በኃይለ ሥላሴ ጊዜ፤…
ፀረ-ሦስት ነበርኩ
…ፀረ-ፊውዳል፣ ፀረ-መሳፍንት፣
ፀረ-ኢምፔሪያሊስት፡፡
በደርግ ጊዜም፤
ፀረ-ሦስት ነበርኩ
…ፀረ-ፊውዳል፣ ፀረ-
ቢሮክራቲክ-ካፒታሊስት፣ ፀረ-
ፋሺስት፡፡
ዛሬሳ እኔ ምንድነኝ?፣
ብዬ ልጽፍ፣ ቁጭ አልኩኝ፡፡
በድንገት መብራት ጠፋብኝ፡፡
እስኪመጣ ‹‹ሻወር›› ገባሁ፡፡
እየታጠብኩ፤ ውኃ ሄደ፡፡
እጅግ በጣም ተናደድኩኝ፡፡
ለሚመለከተው አቤት ልል
ተነሳሁ ስልክ ልደውል፡፡
‹‹ኔት-ወርክ›› እሚባል የለም፡፡
በቃ
ፀረ-ሦስት ስለመሆኔ፣
መጻፍ አላስፈለገኝም!!
- ነቢይ መኰንን ‹‹ስውር ስፌት›› ቁጥር 2
***
የ116 ዓመት ደብዳቤ
ይድረስ ከቢትወደድ ኢልግ
የነገርከኝ የቁንጫ መድኃኒት በስሃን አድርገን ብንሞክረው የሚያልቀው ቁንጫ እጅግ በጣም ጉድ ነው፡፡ አንተው እንዳልከው እውነተኛ መድኃኒት ሆነ፡፡
መስከረም 7 ቀን አዲስ ዓለም ከተማ ተጻፈ 1894 ዓ.ም.
******
ይድረስ ከአባ እንድርያስ፡፡
እጅግ የሚጣፍጥ ኦራንጅ በዘውገ እጅ የላኩልኝ ሁለት አገልግል ደረሰልኝ፡፡ ለዓርብና ለሮብ በቃኝ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡
መስከረም 7 ቀን አዲስ ዓለም ከተማ ተጻፈ 1895 ዓ.ም.
(ሁለት አገልግል የተባለው ሁለት ካርቶን ነው፡፡ ልጅ ዘውገም በጂቡቲ የምኒልክ ጉዳይ ፈጻሚ ነበሩ)
- ጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጤ ምኒልክ›› (1984)
******
እንዲያው በንዲያው
- ጠያቂ፡- ባለበግ በዘንጉ እየነካ
- መላሽ፡- አይሸጥም ለዘንግ
- ጠያቂ፡-ምን ይላል
- መላሽ፡- ባ
- ጠያቂ፡- የት ያደገ ነው
- መላሽ፡- እጋጥ
- ጠያቂ፡- ምን ያራል
- መላሽ፡- በጠጥ
- ጠያቂ፡- ምነው ይኸ ጠማማ
- መላሽ፡- ቀንድ ነዋ አለና አበሸቀው ይባላል፡፡
- መሸሻ ግዛው ‹‹እርስ በርሳችን በወፎች ቋንቋ ንግግራችን›› (1949)
*****
አበባ በታኟ ውሻ
ከሰሞኑ በቺካጎ ከተማ በተከናወነ የሠርግ ፕሮግራም ላይ ያልተለመደ ነገር ግን አስደናቂ ክስተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ብራያን ሺፋር የተባለችውን ሙሽራ በሠርጉ ዝግጅት አጅበው ከተገኙ አበባ በታኞች መካከል ማራኪ ቀለም ያላት ፀጉራም ውሻ አንዷ ነበረች፡፡ ‹‹ውሻዋ የቤተሰቡ አንድ አባል ነች፡፡ በየሄድኩበት አብራኝ አለች፡፡ ለኔ ልክ እንደ ጥላዬ ነች፡፡ ስለዚህም በዚህ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳትገኝ ማድረግ ለኔ ምርጫ አልነበረም ያለችው ሙሸራዋ ብራያን ነበረች፡፡ በሰንሰለት ፈንታ አንገቷ በአበባ ያጌጠው ይህች ውሻ የታዳሚውን ቀልብ ስባለች፡፡ በፎቶ ፕሮግራም ላይም እንዲህ ከሙሽራዋ ጎን ቆማ እንደነበር የዘገበው ያሆ ኒውስ ነው፡፡
***
አፕል በ400 ሚሊዮን ዶላር ሼዛምን ሊገዛ ነው
የዩናይትድ ኪንግደሙ ሼዛም እ.ኤ.አ. በ1999 የተገኘ አፕሊኬሽን ነው፡፡ ሼዛም አንድን ሙዚቃ አዳምጦ የማን ሥራ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ሙዚቃውን ገዝተው እንዲያደምጡ ያደርጋል፡፡ በየወሩ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎተ ያሉት ሼዛም ሙዚቃዎች የሚሸጠው ከአፕል የሙዚቃ ክምችት ሲሆን፣ ገቢውን የሚያገኘውም አፕል ከሚያስብለት ኮሚሽን ነው፡፡ አፕል ይኼንን አፕሊኬሽን ለመግዛት ፍላጎት አሳይቷል ያቀረበው ጥያቄም ይሁንታን አግኝቷል፡፡ አጋጣሚው አፕል ለኮሚሽን ብሎ የሚያወጣውን ወጪ ያስቀርለታል፣ ትርፋማም ያደርገዋል መባሉን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡