Saturday, June 22, 2024

የመንግሥት ባለሥልጣናትና መዋቅሮች ቶሎ ቶሎ መለዋወጥ ችግር እየፈጠረ ነው!

መንግሥት ባለሥልጣናትንና መዋቅሮቹን በተጠና መንገድ መለዋወጥ፣ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነቡ ተቋማትን መፍጠር፣ አቅምና ብቃት ያላቸውን ተሿሚዎች ኃላፊነት መስጠት አንደኛው ኃላፊነቱ ነው፡፡ የሕዝብን ፍላጎት የሚያረኩ ተቋማትና ተሿሚዎችን ማግኘት የሚቻለው ግን በቂ ጊዜ ተሰጥቶ በሚገባ ጥናት ሲደረግ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የተጠና አካሄድ የተረጋጋና የሰከነ መንግሥት ለመመሥረት ከማስቻሉም በላይ፣ ዕቅዶችና አፈጻጸሞች በስኬት እንዲከናወኑ ይረዳል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት የተለያዩ መዋቅሮችና በኃላፊዎቻቸው ላይ በተደጋጋሚ ለውጦች እየተደረጉ በመሆናቸው፣ በተገልጋዩ ሕዝብም ሆነ በባለድርሻ አካላት ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው፡፡

በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ ተደጋጋሚ መልሶ የማዋቀርና እንደገና የማፍረስ ሥራዎች ተካሂደዋል፡፡ የተለያዩ ሚኒስትሮችም ከአንዱ ወደ ሌላው በፍጥነት ተዘዋውረዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ አንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በሥሩ ከሚገኙ የተለያዩ ኤጀንሲዎች ጋር ግንኙነት ባላቸው ባለድርሻ አካላት ላይ ቅሬታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት ሚኒስቴር በሥሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ወዘተ. የመሳሰሉ ትልልቅ ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ በሥራቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሰፊ የትራንስፖርት ሴክተር ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት፣ ሴክተሩን የበለጠ ለማዘመንና ለማሳደግ የተረጋጋ አመራር መኖር አለበት፡፡ ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም ባሉት ሒደቶች ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታትና የተሻለ ውጤት ማግኘት የሚቻለው በተጠና መንገድ መሾምና ማዋቀር ሲቻል ብቻ ነው፡፡

መንግሥት አንድ ባለሥልጣንን ወይም ተሿሚን ለአንድ ኃላፊነት ሲያጭ በሚገባ ጥናት ማካሄድ አለበት፡፡ ለኃላፊነቱ ትክክለኛውን ሰው ለማግኘት በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ ደግሞ ደጋግሞ አውጥቶ ካወረደ በኋላ መሾም ይኖርበታል፡፡ ለሚኒስትርነት፣ ለኮሚሽነርነት፣ ለዋና ዳይሬክተርነት ወይም ለሥራ አስኪያጅነት ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ከሰጠ በኋላ፣ ለተሿሚው ሙሉ ኃላፊነትና ነፃነት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አንድ ተሿሚ የተቋሙን ማኔጅመንት በነፃነት እንዲመራ ዕድሉን ማግኘት አለበት፡፡ ተሿሚው የሚመራውን ተቋም ተቆጣጥሮ በነፃነት መሥራት መቻሉን ካላረጋገጠ ኃላፊነቱን መወጣት አይችልም፡፡ አንድ ተሿሚ ሲመጣ የራሱን ዕቅድና ድርጅቱን የሚመራበት መርሐ ግብር ይቀርፃል፡፡ ይህንን ተግባራዊ የሚያደርግበት በቂ ጊዜ ማግኘትም አለበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ በብዛት እየታየ ያለው ሥራውን አውቆ፣ ዕቅዱን ነድፎና መርሐ ግብሩን ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ሳይጀምር በድንገት ይነሳል፡፡ በቦታው ሌላ ተሿሚ ይመጣና እንደገና አዲስ ዕቅድ ይነድፋል፡፡ ይኼኛውም በስንት መከራ ዘርፉን ተለማምዶ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ሲነሳ በሌላ ተሿሚ ይተካል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተደጋጋሚ የሹም ሽርና መልሶ የማደራጀት ተግባር በተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ላይ በመካሄዱ በርካታ ተገልጋዮችን ተስፋ እያስቆረጠ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ያለመረጋጋት በአገሪቱ ላይ የሚያደርሰው ችግርም መጤን አለበት፡፡ በዓለም ላይ ኪሳራ የሚያስመዘግቡ የፋይናንስ ተቋማት፣ አየር መንገዶች፣ የንግድ ድርጅቶች፣ አምራቾችና የመሳሰሉት ዋነኛው ችግራቸው የተረጋጋ አመራር ማጣት ነው፡፡ በተጠና መንገድ መሪዎቻቸውን ያገኙ ተቋማት ግን ከዓመት ዓመት በትርፍ ይንበሸበሻሉ፣ ማስፋፊያ ያካሂዳሉ፣ ለበለጠ ውጤት ይተጋሉ፡፡

ብዙ ጊዜ በአግባቡ ካለማቀድና ከዝቅተኛ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የኤክስፖርት ገቢ በየጊዜው ሲቀንስ፣ የኢንዱስትሪና የግብርና ውጤቶች በቂ ገበያ ሲያጡ፣ የአገሪቱ የትራንስፖርት ሲስተም በሚፈለገው ደረጃ ማደግ ሲያቅተው፣ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡ ማሳሰቢያዎች፣ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ትኩረት ሲነፈጋቸው፣ በትምህርት ጥራት ላይ የሚነሳው የዓመታት ችግር ሳይፈታ፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የፍትሕ ችግሮች መቀረፍ ሲያቅታቸው፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ አሳሳቢ ችግሮች በነበሩበት ሲቀጥሉ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የአገር ራስ ምታት ሆነው ሲዘልቁ፣ ወዘተ. ሹማምንቱን ያለ ጥናት ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስና ተቋማቱን በተደጋጋሚ መላልሶ ማደራጀት ፋይዳው ምንድነው? ለአማካሪነት የተመደቡ የሥራ መደቦች አያስፈልጉም ተብሎ አስተባባሪ የሚባሉ ሹመቶች ሲፈጠሩም እየታየ ነው፡፡ በቂ ጊዜ ያልተሰጣቸውና ጥናት ያልተደረገባቸው ተግባራት እየበዙ ነው፡፡ ይታረሙ፡፡

በተለያዩ ዘርፎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳይ ያላቸው ዜጎችና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያፈሰሱ ኩባንያዎች፣ በተቋማትና በሹማምንት ቶሎ ቶሎ መለዋወጥ ምክንያት እየተጎዱ መሆናቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች እየገለጹ ነው፡፡ በተለይ በርካታ ዘርፎችን የሚመሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ቶሎ ቶሎ ሲለዋወጡ የበሰለው ጉዳይ ጥሬ እየሆነባቸው እየተቸገሩ ያሉም ብዙ ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ኩርፊያና መነጫነጭ በየቦታው ይሰማል፡፡ የተቋማት መዋቅር በየጊዜው እየተሠራ ቶሎ ቶሎ ለውጥ ሲደረግበት የአገር ሀብትም ይባክናል፡፡ አንዱን ከሌላው ጋር በማዋሀድ ወይም በማለያየት የሚባክነው የአገር ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ ለብዙ ተግባራት ሊውል የሚችልም የሠለጠነ የሰው ኃይል ነው፡፡ በየተቋማቱ በጥናት ላይ የተመሠረተ ለውጥና ማሻሻያ ማድረግ ጠቃሚነቱ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣናቱንና መዋቅሮቹን ያለ ጥናት ቶሎ ቶሎ መለዋወጥ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መሆኑ መታወቅ አለበት!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...