፡ ዜጎች በነፃነት መኖራቸውንና በእኩልነት መስተናገዳቸውን በተግባር ማረጋገጥ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዕውን ሲሆን ዩኒቨርሲቲዎች የዕውቀትና የምርምር ማዕከላት እንጂ የብሔርተኝነት ምድጃ አይሆኑም፡፡ በዚህ እሳቤ ዩኒቨርሲቲዎች የግጭት ዓውደ ግንባር አይሁኑ መባል አለበት!  

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...