Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብድር የመክፈል ሥጋት የለበትም›› ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር

ኢትዮጵያ በ2008 በጀት ዓመት የተፈተነችበት ነበር፡፡ በተለይ አገሪቱ ከ50 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ቦታ የሚሸፍን ድርቅ አጋጥሟታል፡፡ በዚህ ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ሕዝቦች የምግብ ዋስትናቸው ተናግቷል፡፡ ኤልኒኖ በሚባለው የአየር ፀባይ ክስተት ምክንያት የተከሰተው ይህ ድርቅ፣ አገሪቱን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከማስወጣቱ በተጨማሪ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጥላውን አጥልቶ አልፏል፡፡ መንግሥት በ2008 ዓ.ም. የአገሪቱ ኢኮኖሚ በ11 በመቶ እንደሚያድግ ተንብዮ ነበር፡፡ ነገር ግን በድርቁ ምክንያት በተለይም ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የመኸር ምርት በመቀነሱ ኢኮኖሚው ከተቀመጠለት ግብ በሦስት በመቶ ቀንሶ፣ ስምንት በመቶ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ለስምንት በመቶ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ግብርና 36.6 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 16.6 በመቶ፣ አገልግሎት 47 በመቶ አበርክተዋል፡፡ በሚኒስትር ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ ሐሙስ ኅዳር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያ ዓመት (2008 ዓ.ም.) ኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ለውጡ መጠነኛ ሽግግር ብቻ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ብዙ ዕቅዶች ቢኖሩም፣ ኢንዱስትሪው አሁንም ዝቅተኛ አስተዋጽኦ (16.6 በመቶ) በማበርከቱ ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩ አሁንም ብዙ ይቀረዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት 15.1 በመቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ኢንዱስትሪው በኢኮኖሚው ዕድገት የሚኖረው ድርሻ 18.8 በመቶ ይሆናል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለው ክፍተት ከመጥበብ ይልቅ የመስፋት አዝማሚያ እያሳየ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ ዘርፍ አራት ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሎ ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሊሳካ የቻለው 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ በዕቅዱና በተሳካው መካከል የ1.1 ቢሊዮን ዶላር ልዩነት አለ፡፡ በሌላ በኩል ግን የገቢ ንግዱ 22 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ መረጃዎች አመለክተዋል፡፡ ይህም በገቢና በወጪ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት የጫማና የባርኔጣ ያህል አራርቆታል፡፡ ለገቢ ንግድ መቀዛቀዝ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ውስጥ የግብርና ምርቶች ዋጋ መቀነስ መሆኑን ዶ/ር ይናገር አስረድተዋል፡፡ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር በወቅታዊ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከውድነህ ዘነበ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2008 ዓ.ም. መንግሥት የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አጠናቆ ሁለተኛውን ጀምሯል፡፡ ይህንን ግዙፍ ዕቅድ ለማስፈጸም የፋይናንስ አቅርቦቱ ምን ይመስላል? ከአገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችሁ ምን ያህል ነው? ከውጭ የተጠበቀውን ያህል ዕርዳታና ብድር እየተገኘ ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- ሁለት ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኛው ወጪዎች የሚሸፈኑት በአገር ውስጥ ገቢ ነው፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ይገባል፡፡ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችን በየዓመቱ እየጨመረ ነው፡፡ ግን እየሰበሰብን ያለነው ባቀድነው ልክ አይደለም፡፡ በየዓመቱ የአገር ውስጥ ገቢ እያደገ ቢሆንም አሁንም ብዙ ይቀራል፡፡ የአገር ውስጥ ገቢ የመሰብሰብ ጉዳይ ከቁጠባ ጋርም ይያያዛል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሁለተኛው የፋይናንስ ምንጭ ብድርና ዕርዳታ ነው፡፡ በተለይ ለትልልቅ መሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የባቡርና የኃይል አቅርቦት ለመሳሰሉ ፕሮጀክቶች በታቀደው መንገድ ይካሄዳል ብለን ነው የምናስበው፡፡ ያም ሆኖ ግን ወሳኙ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ነው፡፡ ምክንያቱም የወጭ ምንዛሪ የምናገኘው ከወጪ ንግድ ነው፡፡ ብቸኛው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገድ ግን የወጪ ንግድ ብቻ አይደለም፡፡ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር የሚፈስ የውጭ ምንዛሪ አለ፡፡ ለምሳሌ በ2008 ዓ.ም. አራት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህ ከኤክስፖርት በላይ ነው [በ2008 ዓ.ም. ከኤክስፖርት 2.9 ቢሊዮን ዶላር ነው የተገኘው]፡፡ ከተለያዩ ምንጮች ብድርና ዕርዳታዎች የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፡፡ ዋናው ግን ከአገር ውስጥ የሚገኘው ፋይናንስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ አገሮች የተለያየ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እየገጠማቸው ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ባቀደችው መንገድ ብድርና ዕርዳታ እያገኘች ነው ማለት ይቻላል? የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማስፈጸም የተገኘውን ብድርና ዕርዳታ ከአዲሱ ዕቅድ የፋይናንስ ሁኔታ ጋር አነፃፅረው ቢያስረዱኝ?

ዶ/ር ይናገር፡- ያለፉትን ዓመታት አፈጻጸም ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተጀመረው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፋይናንስ ሁኔታ ማየት ካስፈለገ በእኛ ድረ ገጽ ላይ ማየት ይቻላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ይህ ብድርና ዕርዳታ በተለይ ብድርን በሚመለከት በዘፈቀደ አንበደርም፡፡ ብድር ለመበደር ምጣኔ አለ፡፡ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ ጋር አብሮ የሚሄድና ከመክፈል አቅም ጋር የተየያዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ያ እየታየ ነው አበዳሪዎቹ ለኢትዮጵያ መንግሥት ብድር የሚፈቅዱት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ ያቀድነውን ያህል በተለይ ለማክሮ ኢኮኖሚው አስተዋጽኦ ላላቸው ፕሮጀክቶች ፋይናንስ እያገኘን ነው፡፡ ዝርዝሩን ከድረ ገጹ ላይ ማየት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ነገር ግን ሥራው በሚካሄድበት ወቅት መጣጣም የሚጎድላቸው ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ተገንብተውም የሚፈለገውን ግልጋሎት መስጠት ያልቻሉ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቁ አይደለም፡፡ እነዚህ አካሄዶች በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሱትን ተፅዕኖ እንዴት ነው የምትገነዘቡት?

ዶ/ር ይናገር፡- የብድር ገንዘብን ለታለመለት ዓላማ በማዋልና በአጠቃቀም በኩል ከታየ ኢትዮጵያን የአፍሪካና የሌሎች ታዳጊ አገሮች አይስተካከሏትም፡፡ ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት ያገኘነውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ነው የምናውለው፡፡ ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች በውጭ ኩባንያዎች ይገነባሉ፡፡ በአገር ውስጥ ኩባንያዎችም የሚሠሩ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የሚጠበቀውን አገልግሎት በወቅቱ ሳይሰጡ ይቀራሉ፡፡ ይኼ ድክመት ነው፡፡ የፕሮጀክት አፈጻጸም በሒደት እየተሻሻለ የሚሄድ ነው፡፡ ከልምድም ከተለያዩ ቴክኖሎጂዎችም አንፃር እየተሻሻለ ይሄዳል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ መዘግየት ይኖራል፡፡ አንዳንዱ ተቀናጅቶ በደንብ ያለማቀድ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር ብዙ ጊዜ የሚፈጠረው በዕቅዱ ላይ ነው፡፡ ዕቅዱ ሲታቀድ አንዱ ሲያልቅ አንዱ አብሮ ካልተከተለ ወደ ተግባር መሸጋገር አይቻልም፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ተናቦ ያለማቀድና ያለመገንባት ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በብድር የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች በርካታ ናቸው፡፡ ብድሩ የእፎይታ ጊዜ ቢኖረውም አንዳንድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ሒደት የሚዘገዩ በመሆናቸው ወይም አንዱ አልቆ ሌላው ተያያዥ ፕሮጀክት የሚዘገይበት ዕድል በመኖሩ ወደ ሥራ ያልገቡ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ሥራ ሳይጀምሩ የብድር መክፈያ ጊዜ የደረሰባቸው ፕሮጀክቶች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ይህ በኢኮኖሚው ላይ ጫና አያሳድርም?

ዶ/ር ይናገር፡- ብድሮች የእፎይታ ጊዜ አላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ወለድና ፍሬ ብድር መከፈል ይጀምራል፡፡ ከዚያ አኳያ አሁን ባለው ሁኔታ ከፕሮጀክቶች አፈጻጸም አንተ ባልከው ደረጃ ለክፍያ የደረሰ ፕሮጀክት ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ዋናው ጉዳይ ወለድ የመክፈል ጉዳይ ሳይሆን ፕሮጀክቶቹ በተያዙላቸው ጊዜ አለመጠናቀቃቸው አልፎ አልፎ ይታያል፡፡ ይኼ ማለት በአምስት ዓመታት ይጠናቀቃል የተባለ ፕሮጀክት ሰባት ስምንት ዓመት ወስዶ ቀሪዎቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት የወጪ ጭማሪ ያመጣሉ፡፡ አገልግሎት አለመስጠት ብቻ ሳይሆን ወጪንም ይጨምራል፡፡ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ በሁሉም ፕሮጀክቶቻችን ላይ እየተሳካልን ነው ማለት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ምን ያህል ብድር አለባት? በተለይ ውስጥ አዋቂ ነን የሚሉ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በዓመት 700 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ብቻ ወደ መክፈል ደረጃ እየተሸጋገረች መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ምን ያህል ትክክል ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- በተለያዩ ፕሮጀክቶች የተለያዩ የወለድ ምጣኔዎች አሉ፡፡ የብድር ሥርዓት የተለያየ ነው፡፡ ‘ኮንሴሽናል ሎን’ የሚባል አለ፡፡ ማለትም አገር ከአገር ጋር በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ስምምነት አማካይነት ለሚገኝ ፋይናንስ የሚከፈል ወለድ አለ፡፡ እንደዚያ ዓይነት ብድሮች ወለዳቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ አንድ አገር ሆኖ እንኳ በሚገኙ የተለያዩ ብድሮች ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ አንድ በመቶ የሚከፈል ወለድ አለ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሁለት በመቶ፣ ሌላው 2.6 በመቶ የሚሆንባቸው አሉ፡፡ እንደየፕሮጀክቶቹ ወለዶቹም የተለያዩ ናቸው፡፡ በሁለትዮሽ ግንኙነት የሚገኙ ብድሮች ወለዳቸው አነስተኛ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ አሉ ከፍ ያለ ወለድ የሚያስከፍሉ፡፡ ረዘም ያለ ጊዜ ድርድር የሚፈልጉ አሉ፡፡ ከዚህ ከወለድ አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት ሲበደር የሚያስቀምጠው መሥፈርት አለ፡፡ ወለዱ ዝቅተኛ ነው ወይ? የእፎይታ ጊዜው ረዘም ያለ ነው ወይ? በረዥም ጊዜ የሚከፈል ነው ወይ? ብድሩን የሚፈልገው ፕሮጀክት ብድሩን የመመለስ አቅም አለው ወይ? አንዳንዱ ፕሮጀክት ብድሩን የመመለስ አቅም አለው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ላይመልስ ይችላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ታሳቢ ተደርገው የሚታዩ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል መከፈል ያለበት ወለድና ፍሬ ብድር እየተከፈለ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብድር የመክፈል ሥጋት የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ያለባትን ብድርና በዓመት ምን ያህል ወለድ እየከፈለች መሆኑን ማወቅ ይቻላል?

ዶ/ር ይናገር፡- መጠኑን ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ማግኘት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በ2008 ዓ.ም. አገሪቱን ከፍተኛ ድርቅ ያጋጠማት በመሆኑ ኢኮኖሚው ስምንት በመቶ ብቻ ማደጉ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ድርቁ በግብርና ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩ በተጨማሪ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውኃ እንዲይዙ ማድረግ ባለመቻሉ በኃይል አቅርቦት ምክንያት ኢንዱስትሪው መጎዳቱ አይቀርም፡፡ ከዚህ አንፃር የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጤናማ ሁኔታ ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ይናገር፡- ማክሮ ኢኮኖሚው ጤናማ ነው፡፡ ከማክሮ ኢኮኖሚ አንፃር ጤናማ መሆኑን የምትረዳባቸው መለኪያዎች አሉ፡፡ አንዱ የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኅብረተሰቡን የሚጎዳ የዋጋ ግሽበት የለም፡፡ ግሽበቱ ነጠላ አኃዝ ውስጥ ይገኛል፡፡ አሁንም ተረጋግቶ ይቀጥላል የሚል እምነት አለን፡፡ ሁለተኛው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ጨምሯል፡፡ ከባንኮች የሚወሰደው ብድር ሌላው ነው፡፡ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው የተነቃቃ ነው፡፡ የግል ባለሀብቶች የሚወሰዱት ብድር ጨምሯል፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው መኖሩን ነው፡፡ ከቁጠባ አኳያ በ2008 ዓ.ም. አራት ወራት ውስጥ ባንኮች በቁጠባ የሰበሰቡት ገንዘብ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንፃር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም. የቁጠባ ምጣኔ 21.8 በመቶ ነበር፡፡ አሁን የቁጠባ ምጣኔ 22 በመቶ ደርሷል፡፡ ነገር ግን አሁንም በቁጠባ ላይ ይበልጥ መሠራት አለበት፡፡ የሚያስመልሱት ብድር መጠንም ጨምሯል፡፡ ደምረን ስናየው ኢኮኖሚው ጭማሪ ነው የሚያሳየው፡፡ በአሁኑ ወቅት ችግር ያለው በውጪ ንግድ ላይ ነው፡፡ የወጪ ንግድ በታቀደው መጠን እየሄደ አይደለም፡፡ አነስተኛ አፈጻጸም ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ይሰማል፡፡ በተለይ በርካታ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻላቸው ሥራ እየተስተጓጎለባቸውና ሠራተኛም እየቀነሱ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- የውጭ ምንዛሪን በሚመለከት ሁለት ነገሮችን ማየት ይገባል፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች አሉ፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ማበረታታት፣ ኤክስፖርቱን ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ዘርፎች ለተሰማሩ ባለሀብቶች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ በዚህ ላይ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ በኩል ችግር የለም፡፡ ምናልባት በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ከቅድሚያ አሰጣጥ አኳያ የሚፈልጉትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ላያገኙ ይችላሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኢኮኖሚውን ሊያሳድጉ ለሚችሉ ዘርፎች የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ የሚያስብል አይደለም፡፡ ይህን የሚሉት ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ዘርፎች ውጪ ያሉ ናቸው፡፡ ለሌላ ሥራ የውጭ ምንዛሪ የሚፈልጉ ወረፋ መጠበቅ ሊኖርባቸው ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቁር ገበያ አንድ የአሜሪካ ዶላር ከ26 እስከ 28 ብር እየተመነዘረና እየሸጠ ይገኛል፡፡ ባለፉት ወራት በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ መጠን ተመጣጣኝ ነበር፡፡ በቅርቡ ከተፈጠረው አለመረጋጋት ጋር ይያያዛል ካልተባለ በስተቀር፣ ሁኔታው የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳለ ያመላክታል የሚሉ አሉ፡፡ እናንተ ይህን ጉዳይ እንዴት ገመገማችሁት?

ዶ/ር ይናገር፡- በእኛ በኩል ታይቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ንረት በራሱ ጊዜ እንደሚወርድ ከዚህ በፊት አይተናል፡፡ እጥረት አለ የሚሉና ይህንኑ የሚያስተጋቡ አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በመንግሥትም በግል ባንኮችም የምንዛሪ እጥረት የለም፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ ውስጥ በቅርቡ ተከስቶ በነበረው ሁከት ምክንያት ያለመረጋጋት ይኖራል በሚል የተስተጋባ ነገር አለ፡፡ ይወርዳል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡

ሪፖርተር፡- ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት የቱሪስት ፍሰት ቀንሷል፡፡ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ጉዳት ስለደረሰባቸው በኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ መስተጓጎል ሊያጋጥም ይችላል የሚሉ ትንታኔዎች እየተደመጡ ነው፡፡ በተለይ 2009 ዓ.ም. የተቀዛቀዘ ዓመት ሊሆን ስለሚችል መንግሥት ማካካሻ ማድረግ ይኖርበታል የሚሉ አስተያየቶችም እየተደመጡ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የመንግሥት አቅጣጫ የትኛው ነው?

ዶ/ር ይናገር፡- ባለፉት አራት ወራት በሁሉም ዘርፎች መቀነስ አይታይም፡፡ ይህ ሁኔታ ይቀጥላል ብለን ነው የምናስበው፡፡ እንደሚታየውም በአሁኑ ወቅት የተሻለ መረጋጋት አለ፡፡ በወጪ ንግዳችን ላይም የዋጋ ጭማሪ እያየን ነው፡፡ ኢኮኖሚው በአጠቃላይ ካለፈው ዓመት የተሻለ እንጂ ያነሰ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ዕድገት ለማምጣት በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየሠራን ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ይኖራል፡፡ በቱሪስት በኩል ሁከትና ግርግር በነበረበት ወቅት መደናገጥ ሊኖር ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን መረጋጋት አለ፡፡ ቱሪስቶችም እየገቡ ነው፡፡ ዋናው የዕድገት ምንጭ ግብርናው የተሻለ ሲሆን ነው፡፡ ግብርና 10.8 በመቶ ቢያድግ ኢኮኖሚው 12 በመቶ ያድጋል፡፡ ግብርና ስምንት በመቶ ቢያድግ ኢኮኖሚው 11 በመቶ ያድጋል፡፡ እኛ አገር ባለው ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ግብርና ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ግብርና ላይ ጥሩ ነገር ካለ ኢኮኖሚው ጥሩ ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የግብርና ዘርፋችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ ለኢንዱስትሪው በመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁከትና ግርግሩ የተቃጠሉ ኢንቨስትመንቶች አሉ፡፡ ጉዳት በደረሰባቸው ባለሀብቶች ላይ መተማመን ለመፍጠር መወሰድ ያለባቸው ዕርምጃዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የማካካሻ ሥራ ለመሥራት ጥናቶች እየተጠኑ ነው፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...