Sunday, April 14, 2024

ምሁራን አገራዊ ግዴታቸውን እንዳልተወጡ የተብራራበት ኮንፈረንስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሐረግ ጥበቡ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተማሪ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ ከምዕራብ ጎጃም ዞን እንደመጣች ታስረዳለች፡፡ ቤተሰቦቿ አርሶ አደሮች እንደሆኑና ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ እንደሚገፉ ትገልጻለች፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ ዩኒቨርሰቲዎች እየተሰሙ ያሉ ዜናዎች እያሳሰባት መሆኑን ትናገራለች፡፡ ትምህርቷን አጠናቅቃ አስተምረው ለዚህ ያደረሷትን ቤተሰቦቿን ለመርዳትና ለማስደሰት ህልም ቢኖራትም፣ በአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታዩ ነውጠኛ ድርጊት በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲም እንዳይከሰት ትሠጋለች፡፡ የብሔርተኝነት ስሜት ተስፋፍቶ የአንድ አገር ዜጎች እየተከፋፈሉና እርስ በራሳቸው እየተጠፋፉ መሆናቸው እንደሚያስጨንቃት ታስረዳለች፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል የምሁራን ኮንፈረንስ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በመካሄዱ ደግሞ ተደስታለች፡፡

እሑድ ታኅሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በአማራና በኦሮሚያ ምሁራን መካከል በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የጋራ የሕዝብ ለሕዝብ የቅኝት መድረክ ተካሂዶ ነበር፡፡ የመድረኩ ዋና ዓላማ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለመ ነበር፡፡

‹‹የአማራና የኦሮሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት   ቅኝት ኮንፈረንስ›› የሚል ስያሜ በተሰጠው ኮንፈረንስ ተሳታፊ ከነበሩ ምሁራንና ግለሰቦች መካከል የሁለቱ ክልሎች ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች፣ ምሁራን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጋበዙ ምሁራን፣ ከፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች (ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለን ጨምሮ) የሁለቱም ክልሎች የቢሮ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን፣ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ተወካዮችና የደብረ ብርሃን ከተማ የማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተው ነበር፡፡

የሁለቱ ክልሎች ምሁራን ኮንፈረንስ በሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር በአገራዊ ግንባታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑ ታውቋል፡፡ በአማራና በኦሮሞ ሕዝቦች መካከል የተጀመረው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረውና ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ተካሂዶ በነበረው የሕዝብ ኮንፈረንስ ላይ የተላለፉ ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንደሆነ በዕለቱ ተገልጿል፡፡

በምሁራኑ ውይይት ላይ ለመነሻነት ሁለት ጽሑፎች ቀርበው   ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ‹‹በዘመናዊ ዓለም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግንኙነትና ወንድማማችነት›› የሚል ርዕስ የተሰጠውን የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር ታምራት ኃይሌ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ሁለተኛውን ‹‹የሕዝቦች አንድነትና የምሁራን ሚና›› የሚል ስያሜ የተሰጠውን የውይይት መነሻ  ጽሑፍ ያቀረቡት ደግሞ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር አቶ ሥዩም ተሾመ ናቸው፡፡ የምሁራኑን ኮንፈረንስ የመሩት ደግሞ የፍልስፍና መምህሩ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተፈራ በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ‹‹የኦሮሞና የአማራ የሽምግልና ሥርዓቶች ዘመን የማይሽራቸው ቱባ የችግር አፈታት ቅርሶቻችን ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በኮንፈረንሱ የመጀመሪያውን የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር ታምራት ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል፣ ‹‹ሞገደኛው ዘመናዊ ዓለም በፍጥነት እየመጣ ሲሆን፣ እኛ ግን እጃችንን አጣጥፈን ዝም ብለን እየጠበቅን ነው፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በአንድ በኩል ዘመናዊ መስሎ ለመታየት ከአንገት በላይ ሲቀባባ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘመናዊ ሆኖ ለመገኘት ከአንጀቱ ሲዳክር ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ አሳልፏል፡፡ ይህ በይስሙላ ተጀምሮ ራሱን ማታለሉም ሆነ ከልቡ ተቆጭቶ የመባዘኑ ጉዳይ የኢትዮጵያ ሰምና ወርቅ ነው ተብሎ በአጭሩ ሊተረጎም ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ካሳለፍናቸው ጥቂት አሥርት ዓመታት ጀምሮ ስለሕዝቦች እኩልነትና ነፃነት የተነገረውንና የተሠራውን ያህል ስለሕዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት መወያየትና ማሰብ ተገቢ ነው እየተባለ ነው፡፡ ይህ ራሱ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ሰምና ወርቅ ሌላኛ ስም ሳይሆን አይቀርም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ታምራት በውይይት መነሻ ጽሑፋቸው ላይ ስለሕዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት በተመለከተ ሁለት ማዕቀፎች በመረሳት ላይ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ እነሱም ኩታ ገጠም መልክዓ ምድራዊና ተቋማዊ የግንኙነት ማዕቀፎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

የኦሮሞና የአማራ ሕዝቦች በኩታ ገጠም የሚኖሩ መሆናቸውን ያመለከቱት ዶ/ር  ታምራት፣ ‹‹ለብዙ መቶ ዓመታት ያዳበሩት ታሪካዊ ግንኙነት በርካታ መልክ  ነበረው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ሁለቱ ሕዝቦች በጉርብትናና ባልተቋረጠ ግንኙነት ተወራርሰዋል፡፡ አማርኛ ቋንቋ ከአፋን ኦሮሚፋ፣ እንዲሁም አፋን ኦሮሚፋ ከአማርኛ ቋንቋ ብዙ ተወራርሰዋል፡፡ በጥሞና ላስተዋለ ታዛቢ መበደርና መዋስ የሚያመለክተው አምኖ መቀበልን፣ መግባባትንና ማክበርን ነው፡፡ በኢኮኖሚው ዘርፍም በኩታ ገጠም መልክዓ ምድር በመኖራቸው የምርትና የቴክኖሎጂ መመሳሰል ከፍተኛ ነው›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡

‹‹በየክፍለ ዘመናቱ በተፈጠረውን የኃይል ግንኙነት ታሪክ፣ ከሁለቱ ሕዝቦች የግንኙነት ታሪክ ጋር ማምታታት ሳይንሳዊም ጤናማም አይደለም፡፡ ይህ የኦሮሞንና የአማራን ሕዝቦች ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ በሌሎች ሕዝቦች ሊሂቃን ጭምር የተፈጠሩና የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን ጭምር የሚመለከት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹እየተስፋፉ በመጡት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የንግድና ሌሎች የማኅበራዊ ምጣኔ ተቋማት ውስጥ የሕዝቦች ግንኙነት አዲስ ጠባይና ግብር በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ወንድማማችነት ባለመኖሩ ነፃና እኩል መሆኑ የታወቀለት ግለሰብ ሌላ መሰሉን ተጠራጥሯል፣ ሸሽቷል፡፡ ውድ የሆነ ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ጠልፎ ለመጣል አውሏል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወንድማማችነት ባለመኖሩ የተነሳም በዓለም አቀፍ የካፒታሊዝም ውድድር፣ ነፃና እኩል ነን ባይ ሕዝቦች የሰጧቸውን ብቻ ተቀባይ ከመሆን ያለፈ ዕጣ ፋንታ እንዳይኖራቸው ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

‹‹ወንድማማችነትን ችላ በማለት አካላዊ ጉዳት፣ ሥነ ልቦናዊ አለመረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ ክስረት ያጋጠመው በወንድማማችነት ፍልስፍና ውስንነት ብቻ አይደለም፡፡ ካለፈው ክፍለ ዘመን አንስቶ ነፃነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት የሚጠለሉበት ዘመናዊ ተቋማትን መገንባት ባለመቻላችን ጭምር ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ በአገሪቱ ያሉ ከፍተኛ ተቋማት እየቀነጨሩ እንደመጡና ቀድመውም የተወለዱትም ቢሆኑ እንዳያድጉ እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ታምራት ጠቀመዋል፡፡

 ታሪክንና ውጤትን ማጣጣም እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ ተቋማት በፍልስፍና ብዙ መራመድ ይገባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹በዘመናዊ ዓለም ጊዜ አለን ብዬ አላስብም፡፡ ከአንድ መቶ ሚሊዮን የማይተናነስ ሕዝብ ነፃና እኩል መሆኑ መታወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ከሚጠይቅበትና ወደ ተግባር ከሚቀየርበት ቁሳዊ መሠረተ ልማት ጋር ፊት ለፊት መገናኘት ጀምሯል፡፡ ተቋማቱ በዘፈቀደ የሚያቀርቡላቸውን ዕድሎች ቁሳዊ አገልግሎት በዘመናዊ የወንድማማችነት መርህ መሠረት እየተከፋፈሉ ከመኖር ውጪ ያላቸው አማራጭ ብዙም የሚያዘልቅ አይመስለኝም፡፡ በነፃነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት ዘመናዊ መሆን ወይም አለመሆን ጥያቄው ይኼ ነው፤›› በማለት የውይይት መነሻ ጽሑፋቸውን አጠናቀዋል፡፡

‹‹የሕዝቦች አንድነትና የምሁራን ሚና›› የተሰኘው የውይይት መነሻ ጽሑፍ ሁለተኛ ሲሆን፣ ጽሑፉን ያቀረቡት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር አቶ ሥዩም ተሾመ ናቸው፡፡ አቶ ሥዩም በውይይት መነሻ ጽሑፋቸው ላይ፣ ‹‹ለምንድነው ከማንፈልገው ድህነትና ኋላቀርነት ጋር ተላምደን የምንፈልገውንና የምንመኘውን ዕድገትና ብልፅግና ማምጣት ያልቻልነው?›› የሚል ጥያቄ በማንሳት ጽሑፋቸውን አቅርበዋል፡፡

ለልማትና ዕድገት ምቹ የሆኑ ጉዳዮች ማኅበራዊ እሴቶች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ ማኅበራዊ እሴቶቹ ደግሞ እውቀትና ነፃነት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እውቀትና ነፃነት የሌለው ማኅበረሰብ ከድህነትና ኋላቀርነት ጋር ተላምዶ እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡ ‹‹እውቀትና ነፃነት የተለየ ነገር ለመሥራት፣ የተሻለ ነገር ለመፍጠር፣ አዲስ ነገር ለመሥራት፣ አገር ለመቀየር የሚያስችሉን ቁልፍ ማኅበራዊ እሴቶች ናቸው፤›› ብለው፣ ‹‹ድህነት በሥልጣኔ መቃብር ላይ የሚበቅል አረም ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ልዩነት ያለና የሚኖር ተፈጥሮአዊ ጉዳይ መሆኑን ያወሱት አቶ ሥዩም፣ ‹‹ልዩነት ሲጠፋ ነው ነፃነት የሚገደበው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ለዘመናት ደሃ የሆነችው ሥልጣኔ ስለወደቀ ነው፡፡ ሥልጣኔን እንዴት እናንሳው ካልን ከሞተበት ነው የምናነሳው፡፡ በምን መልኩ ካልን በአዲስ እውቀትና በአዲስ ነፃነት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሰው የሚፈልገው በአገርና በቋንቋ ሳይከፋፈል በሰውነቱ እኩል መታየት ብቻ ነው፡፡ እኔም እንዳንተ እኩል መብትና ተጠቃሚነት ይገባኛል ብሎ የሚያስብ፣ የመንግሥት ድርሻና ኃላፊነት ይህን እኩልነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህን እኩልነት ሊያረጋግጥ የሚችል ፖለቲካዊ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ ይህን ሲመቸን የምንፈጥረው ነገር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ከማክበር ነው የሚመነጨው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የእኩልነት ጥያቄን መቀበል የማይገባ ጥቅምን ያሳጣል፡፡ ችግር የሚፈጠረው እዚህ ላይ ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢ ባህሪ ያለበት ቡድን የመጀመሪያ ሥራው የእኩልነት ጥያቄን ማዳፈን ነው፡፡ ይፈራል፡፡ መፍራቱ ብቻ አይደለም ችግሩ በማስፈራራት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት ይኖረዋል፡፡ ፍርኃት የጨቋኝ ሥርዓት መርህና መመርያ ነው፡፡ ጭቆና ባለበት አገር ፍርኃት እውቀት ይሆናል፡፡ ፖለቲካ እሳት ነው የሚለው እያየለ ይኖራል፡፡ የማያውቁትን መጠየቅ ወንጀል ይሆናል፡፡ ቀይ ሽብርን ላየ ቀላል ነው፡፡ ከቀይ ሽብር ስንተርፍ ፀረ ሽብር አለ፡፡ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ፍርኃት ባለበት እውቀትና ነፃነትን በዜሮ ነው የሚያጠፋው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የምሁራን ድርሻን በተመለከተም፣ ‹‹የመንግሥትን ሥራ መተቸት፣ መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች መለየት፣ የግንዛቤ ለውጥ ማምጣት፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ በዚህም የለውጥ ሐሳቦችን ማስረፅ፣ ለዕድገትና ለብልፅግና ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለሰላምና ለዴሞክራሲ መዳበር መሥራት ግዴታ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ምሁራን መንግሥትን መፍራት የለባቸውም፡፡ ምሁራን መንግሥትን በሚፈሩበት አገር መንግሥት ደግሞ ፍፁም አምባገነን ይሆናል፡፡ መንግሥት አስፈሪ በሆነበት አገር ምሁራን የመንግሥት ቃል አቀባይ ይሆናሉ፤›› ብለዋል፡፡

የውይይት መነሻ ጽሑፎች ከቀረቡ በኋላ ከተሳተፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ነበር፡፡ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አብዘኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአገሪቱን ችግሮች መፈታት ለምን ተሳናቸው? ይህን ጉዳይ አጀንዳው የሚያደርግ ምሁራን ማፍራት ለምን ተሳነን? የአገሪቱ ምሁራን ለምን በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ ላይ ውይይትና ክርክር በማድረግ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማስቀመጥ ተሳናቸው? የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ስማቸውን ያልገለጹ አንድ ግለሰብ፣ ‹‹የእኔን ማንነት አጉልቶ የማያሳይ ነፃነት ነፃነት አይባልም፤›› ብለዋል፡፡ ነፃነት ሲባል በአገሪቱ ሁለንተናዊ መስተጋብሮች እኩል የመሳተፍና የመጠቀም፣ እንዲሁም እኩል ግዴታን የመጣል እንደሆነ አውስተዋል፡፡ በአገሪቱ እየተከሰተ የመጣውን የብሔርተኝነት ስሜትና እየተስተዋሉ ያሉት ድርጊቶች ከባድ ፈተና እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ዋነኛ ምክንያቱም በውይይት መነሻ ጽሑፍ እንደተጠቆመው የዜጎች ነፃነት ማጣትና መታፈን እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ይህን ለማስተካከል ምሁራን የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡

የብሔርተኝነት ስሜት እያየለና አገራዊ አንድነት እየተሸረሸረ በቡድን የመደራጀት አባዜ እየተስተዋለ መምጣቱን የጠቆሙት ሌላ አስተያየት ሰጪ፣ ችግሩን ለማስተካከል ምሁራንና ‹አክቲቪስቶች› ሰፊ ሥራ ሊያከናውኑ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ምሁራንና አክቲቪስቶች መደማመጥ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ ታሪክ ላይ ችግር እንዳለ ያነሱት ግለሰቡ፣ ሕዝብ የግል ታሪኩን እየመዘገበ፣ አገራዊ ታሪክን እየሸረሸረና እያዛባ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ያለው እንዳወቅ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው ምሁራን የምሁርነት የሥነ ምግባርና የትውልድ ግዴታ እንዳለባቸው አንስተው፣ ‹‹ችግሩን ወደ ውጭ ከመግፋታችን በፊት መጀመሪያ እኛ እንታከም፡፡ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች የጋራ የነበሩ እሴቶች ወድመዋል፡፡ ሽማግሌዎቻችንና አባ ገዳዎቻችን ትልቅ ዋጋ ነበራቸው፡፡ አሁን ይህን ነው ያጣነው፤›› ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አባተ ጌታሁን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ከዚህ በፊት እንደተባለው የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ሰርገኛ ጤፍ ነው፡፡ ልንለየው አንችልም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ጥያቄው ብዝኃነትንና አንድነትን አንዱ አንዱን ሳይጨፈልቅ እንዴት እንሥራ? የሚል ነው፤›› ብለው፣ ‹‹በዩኒቨርሲቲዎቻችን በትግሬና በአማራ ወይም በሌላ መቀላለድ የማይችልበት ጊዜ ደርሷል፡፡ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጩ ድርጊቶች አፍጥጠው እየመጡ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎቻችን መቻቻል በሚለው መርህ ላይ እየሠራን አይደለም፡፡ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎለብቱ እሴቶች ላይ እየሠራን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጡ አንድ መምህር ምሁራን እንደ ምሁርነታቸው የሚጠበቅባቸውን ሥራ በተገቢው ካለማከናወን፣ መንግሥትንም ቢሆን ባለመሞገት፣ እንዲሁም እንደ ተባለው ቃል አቀባይ በመሆን ችግሮች ሲፈጠሩ ዝምታ እንደ ተመረጠ ተናግረዋል፡፡ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች በኩታ ገጠም ይኖራሉ የሚለው የውይይት መነሻ ሐሳብ እንደማይሰማማቸው የገለጹት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያዊያን በተለይም ሁለቱ ሕዝቦች ከዚህም በላይ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር ታምራት በበኩላቸው፣ ‹‹ዩኒቨርሲቲዎች የዩኒቨርሳል እውቀት ማዕከል ቢሆኑም እየሠሩ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር የተቋማቱ አሠራርና አመለካከት ለዚህ የሚፈቅድ አይደለም፡፡ በቋንቋ መግባባት አልተቻለም፡፡ ሀብትን ለመቀራመት ሩጫ በዝቷል፡፡ ተቋማት ውስጥ የወንድማማችነት መንፈስ ባለመፍጠር ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡ ተቋማትን መፈተሽ ካልቻልን የሚመጣው ጉዳይ ከባድ ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት፣ ‹‹በነፃነት ማሰብና መናገር በዚህ አገር ያሳስራል፡፡ መንግሥት በሕጉና በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሥራት አለበት፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ላይ የአገሪቱ ምሁራን አንድ በመሆን ለአገሪቱ ለውጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና ምክረ ሐሳቦችንና የመፍትሔ ሐሳቦችን እንዲጠቁሙ መግባባት ተፈጥሯል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ምሁራን መካከል የሚደረገው ውይይት በቋሚነት መካሄድ እንዳለበት ስምምነት ተደርሷል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ምሁራንን የሚያገናኝና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን የሚያጠናክር ተቋም እንዲቋቋሙ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁንና የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በውይይቱ መጨረሻ ላይ እንደተናገሩት፣ የሁለቱን ክልሎች የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር ቋሚና ዘላቂ በሆነ መንገድ ለማካሄድ ሁለቱ መንግሥታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡ የምሁራን ውይይት ማካሄድም የዕርምጃው አንዱ ቀዳሚ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሕዝቦች መካከል ያለውን መስተጋብር በማዛባትና በማምታታት የተፈጠረውን ክፍተት ምሁራን በመሙላት የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክት ተላልፏል፡፡ ጊዜው ከማይፈቅደው መርህና አሠራር በመውጣት አንድነትንና ተባብሮ መሥራትን የሚሸረሽሩ ጉዳዮች በትክክለኛ መንገድ ተጠንተውና ተለይተው ለውይይት መቅረብ እንዳለባቸው ምሁራን አሳስበዋል፡፡

ትንንሽ ጉዳዮች እየተነቀሱና እየተቀለሙ የአብሮ መኖር እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸውን ምሁራኑ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሞና በአማራ ምሁራን የተጀመረው ኮንፈረንስ አድጎና ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ብሎ የአገሪቱን ችግር በመፍታት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዳለበት በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ ተገልጿል፡፡ የሁለቱን ክልሎች የምሁራን ውይይት በቀጣይ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ለማካሄድ ስምምነት ላይ በመድረስ ኮንፈረንሱ ተጠናቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -