Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለዘረ መል ጥጥ የታጩ ማሳዎች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም የግብርና ዘርፍ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ በግዙፉ የሚጠቀሰው የአረንጓዴው አብዮት እየተባለ የሚጠራው ወቅት ነው፡፡ በርካቶች ከረሃብና ቸነፈር ለመዳን የቻሉበትን የሳይንስ ውጤት የተገበረው ይህ አብዮት በግብርና መስክ አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድም ይታወሳል፡፡

የአረንጓዴው አብዮት ተቋዳሽ ከነበሩ አገሮች መካከል በተለይ በደቡብ አሜሪካና በእስያ የሚገኙ አገሮች በርካታ ሕዝቦቻቸውን ከድርቅ አደጋ ለመታደግ በቅተዋል፡፡ ህንድና ሜክሲኮ በአረንጓዴው አብዮት ብዙ አትርፈዋል፡፡ ለሕዝባቸው የዕለት ቀለብ ለመስፈር ከመቻል ተርፈረው እህል ለመላክ የሚችሉበት አቅም እንዲያገኙ በሩን የከፈተው ይኸው አብዮት በብዙ ፈርጁ ሲወደስ ቆይቷል፡፡

የአረንጓዴው አብዮት አባት እየተባሉ የሚጠቀሱት አሜሪካዊው ምሁር ዶ/ር ኖርማን ቦርሎግም ለቴክኖሎጂው መስፋፋት በብዙ ስማቸው ይነሳል፡፡ ይዘከራል፡፡ ይህ አብዮት ለአብዮትነት እንዲፈረጅ ካበቁት መካከል በግብርናና በእርሻ ሥራዎች ላይ የሚተገበሩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማስተዋወቁ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በልማድ ይሠራባቸው የነበሩትን ዘደዎች በመቀየር፣ በላቦራቶሩ የተሻሻሉ፣ ከፍተኛ ውጤት የሚሰጡ ልዩ ልዩ የሰበል ዝርያዎችን በማውጣት ለአምራቾች ማዳረስ አንዱ የአብዮቱ ተልዕኮ ነበር፡፡

የተዘራው ዘር አረም እንዳይወርሰው፣ ተባይ እንዳይጨርሰውም ፀረ አረምና ተባይ መከላከያዎችን መርጨት እየተዘወተረ የመጣው በአብዛኛው ከአረንጓዴው አብዮት በኋላ ነበር፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የዘረ መል ምህንድስናን (ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝምስ) በመተግበር ሲሠራበት ቆይቷል፡፡

ምንም አንኳ በበርካቶች አገሮች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት ውጤት ቢታይበትም የዚያኑ ያህል ሲተች ቆይቷል፡፡ አረንጓደው አብዮት የጥቅሙን ያህል ጉዳቱም በርካታ ነው ተብሎ ሲወገዝ ኖሯል፡፡ በርካታ ለም መሬቶች መዳበሪያ ከመለዱ በኋላ ያለማዳበሪያ ምርት አልሰጥ ብለዋል ከሚለው ጀምሮ፣ የአፈር አሲዳማነትን አምጥቷል፣ የከባቢ አየርን ጤንነት አዛብቷል፣ መርዛማ ኬሚካሎችን አበራክቷል ወዘተ. የሚሉ ውንጀላዎች ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ 

ይህም ቢባል ግን እንደ ህንድ ባሉ አገሮች ውስጥ ከስድስት ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ በረሃብ ከመርገፍ ታድጓል ብለው የሚሞግቱለት ባለሙያዎችም አሉ፡፡ ጠቀሜታው በርካታ ስለመሆኑ ከሚገልጹት መካከል የደቡባዊና ምስራቃዊ አፍሪካ የጋራ ንግድ ተቋም (ኮሜሳ) ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ጌታቸው በላይ አንዱ ናቸው፡፡

አረንጓዴው አብዮት በእስያም ሆነ በደቡብ አሜሪካ ያደረገውን አስተዋጽዖና ያስገኘውን ውጤት ያህል በአፍሪካ  ምንም ሊያስገኝ አልቻለም፣ በአፍሪካ ተሞክሮ ከሽፏል የሚለውን ስሞታ ዶ/ር ጌታቸው አይቀበሉትም እንደውም በተገላቢጦቹ ለቴክኖሎጂው አፍሪካ ዝግጁ አልነበረችም የሚል የመልስ ምት ያቀርባሉ፡፡

ይህ አብዮት በአፍሪካ ተሳካም አልተሳካ ከዓመታት በኋላ ሌላኛውን የቴክኖሎጂ ውጤት አስከትሏል፡፡ መነጋገሪያ ከሆነም ሁለት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ከአረንጓዴው አብዮት በባሰ ሁኔታ ክርክርና ንትርክ አስነስቷል፡፡ የዘረመል ምህንድስና፡፡

አፍሪካውያን ለዘረመል ምህንድስና ፊታቸውን ኡዙረው ቆይተዋል፡፡ እንደውም ጠበቅ ያሉ ሕጎችን በማውጣት ጭምር ቴክኖሎጂው እንዳሻው እንዳይስፋፋ ሲከላከሉ ቆይተዋል፡፡ ነገሮች ግን እንዲህ እንደሆኑ የሚቀጥሉ አይመስሉም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየ እንዳለው ከሆነ ሕጎቻቸውን በማሻሻል የዘረ መል ምህንድስናን ለመቀበልና ለመተግበር የፈቀዱ አገሮች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡

በኢንዱስትሪ መስክ ለማደግ ካላቸው ፍላጎት በመነሳት በግብርና የሚፈልጓቸውን ጥሬ ዕቃዎችን በብዛትም በጥራትም እንደልብ ለማግኘት ከሚቻልባቸው ቴክኖሎጂዎች መካከል የዘረ መል ውጤቶች እንደሆኑ ማመን ከጀመሩ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ሆናለች፡፡ በዘረ መል ምህንድስና የተመረተ ጥጥ ለማልማት እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ቢቲ ኮተን የተሰኘውን ዝርያ ከህንድ በመውሰድ ሙከራ ስታደረግ ቆይታ ለአምራቾች ለማሰራጨት ጫፍ መድረሷን ይፋ አድርጋለች፡፡ በቅርቡ እንደተዘገበው ከሆነም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የዚህ ጥጥ ዝርያ ለገበያ መቅረብ ይጀምራል፡፡

የዘረ መል ጥጡን በሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት እንደሚታሰብ ከመንግሥት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕቅድ መረዳት ተችሏል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚመራው የጥጥ ዘርፍ ልማት ስትራቴጂም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡ አገሪቱ በጠቅላላው ከሰባት ሚሊዮን ሄክታር ያላነሰ ለጥጥ ተስማሚ መሬት እንዳላት ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ለዘረ መል ጥጥ ምቹ የሆነው ሌላው አጋጣሚ መንግሥት እያስፋፋው የሚገኘው የኢንዱስትሪ ፓርኮ ግንባታ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሠማሩ ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች የሚውል የጥጥ ምርት እንደልብ ማምረትና ማቅረብ ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን፣ ግብዓቱ ያለችግር ለፋብሪካዎች እንዲቀርብ ለማስቻልም ጥጥ አምራቾች የቢቲ ኮተን ዝርያ እንዲጠቀሙ የማድረግ ዕቅድ ተወጥኖ፣ የሙከራ ሥራውም ከላቦራቶሪ ወደ ማሳ ከገባ ሰነባብቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት፣ በአሁኑ ወቅትም የኢንዱስትሪ ዘርፍና የፋይናስና ዕቅዶች ውጤማነት ክትትልና ድጋፍ ዘርፍ አስተባባሪ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው የሚነገርላቸው ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የዘረ መል ጥጥ በስፋት መመረት እንደሚጀምር በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

የባዮቴክኖሎጂ ምሁራን የዘረ መል ምህንድስና ቴክኖሎጂ በአግባቡ ከተሠራበት ጥቅሙ እንደማያጠራጥር ይከራከራሉ፡፡ በተደጋጋሚ በቴክኖሎጂው ላይ የሚነሱት ዘመቻዎችም ትክክለኛ ሳይንስን መሠረት አድርገው እንደማይነሱ ይሞግታሉ፡፡ ይሁንና ተቃውሞቹ ግን አሁንም ድረስ ቀጥለዋል፡፡ እንደ ጀርመንና ፈረንሳይ ያሉ አገሮች የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች ወደ አገሮቻቸው እንዳይገቡ መከልከላቸው ተሰምቷል፡፡

ከአውሮፓውያኑ ባሻገርም ቡርኪናፋሶ በቅርቡ የዘረ መል ጥጥ ከአገሯ እንዲወጣ ትዕዛዝ ማስላለፏ ይታወቃል፡፡ ለዕርምጃው መንስዔ የሆነው ደግሞ አገሪቱ ከዘረ መል ጥጥ የምታገኘው የምርት ጥራት ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ሲሆን፣ በዘረ መል ምህንድስና የተመረተ ጥጥ ያከሰራቸው ገበሬዎችም ዝርያውን ያቀረበላቸውን የአሜሪካውን ታዋቂ የዘረ መል ቴክኖሎጂዎች አቅራቢ ኩባንያ የሆነውን ሞንሳንቶ ላይ ክስ አቅርበዋል፡፡ ኩባንያው የ83 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂው ጉዳት እንዳለው ማሳያ መሆኑን የሚከራከሩ ወገኖች በኢትዮጵያ ሊተገበር ስለታሰበው የጥጥ ዝርያም ስጋታቸውን ሲያስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ጉዳቱ በሳይንስ ተፈትሾ መረጋገጡን፣ በርካታ ጥቅም ያሳተሳሰራቸው የውጭ ኩባንያዎችና ተመራማሪዎች የሚያደርጉት ጫና እያየለ በመምጣት እንዲህ ያለውን ቴክኖሎጂ በግድ የመቀበል ያህል እያደረጉት መምጣጣቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡

የመልካ ማኅበር ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተርና የአካባቢ ጥበቃ አቀንቃኙ ዶ/ር ሚሊዮን በላይ፣ ቴክኖሎጂው ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ አመዝኖ ስለመገኘቱ በርካታ አስረጂ ማሳያዎች እንዳሉ ይሞግታሉ፡፡

መንግሥት ግን ፀረ ዘረ መል አዋጁን ከማሻሻል ባሻገር ዝርያዎች ተሞክረው ወደ እርሻ ማሳያዎች እንዲገቡ ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን ጨምሮ፣ የባዮቴክሎጂ ዘርፍ ተመራመሪዎችና የምርምር ተቋማት ኃላፊዎች፣ ጥጥ አምራቾች የተወከሉበት የሰሞኑ የህንድ ጉበኝት ከኢትዮጵያ ባሻገር ኬንያውያንን፣ ዛምቢያውያንን፣ የስዋዚላንድ ተወካዮችንና የማሊ ሰዎችን ያካተተ ነበር፡፡

የአፍሪካውኑ ጉብኝት ህንድ የምታመርታቸውን የዘረ መል ጥጥ ዝርያዎችን፣ የእርሻ ማሳዎችን፣ በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ የሚመራመሩ የምርምር ተቋማትን ያስጎበኘ ነበር፡፡ ህንድ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ገበሬዎችን በዘረ መል ጥጥ አምራችነት ዘሰማርታለች፡፡11 ሚሊዮን ሄክታር መሬትም በዚህ የጥጥ ዝርያ ሸፍናለች፡፡ ከ95 ከመቶ በላይ የህንድን የጥጥ እርሻዎች የሞላውም ሞንሳንቶ ማሂኮ ከተባለው የህንድ ኩባንያ ጋር የሚያቀርበው ቦልጋርድ-II የተባለውና በላቦራቶሪ ምህንድስና የተሠራው ጥጥ ነው፡፡ ይህ ጥጥ ግን በቡርካና ፋሶ ገበሬዎችን ለኪሳራ መዳረጉ የተነገረለት ነው፡፡

ይህም ቢባል ህንድ በጥጥ ምርት ራሷን ችላ፣ ትርፍ አምራች ሆና ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯን አስታውቃለች፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት ስታመርተው በመቆየቷ ይህ ነው የሚባል ችግር እንዳልገጠማት ትገልጻለች፡፡ ይሁንና ግን በርካታ ፀረ ቢቲ ኮተን ዘመቻዎች በህንድ ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ ገበሬዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ተገደዋል፤ ጥጡ በቀላሉ ይቋቋመዋል ተብሎ የሚነገርለትንና እንዲቀንስ እያስቻለው ነው የተባለለትን ቦልዎርም የተባለውን የጥጥ ተባይ በቶሎ ተላምዷል የሚሉ ቅሬታዎች በህንድ ሲስተጋቡ ቆይተዋል፡፡

የቴክኖሎጂው ደጋፊዎች ግን ሁሉንም በሳይንስ አረጋግጠን አብዛኛውን ተቃዋሚ በውጤቱ አሳምነናል በማለት ላይ ናቸው፡፡ የደቡብ እስያ የባዮቴክኖሎጂ ማዕከል መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ባጊራት ኮዳህሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ አፍሪካ ከህንድ ጋር ተመሳሳይ የአየር ጠባይ ያላት፣ በትሮፒክ ዞን ውስጥ የምትገኝ በመሆኑ በህንድ የሚሠራውና ውጤታማ የሆነው ነገር በአፍሪካም ውጤታማነት እንሚያሳይ ያምናሉ፡፡

ስለዚህም የህንድን ተሞክሮ ውሰዱ፣ ከታች ጀምራችሁ ከማጥናት ይልቅ በተጠናው ላይ ተመስርታችሁ ወደ ሥራ ግቡ የሚል ምክር ለግሰዋል፡፡ በዚህ አባባል ዶ/ር ጌታቸውም ይስማማሉ፡፡ ዶ/ር ሚሊዮንና መሰሎቻቸው ግን ይህን አይቀበሉትም፡፡ በአንዱ አገር ያለው የሥነ ምህዳር ብዜተ ሀብት፣ ልዩልዩነት፣ የአፈር ጠባይ፣ የሰብል ዓይነትና ሌላውም ሲታይ እንዲህ ያለው አመለካከት ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖረው ይሞግታሉ፡፡

በዚህም ተባለ በዚያ መንግሥት የጥጥ ቴክኖሎጂን በዘረ መል በመመሥረት ከፍተኛ ምርት የማግኘት ህልሙን ለመተግበር ከጫፍ ደርሷል፡፡ አምራቾች እስከተቀበሉት ድረስ ቴክኖሎጂው ወደ እርሻ ማሳዎች ለመግባት የሚችልበት ቀነ ቀጠሮ ተቆርጦለታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች