Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት

በዩኔስኮ የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት

ቀን:

የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸር ኦፍ ሒውማኒቲ) መስፈሩ ይፋ የተደረገው ዕሮብ ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ከሰዓት ነበር፡፡ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደው አሥራ አንደኛው የዩኔስኮ ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅ) ጉባኤ በቅርስነት እንዲመዘገቡ ጥያቄ ከቀረበባቸው ቅርሶች ገዳ አንዱ ነበር፡፡

መመዝገቡ በታወቀበት ቅጽበት በርካቶች ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ አባ ገዳዎች፣ ሥርዓቱን አጥንተው ለዩኔስኮ ያቀረቡ ተመራማሪዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎችና ሌሎችም በአዳራሹ የተገኙ ግለሰቦች እየተቃቀፉ፣ እየዘፈኑና የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለቡ ሀሴታቸውን አሳይተዋል፡፡ በዕለቱ ከገዳ ሥርዓት በፊት አሥር ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች በዩኔስኮ መዝገብ ቢሰፍሩም፣ የገዳ መመዝገብ ልዩ ድባብ ፈጥሯል፡፡

የገዳ ሥርዓትን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት የተጀመረው ሰኔ 2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሚካተቱት እንደ ኢሬቻ፣ ጉዲፈቻ፣ ዋቄፈና ሲንቄ ያሉትን ሥርዓቶች የሚገልጽ ጥናት፣ ፊልምና ፎቶግራፎች ከኦሮሚያ ክልል ማለትም ከቦረና፣ ጉጂ፣ ምሥራቅ ሸዋ ከረዩ፣ ምዕራብ ሐረርጌ ቦዳ ቡልቱ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ወሊሶ፣ አምቦና ወለጋ ተሰባስቦ ለተቋሙ ቀርቧል፡፡ በዩኔስኮ ኮንቬንሽን ድንጋጌዎች መሠረት የተመዘነው ሥርዓቱ፣ ከመጽደቁ አስቀድሞ ቅርሱ ስለሚጠበቅበት እንዲሁም ከትውልድ ወደ ትውልድ ስለሚተላለፍበት ከ24 አገሮች የተውጣጣው ገምጋሚ ኮሚቴ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኮንቬንሽኑ ድንጋጌ የሚያስቀምጠው አምስት መሥፈርቶችን ነው፡፡ የመጀመርያው የቅርሱን ግዙፍነት ማረጋገጥና የቅርሱ ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ በሥርዓቱ ያለው ተሳትፎ ላይ ያተኩራል፡፡ ማኅበረሰቡ በሥርዓቱ ትግበራ አንዳች ሚና ከመጫወቱ ባለፈ፣ ቅርሱ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍበት መንገድም ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ቅርሱ ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር መካተቱ ከማኅበረሰቡ አልፎ ለዓለም ያለው ጠቀሜታ እንዲሁም የሰው ልጆች ወካይነቱ ይታያል፡፡

ቅርሱ እንዲመዘገብ ጥያቄ ሲቀርብ፣ ደኅንነቱን ለመጠበቅ ስለሚወሰዱ ዕርምጃዎች መግለጽ ሦስተኛው መስፈርት ሲሆን፣ የይመዝገብልን ጥያቄው የማኅበረሰቡ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ ማቅረብ አራተኛው ነው፡፡ በአምስተኛነት የቅርሱ ባለቤት የሆነው አገር፣ በአገራዊ ደረጃ ቅርሱን መዝግቦ ዕውቅና የመስጠቱ ጉዳይ ነው፡፡

የገዳ ሥርዓት በነዚህ መሥፈርቶች ተመዝኖ በኮሚቴ አባላቱ ሙሉ ድምፅ ከማግኝት በፊት፣ ከቅርሱ ጥበቃ ጋር የተያያዘ ማሻሻያ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡ የገዳ ሥርዓት ግዙፍነት የሌለው ባህላዊ ቅርስ ቢሆንም፣ ሥርዓቱን ለማካሄድ ግዙፍነት ያላችው ቅርሶች ያስፈልጋሉ፡፡ በሥርዓቱ እንደ ኦዳ ዛፍ ያሉ ተፈጥሯዊና ሌሎችም ሰው ሠራሽ ቁሳቁሶች ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ እነዚህን ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች መጠበቅ ደግሞ በቀጥታ ሥርዓቱን ከመጠበቅ ጋር ይያያዛል፡፡ ቅርሱን ለመጠባበቅ መንግሥት ከሚተገብራቸው ሕግጋት ጎን ለጎን ማኅበረሰቡም የራሱ መንገዶች እንዳሉት በማሻሻያው ተመልክቷል፡፡

ስለ ቅርስ ጥናትና አጠባበቅ ከወጣው አዋጅ ቁጥር 209/2000 በተጨማሪ ማኅበረሰቡም ቅርሱን የሚጠብቅባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ የኦዳ ቡልቱ አባ ገዳ የሆኑት አህመድ ሰኢድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በገዳ ውስጥ ፉዱለማ በመባል የሚታወቀው ሥርዓት በተከለለ አካባቢ ያሉ ዕፅዋትና እንስሳት ደኅንነት የሚጠበቅበት ነው፡፡ ‹‹የሚያድግ ልጅና እንጨት አይነካም ይባላል፤›› የሚሉት አባ ገዳው፣ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ቅርሱ የሚጠበቅባቸው መንገዶች እንዳሉ ይናራሉ፡፡ እነዚህ መንገዶች በቂ እንደሆኑ ያመኑት የዩኔስኮ የግምገማ ኮሚቴ አባላትም  መመዝገቡን አፅድቀዋል፡፡ ልዩ ልዩ ባህላዊ ክንውኖች የሚካሄዱባቸው ቦታዎች ጥበቃ በማኅበረሰቡ ካለው ባህላዊ ሕግ (ከስተመሪ ሎው) በተጨማሪ መንግሥትም ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

በኦሮሞ ማኅበረሰብ የሚተገበረው ገዳ የማኅበረሰቡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ይመራበታል፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የገዳ ሥርዓትን በዓለም አቀፍ ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች ለማስመዝገብ የተቋቋመ የጥናት ቡደን አስተባባሪና የባህል አንትሮፖሎጂስት አቶ ገዛኸኝ ግርማ፣ ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ገዳ ብዙ ፍቺዎች ያሉት ሲሆን፣ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ከአንድ በላይ ፅንሰ ሐሳቦች ይወክላል፡፡ ገዳ የጊዜና የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ነው፡፡ በገዳ ሥርዓት የስድስተኛው እርከን መጠሪያም ነው፡፡ ገዳ አገር በቀል ዕውቀትን አካቶ የያዘ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ እንደ ዘመናዊ የመንግሥት መዋቅር የራሱ አደረጃጀት ያለው ሕግ አውጪው አካል ጨፌ፣ ሕግ አስፈጻሚ አባ ገዳና ሕግ ተርጓሚም አለ፡፡ ሥርዓቱ የፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያስተናግዱ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በውስጡ ያካተቱ ተቋማት አሉት፡፡ ከነዚህ መካከል ጉማ (ካሳ) በመክፈል የሚደረግ ዕርቅ ነው፡፡ የሞጋሳ ሥርዓት በራሱ ሙሉ ፍላጎትና ውዴታ ከኦሮሞ መቀላቀል የሚፈልግ ግለሰብም ሆነ ቡድን መብት የሚያገኝበት ሥርዓት ነው፡፡

ሲንቄ መብት ለማስከበር ይሠራል፡፡ ሲንቄ ቀጭን በትር ሲሆን፣ ለአንዲት ኦሮሞ ሴት በጋብቻ ዕለት በወላጅ እናቷ ይሰጣታል፡፡ ሲንቄ የሴቶች መብት ማስከበሪያ መሳሪያ ሲሆን፣ ሴቶች የመብት ጥሰት ቢፈጸምባቸው ሲንቄያቸውን ይዘው በመቃወም ፍትሕ ያገኙበታል፡፡ ሌላው የኢሬቻ ክብረ በዓል ማኅበረሰቡ ለፈጣሪ (ዋቃ) በዓመት ሁለቴ ምሥጋና የሚያቀርቡበት ነው፡፡

አባ ገዳው ሻሚል፣ ገዳ በተለይም በዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ረገድ ጥንታዊ ሥልጣኔን ያሳያል ይላሉ፡፡ በሥርዓቱ ከሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጎን ለጎን፣ አንድ ሰው ሥልጣን ከለቀቀ የተረካቢው አማካሪ እንጂ ተቀናቃኝ አይሆንም፡፡ በየስምንት ዓመት ልዩነት ሥልጣን የሚይዝ ሰው በሥልጣን ዘመኑ ማሳካት ያልቻለውን ነገር ተከታዩ ከግብ እንዲያደርስ ነግሮና መርቆ ሥልጣን ያስረክባል፡፡ በገዳ ከሕፃናት እስከ አዋቂዎች በዕድሜ እርከን ተከፋፍለው ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ‹‹ገዳ ከዘመናት በፊት ይተገበር ከነበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አንስቶ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ተምሳሌት መሆን የሚችል ሥርዓት በመሆኑ በዩኔስኮ በመመዝገቡ የተሰማኝን ደስታ መግለጽ አልችልም፤›› ሲሉ ነበር አባ ገዳው የተናገሩት፡፡

በገዳ መመዝገብ ከየአቅጣጫው የደስታ መግለጫዎች እየተደመጡ ቢሆንም፣ ቅርሶችን በዩኔስኮ መመዝገባቸው ምን ጠቀሜታ አለው? የሚለው ጥያቄም ይሰነዘራል፡፡ የዩኔስኮ ኮንቬንሽን እንደሚያትተው፣ አንድ ግዙፍነት የሌለው ባህላዊ ቅርስ የሚያስመዘግብ አገር ለቅርሱ ጥበቃ ከማድረግ በተጨማሪ ቅርሱን የተመለከቱ ጥናትና ምርምሮች እንዲደረጉ የማበረታታት ኃላፊነትም አለበት፡፡

ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች ረገድ የቅርሱ ቀጣይነት የማኅበረሰቡን መኖር የተመረኮዘ ነው፡፡ ስለዚህም የዩኔስኮ ኃላፊነት አንድ ማኅበረሰብ ባህላዊ ቅርሶቹን የሚተገብርበትን መንገድ መጠበቅ ነው፡፡ በሰው ሠራሽ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ቅርሱ አደጋ ቢያንዣብብበት፣ ዩኔስኮ ለቅርሱ የገንዘብና ሙያዊም እገዛ ያደርጋል፡፡

የቱለማና ኦሮሚያ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ሮቢ፣ ‹‹ ገዳ በዩኔስኮ ተመዘገበ ብሎ እጅ አጣጥፎ መቀመጥ ሳይሆን ጥናትና ምርምር በመሥራት ለቀጣዩ ትውልድ ስለሚተላለፍበት መንገድ መታሰብ አለበት፡፡ ጎብኚዎች መጥተው እንዲመለከቱት ማድረግም ያስፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡ ሥርዓቱ ዓለም ዛሬ ከሚገኝበት ደረጃ በዘመናት ቀድሞ ማኅበረሰቡ የሚተዳደርበት መሆኑን ትኩረት ሳቢ እንደሆነ ያክላሉ፡፡

በገዳ ሥርዓት አንድ ሰው ሥልጣን ሲሰጠው ያለውን ኃላፊነት ለማመልከት የሚከተሉትን ሥርዓቶች ይከተላል፡፡ መጀመርያ በሥልጣን ዘመኑ ጥሩና መጥፎ እንደሚመጣ ለማመልከት ከርቤ ይቀምሳል፡፡ በምግባር እንደ ማር ጣፍጥ ለማለት ማር፣ እንደ እርጎ ሁን ለማለት ወተትና አገር ስለሰጠኽን ሁሉንም እኩል እያየህ አስተዳድር ለማለት ፈረስ ይሰጠዋል፡፡ እነዚህና ሌሎችም ተምሳሌታዊ ክንውኖች ያሉት የገዳ ሥርዓት፣ አሁን አገሪቱ እየተዳደረችበት ላለው ሥርዓት መሠረት መሆን እንደሚችል አባ ገዳው ይገልጻሉ፡፡ ገዳ አገሪቱ እየተዳደረችበት ካለው ሥርዓት ጎን ለጎን መሄድ የሚችል እንዲያውም ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡

የሥርዓቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ትምህርት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ሥርዓቱ በሃይማኖት፣ በጾታ፣ በጎሳና በማንኛውም መሥፈርት እኩልነትን የሚያበረታታ በመሆኑ ከኦሮሚያ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ቢስፋፋ መልካም ነው፡፡

አባ ገዳው ባለፉት ስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው የገዳ ሥርዓት የተዳከመባቸው አካባቢዎች ሥርዓቱን ዳግም ለማስረጽ እንደሠሩ ይናገራሉ፡፡ በኢሉአባቦራና ሐረርጌ አካባቢ ሥርዓቱ እንዲያንሰራራ ከተደረጉት ሙከራዎች በተጨማሪ ገዳ አሁንም በቦረና፣ በጉጂ፣ በሸዋ ቱለማና በመጫ እየተተገበረ ነው፡፡

የጉጂ አባ ገዳ ጂሎ ማኖም በአባ ገዳዎቹ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ አንድ ሰው ቢያጠፋ እንኳን ቤተሰቦቹ ላይ በበቀል ማንም ጉዳት እንዳያደርስ መጠበቅና እርቀ ሰላም እንዲያወርድ ማድረግ ለማኅበራዊ መስተጋብር ያለውን አስተዋጽኦ ይገልጻሉ፡፡ እርስ በርስ በመተባበር (ደቦ) መሥራትና ሌሎችም ሥርዓቶችን የዓለም ሕዝብ እንዲያውቃቸው ለማድረግ በዩኔስኮ መመዝገቡ እንደሚረዳም ያምናሉ፡፡

ከዚህ ቀደም የገዳ ሥርዓት አሁን በተመዘገበበት ሳይሆን ማስተርፒስ ይባል በነበረው የዩኔስኮ መዝገብ ለማስፈር ጥረት ተደርጎ አለመሳካቱ ይታወሳል፡፡ እንደ አንትሮፖሎጂስቱ አቶ ገዛኸኝ፣ በ1990ዎቹ መግቢያ የቀረበው ፋይል ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም፡፡ ቅርሱን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን አያሟላም ነበር፡፡ ማስተርፒስ የሚባለው ስያሜ ቀርቶ የዓለም ወካይ ቅርስ በሚል ተተክቶ 1995 ዓ.ም. ኮንቬንሽኑ ወጥቷል፡፡ በዚህ መዝገብ ኢትዮጵያ ከገዳ ሥርዓት በተጨማሪ የመስቀል በዓልንና ፊቼ ጨምበላላን አስመዝግባለች፡፡

‹‹ዘ አሊያንስ ኦፍ ናይሎቲክ ኤንድ ኦሞቲክ ፒፕል ኦፍ አፍሪካ›› በሚል የሚጠራ  ቡድን ዩኔስኮ ገዳን እንዳይመዘግበው ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ በአንትሮፖሎጂስቱ ገለጻ፣ ቡድኑ ለዩኔስኮ ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል ሥርዓቱ የኦሮሞ ብሔር ብቻ ሳይሆን፣ ኬንያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ጎሳዎችም ጭምር መሆኑና ለሴቶች መብት የማይሰጥ መሆኑ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ለዩኔስኮ የተሰጠው ምላሽ፣ እንደ ማሳይ ያሉ የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች ያላቸው ሥርዓት የዕድሜ እርከን እንደሆነ ያትታል፡፡ በአንፃሩ ገዳ በትውልድ ቅደም ተከተል ላይ በመመሥረት በአምስት መደቦች በመከፋፈል በእያንዳንዱ መደብ በየስምንት ዓመቱ የሚከናወን የሥልጣን ርክክብ አለው፡፡ በሴቶች መብት በኩል የሲንቄ ሥርዓት ያለው ሚና ይጠቀሳል፡፡

ገዳ ግዙፍነት በሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች በተመዘገበበት ዕለት የቤልጄም የቢራ አጠማመቅ እንዲሁም የማኅበረሰቡ ቢራን ያማከለ የዕለት ተዕለት ሕይወት የቢራ ባህል በሚል ተመዝግቧል፡፡ ከአፍሪካ ባህል ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለውና ሙዚቃና ዳንስን ያማከለው የኩባው ሩምባና፣ ታህቲብ በመባል የሚታወቀው የግብፅ ባህላዊ ጨዋታም በመዝገቡ ሰፍረዋል፡፡ ጉባኤው ካፀደቃቸው ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች በተጨማሪ፣ አደጋ ያንዣበበባቸው ቅርሶችና በቅርስ ጥበቃ ተምሳሌት የሚሆኑ ቅርሶች ምዝገባ ላይም ውሳኔ አሳልፏል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...