የዓመቱ የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በክረምቱ ወራት ክለቦች ሲዘጋጁ ቆይተዋል፡፡ በርካታ ተጨዋቾች በሚሊዮን ብሮች ተዘዋውረዋል፡፡ ከክለብ ክለብ የተደረጉ ሽያጮች፣ የአዳዲስ አሠልጣኞች ሹመት፣ የነባሮች ስንብትና ሌሎችም ሲካሄዱ የቆዩ የፕሪሚየር ሊጉ ክንውኖች ናቸው፡፡
ሁሉም ክለቦች በየፊናቸው ሲያደርጉት የነበረውን ዝግጅት አጠናቀው መደበኛውን ውድድር ማከናወን ጀምረዋል፡፡ ይሁንና የበርካቶቹ ክለቦች የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ ግን ዝግጅታቸው ምን ይመስል እንደነበር የሚጠቁም ነው፡፡ አብዛኞቹ ከጅምሩ ተዳክመው የታዩበት በጣት የሚቆጠሩ ክለቦች ደግሞ ከወዲሁ አስፈሪ የሆኑበት እንቅስቃሴ እየታዩም ይገኛል፡፡
በተጨዋቾች አመላመል፣ በተጨዋቾች የሜዳ ውስጥ እንቅስቃሴ፣ ብቃትና የመሳሰሉትን ጨምሮ የአሠልጣኞች አንብቦ የማስተካከል፣ በተቃራኒ ቡድን ላይ ብልጫ የመያዝና ሌሎችንም ነጥቦች መነሻ በማድረግ የሊጉ የተፎካካሪነት አቅም ሲታይ፣ ክለቦች የሚያሳዩት የብቃት ልዩነት የዓመቱ መርሐ ግብር ከግማሽ መንገድ ሳይደርስ እንዳይጠናቀቅ ሥጋት የጫረባቸው በርካቶች ሆነዋል፡፡
የአገሪቱ እግር ኳስ በተለያዩ የውድድር ይዘት (ፎርማት) እስከ 1990 ዓ.ም. ድረስ በተለያየ መልኩ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከ28 ዓመት በኋላ ግን አሁን ድረስ ሲጠራበት የቆየውን ‹‹ፕሪሚየር ሊግ›› የውድድር ይዘት ይዞ ቆይቷል፡፡ አገሪቱ የምትከተለውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተከትሎ በተዟዙሮ ሲከናወን የቆየውን ይህንኑ የውድድር ይዘት ለእግር ኳስ ዕድገት የማይበጅ መሆኑን በመጥቀስ አንዳንዶች ይከራከራሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ለእግር ኳሱ ውድቀት ችግሩ የውድድሩ ይዘት ሳይሆን እግር ኳስ በተለይ በአሁኑ ወቅት ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ሊሰጠው የሚገባው ትኩረት ማነስ መሆኑን የሚገልጹ አሉ፡፡ ለአብነትም ለአገሪቱ እግር ኳስ መነሻነት የሚጠቀሱት እንደ አዲስ አበባ የመሳሰሉ ከተሞች ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው የሚከናወኑ መሠረተ ልማቶች ስፖርቱን ያማከሉ አለመሆናቸው በዋናነት ተጠቃሽ እንደሆነ በማሳያነት የሚያቀርቡም አሉ፡፡
ከ1980ዎቹ ጀምሮ የእግር ኳስ ጨዋታ በሚከናወንባቸው ቦታዎች ሁሉ እንደማይጠፋ ይናገራሉ፡፡ አቶ ርስቱ ተሰማ በክለብ ደረጃ በቀድሞ መጠሪያው የመብራት ኃይል ደጋፊ እንደነበሩም ያስረዳሉ፡፡ መብራት ኃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በእግር ኳሱ የነበረውን አቋም እንኳ ማቆየት ባለመቻሉ ምክንያት ደጋፊነታቸውን ትተው ተመልካች በመሆን መዝለቃቸውን ይናገራሉ፡፡ እንደ አቶ ርስቱ አሁን አሁን የቀድሞ ክለባቸው ደጋፊዎችን ጨምሮ ሰዎች ስለፕሪሚየር ሊጉ ሲከራከሩ በሚሰሙበት ሰዓት እንደሚገረሙም ያስረዳሉ፡፡ አስተያየት ሰጪው ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተመሠረተበት ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ሆኖ የዘለቀበትን የውድድር ሒደት ይጠቅሳሉ፡፡
ሁለት አሠርታትን ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ1990 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ዋንጫ ያነሳው የቀድሞው መብራት ኃይል የአሁኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲሆን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ባደገበት በ1991 ዓ.ም. እና በ1992 ዓ.ም. አከታትሎ ወስዷል፡፡ በ1993 ዓ.ም. ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሳ፣ በ1994 እና 1995 ዓ.ም. ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ አከታትሎ በመውሰድ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡
በ1996 ዓ.ም. ሐዋሳ ከተማ ሲወሰድ፣ 1997 እና 1998 ዓ.ም. አሁንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወስዷል፡፡ በ1999 ዓ.ም. በክለቦችና በፌዴሬሽኑ መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የአዲስ አበባ ክለቦች ባልተሳተፉበት ሐዋሳ ከተማ ለሁለተኛ ጊዜ የዋንጫው ባለቤት የሆነበትን ታሪክ አስመዝግቧል፡፡ ሲቀጥል ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2000፣ በ2001 እና በ2002 ዓ.ም. ሦስት ጊዜ አከታትሎ በመውሰድ ዋንጫውን የግሉ አድርጓል፡፡ በ2003 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ቡና ሲወስድ፣ በ2004 ዓ.ም. እንደገና ቅዱስ ጊዮርጊስ ወሰዷል፡፡ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ ደደቢት የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ማለትም በ2006፣ በ2007፣ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም. ለአራት ተከታታይ ዓመታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለ ተቀናቃኝ ሻምፒዮን መሆኑን አስጠብቆ ቆይቷል፡፡
የዘንድሮው መርሐ ግብር አጀማመርን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪው፣ የቅዱስ ጊዮርጊስና ሌሎች ቡድኖች በሜዳ ላይ በሚያሳዩት ወቅታዊ እንቅስቃሴ ልዩነት ከወዲሁ እየታዩ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡