የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ወደ አገር የሚገቡ ምርቶችና ሸቀጦች ከዓለም አቀፍ ዋጋቸው በታች በሆነ ሒሳብ በባንኮች በኩል ይከፈቱላቸው የነበሩ የቅድመ ክፍያ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት – ኤልሲ)፣ ካሁን በኋላ በትክክለኛ ዋጋቸው እንዲስተናገዱ የሚያስገድድ መመርያ በቅርቡ አወጣ፡፡
ብሔራዊ ባንክ ሁሉም የንግድ ባንኮች ተግባራዊ እንዲያደርጉት ያሠራጨው መመርያ፣ ከዚህ ቀደም ባንኮች ከትክክለኛ ዋጋቸው በታች ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች ኤልሲ መክፈት እንደማይችሉ ያሳስባል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ሸቀጦችና ምርቶች ሰበብ የሚፈጸሙ ሕገወጥ የገንዘብ ማሸሽ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር መመርያውን እንዳወጣ ተገልጿል፡፡
በመመርያው መሠረት የሚመለከታቸው 34 ምርቶችና ሸቀጦችን ለማስገባት የሚቀርብላቸውን ጥያቄ ባንኮች ማስተናገድ የሚችሉት፣ የትክክለኛ ዋጋቸውን ጠቋሚ የገበያ ወይም የምርት ዋጋ መነሻ በማድረግ ብቻ ነው፡፡
ለዕቃዎች አማካይ የዋጋ ማሳያ የተቀመጠላቸው በመሆኑም በዚሁ መሠረት ባንኮቹ ማስተናገድ እንደሚገባቸው የተቀመጠ ሲሆን፣ አስመጪዎችም ትክክለኛ ዋጋ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው የምርቶች ዋጋ ዝርዝር መሠረት አገልግሎቱን ስለመስጠታቸው የሚያረጋግጥ መረጃ በመያዝ ባንኮቹ ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች የፕሮፎርማ ደረሰኝ ማሳየት እንደሚገባቸው መሥፈርት ያስቀመጠ ሲሆን፣ በዚህም ደረሰኝ የሚቀርበው ዋጋ ትክክለኛ መሆኑን ለማወቅ ዓለም አቀፍ መለያ ቁጥር መገለጽ እንደሚኖርበት በመመርያው ሠፍሯል፡፡
ወደ አገር የሚገባው ዕቃ የብራንድ ስያሜ፣ የተመረተበት አገር ወይም የሚመጣበት አገር፣ የምርቱ ብዛት፣ የመነሻ ወደብና የመሳሰሉት መጠቀስ እንዳለባቸው የብሔራዊ ባንክ መመርያ አመልክቷል፡፡ በፕሮፎርማ ደረሰኝ ላይ ዕቃው ግብይት የሚፈጸምበት የገንዘብ ዓይነት፣ የምርቱ ብዛትና የነጠላ ዋጋም መጠቀስ ይኖርበታል፡፡
ባንኮች በመመርያው መሠረት አስመጪዎች የሚያቀርቡትን የገቢ ንግድ መጠየቂያ ማመልከቻ ከተያያዥ ሰነዶች ጋር በየሳምንቱ ለብሔራዊ ባንክ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ባንኮች አፅድቀው ዋጋ የሚሰጡበትን ሰነድ ደግሞ በየወሩ በኢሜይል ለብሔራዊ ባንክ መላክ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በዚህ መመርያ መሠረት ከደረሰኝ ዋጋ በታች ወይም በአንደር ኢንቮይሲንግ የሚሠሩ አስመጪዎችና በአንደር ኢንቮይሲንግ ፈቃድ ሲሰጡ የሚገኙ ባንኮች ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ መመርያ የጣሱ ባንኮች ከተገኙ፣ የሚተላለፈው ቅጣት በእያንዳንዱ የሕግ ጥሰት 10 ሺሕ ብር እንደሚደርስ ታውቋል፡፡
የመመርያውን መውጣት ተከትሎ ባንኮች የአንዳንድ አስመጪዎችን ጥያቄ ማስተናገድ ያቆሙ ሲሆን፣ መመርያው የሚደግፋቸውና ቀደም ያሉ ጥያቄዎችንም ደንበኞቻቸው በአዲሱ አሠራር እንዲያስተካክሉ እያደረጉ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡