Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአገር ውስጥ ለሚከናወኑ ግዥዎች ከውጭ መክፈል የሚቻልበት ሥርዓት ተዘረጋ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሆነው ለተለያዩ አገልግሎት ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉበት ‹‹መላ›› የተሰኘ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ሥራ ጀመረ፡፡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የስልክ፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የዕድር፣ የትምህርት ቤት፣ የሆስፒታል፣ የኢንሹራንስና ሌሎች የቤተሰቦቻቸውን የቤት ውስጥ ወጪዎችን ጭምር መክፈል የሚችሉበት ሥርዓት ሲሆን፣ ሥርዓቱን የዘረጉት ክፍያ ፋይናንሺያል ሰርቪስና ማስተር ካርድ በጥምረት ሆነው ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2010 የተቋቋመው ክፍያ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉን ወደ ዲጂታል ሥርዓት በመቀየር አገልግሎቱን የማቅረብ ሥራ ላይ ያተኮረ ኩባንያ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማስተር ካርድ በበኩሉ ማንኛውንም ዓይነት ክፍያ በዲጂታል ሥርዓት በማከናወን በ210 አገሮች ውስጥ ይህንኑ አገልግሎቱን እያቀረበ የሚገኝ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ተጠቃሚዎች በተዘረጋው የመላ ዲጂታል ሥርዓት መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ ክፍያዎችን የሚፈጽሙት በሚገለገሉባቸው የክሬዲትና ዴቢት ካርድ አማካይነት ይሆናል፡፡

በቅርቡ የዓለም ባንክ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት፣ እ.ኤ.አ በ2015 ከሰሃራ በታች ወዳሉ አገሮች በውጭ ከሚኖሩ ዳያስፖራውያን የተላከው ገንዘብ 36 ቢሊዮን  ዶላር ነበር፡፡ ከናይጄሪያ ቀጥላ ከፍተኛ የውጭ ሐዋላ የምትቀበል አገር ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በየዓመቱ ከሦስት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትልውደ ኢትዮጵያውያን እንደምታገኝ ተመዝግቧል፡፡ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚሆነው ግን መደበኛ ባልሆኑ መላኪያ መንገዶች የሚገባ ገንዘብ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ2020 500 ሚሊዮን የዓለም ሕዝብን የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚንቀሳቀሰው ማስተር ካርድ፣ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዕፎይታን እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለው አሠራር ባለመኖሩ ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ አገር ውስጥ ገንዘብ በመላክ ክፍያ መፈጸም ለዳያስፖራዎች አስቸጋሪ ነበር፡፡ በተለይም ወቅቱን ጠብቀው የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውኃና የስልክ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመፈጸም ስለሚቸገሩ አገልግሎቱ ይቋረጥባቸው እንደነበር በመግለጽ ያማርራሉ፡፡

‹‹ባህር ማዶ የሚኖሩ ዜጎች የመላን ዲጂታል ሥርዓት በመጠቀም ማንኛውንም ክፍያ በቀጥታ መክፈል ይችላሉ፡፡ ገንዘባቸውም በትክክል ለታሰበው ተግባር እንደሚውል ስለሚያውቁ ጭንቀት አይገባቸውም፤›› ያሉት የማስተር ካርድ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምሥራቅ አፍሪካ የቀጣናው የማስተር ካርድ አገልግሎት ኃላፊ ክሪስ ዋኪራ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሦስት ሚሊዮን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ገንዘብ በመላክ ቤተሰቦቻቸውን ይረዳሉ፡፡ ነገር ግን ገንዘብ የሚልኩበት የሐዋላ ሥርዓት ዋጋው ውድና ከዚህ ውጪ ባለው መንገድ ሲልኩም፣ የሚልኩት ገንዘብ ለታሰበው ዓላማ መዋል አለመዋሉን የሚያውቁበት መንገድ ባለመኖሩ ይቸገሩ እንደነበር ፕሮግራሙ ይፋ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

አገልግሎቱ የሚጀመረው በርካታ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩባት በሚነገረው አሜሪካ ሲሆን፣ ወደፊት በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪካውያን እንዲጠቀሙበት ተደርጎ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ዕቅድ ተይዟል፡፡ መላ በሞባይል ስልክም መሥራት እንዲችል ተደርጎ የተዘጋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው፡፡

ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ያደረገው ማስተር ካርድ፣ ከተቋቋመ 50 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የባንክ ኦፍ አሜሪካ ተወዳዳሪ እንዲሆን ታስቦ የተቋቋመው በካሊፎርኒያ በሚገኙ ባንኮች ኅብረት አማካይነት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1966 እስከ 1979 ‹‹ኢንቴር ባንክ›› እና ‹‹ማስተር ቻርጅ›› የሚል ስያሜ በማንገብ ይንቀሰቀስ ነበር፡፡ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻዎችን የክፍያ ሒደቶች የማቀላጠፍ ሥራ በመሥራት የሚታወቀው ማስተር ካርድ፣ በተለይ በክፍያ ካርዶች አገልግሎቶቹ በመላው ዓለም ዕውቅና ያለው ነው፡፡

ክፍያ ፋይናንሺያል ሰርቪስ በበኩሉ በኢትዮጵያ በተለይ ክፍያ ለሁሉ በሚል ስያሜ የኤሌክትሪክ ኃይል ወርኃዊ ክፍያዎችን፣ የውኃ ፍጆታዎችን፣ የትራፊክ ቅጣትና የመንጃ ፈቃድ ክፍያዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የክፍያ ሒደቶችን በመረከብ በዲጂታል ሥርዓት እያስተናገደ የሚገኝ አገር በቀል ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች