Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ እየመከረ ነው

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ እየመከረ ነው

ቀን:

ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሰባ፣ በአገሪቱ የፀጥታ ጉዳይ ላይ እየመከረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደጠቆሙት የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ማክሰኞ ታኅሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ የተጀመረ ሲሆን፣ በዋናነት አገሪቱ ባጋጠማት የፀጥታ ጉዳይ ላይ እየመከረ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር አድርጎት በነበረው ስብሰባ አገሪቱ ያለችበት የፀጥታ ጉዳይ ተነስቶ እንደተመከረበት መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም በዋናነት በዚህ አጀንዳና ከዚያ ወዲህ በአገሪቱ እየተፈጠሩ ባሉ ችግሮች ላይ እየተወያየ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ ከሁሉም ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችና የፀጥታ አካላት ጋር አድርጎት በነበረው ስብሰባ እየተከሰተ ያለው ቀውስ እንዲቆም የሁሉም ክልሎች አመራሮች ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ ውሳኔ ቢያስተላልፍም፣ በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች ተፈጥረው ከሃያ በላይ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ትምህርት ከመቋረጡ በተጨማሪ፣ በብሔር ተኮር ግጭት የተማሪዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡

ሁለተኛው የኢሕአደግ ሥራ አስፈጸሚ ኮሚቴ የመወያየ አጀንዳ በድርጅቱ ውስጣዊ አንድነት ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በአባል ድርጅቶች መካከል እየተፈጠረ ያለውን መላላት በመፈተሽ አዳዲስ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ በአሁኑ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ለየት ያሉ ጠንካራ ውሳኔዎች ሊተላለፉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ፣ በአባል ድርጅቶች መካከል መጠራጠር አለ፡፡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ይኼን ግምት ውስጥ በማስገባት አዳዲስ የውሳኔ ሐሳቦችን ሊያስተላልፍ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የተፈጠረው አለመተማመን የቆየና እየተደራረበ የመጣ ነው ያሉት አቶ ሽፈራው፣ ቢዘገይም አሁን የፓርቲው አመራር አገሪቱን ከውድቀት ለመታደግ ኃላፊነት የተሞላበት ውሳኔ ያስተላልፋል የሚል ዕምነት እንዳላቸው መግለጻቸው ተሰምቷል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ መካሄድ የጀመረው የሕዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሰላሳ አምስት ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ በመሆኑ፣ ብዙ አዳዲስ ነገሮች ይጠበቃሉ፡፡ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ  ስብሰባውን ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ሕወሓት የጥገኛ መደብ ፈተና እንደ ገጠመው ገምግሟል፡፡ በዚህም የፓርቲውን ሊቀመንበር ከማውረድ ጀምሮ አዳዲስ ሰዎችን ወደ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነት አምጥቷል፡፡

የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ከወራት በፊት አካሂዶት በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ፣ አሥር ነጥቦች ያሉት የአቋም መግለጫ እንዳወጣ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ከመግባቱ በፊት የአንድ ቀን ስብሰባ እንዳደረገ ታውቋል፡፡ ብአዴን በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ የክልሉ ሕዝብ በሚፈልገው ተክለ ቁመና ላይ አለመሆኑን እንደገመገመ፣ ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር መራመድ የሚያስችሉ አዳዲስ አቅጣጫዎችን ለመከተል ውሳኔ ማስተላለፉን የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...