Tuesday, April 23, 2024

የኢትዮጵያ ወዳጅ ቱርክ በምታካሂደው ፀረ ሽብር ዕርምጃዋ የአጋሮቿን ድጋፍ ትፈልጋለች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. በ1912 የመጀመሪያውን የኦቶማን ቱርክ ቆንስላ ጄኔራልን በሐረር ካቋቋመች በኋላ የቱርክ ሪፐብሊክ ከሰሃራ በታች አፍሪካ የመጀመሪያውን ኤምባሲ እ.ኤ.አ. በ1926 በአዲስ አበባ ከፍታለች፡፡ በዚህም የኢትዮጵያና የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ሆኗል፡፡ አሁንም የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከመቼውም የበለጠ ጠንካራ ነው፡፡ በአፍሪካ ካለው የቱርክ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል በጉልህ የሚታይ ልዩነት ቢኖርም፣ በቅርቡ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥሟቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጁ ከመገደዳቸው በፊት ቱርክና ኢትዮጵያ በአንፃራዊነት በበጎ የሚነሱ አገሮች ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. ሐምሌ 15 ቀን 2016 ከቱርክ ወታደሮች የተወሰኑት መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በቱርክ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶጋን በተመሠረተው ኤኬ ፓርቲ የሚመራው የቱርክ መንግሥት አመራር ቱርክ የበለፀገችና የተረጋጋች ዴሞክራሲያዊ የሙስሊም አገር መሆን ችላለች፡፡ ተቀባይነት ላገኙ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ምክንያት የቱርክ ኢኮኖሚ ጤናማ ዕድገት እያስመዘገበ ነው፡፡ የኤርዶጋን መንግሥት ለቱርክ የሠራው ባለፉት አሠርት ዓመታት የነበሩት የቀደሙት መንግሥታት ያልሞከሩትን ነው፡፡ የቱርክ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሦስት እጥፍ አድጓል፡፡ የቱርክ የአውሮፓ ኅብረት የአባልነት ድርድር እ.ኤ.አ. በ2005 ነው የተጀመረው፡፡ ቱርክ በኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ፣ በውጭ ኮንስትራክሽንና አገልግሎት ከቻይና በመቀጠል ሁለተኛ እንድትሆንም አስችሏል፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያም ባለፈው ዓመት ችግር ውስጥ በመግባቷ ለዓመት ያህል የቆየው ተቃውሞና አመፅ በሰዎች ሕይወት፣ አካልና የአገር ንብረት ላይ ውድመት ከማስከተሉ በፊት ደካማ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ቢኖራትም፣ በበርካታ ጉዳዮች ላይ በለውጥ ጎዳና ላይ የነበረች አገር ናት፡፡ ነገር ግን በመስከረም ወር 2009 ዓ.ም. ብቻ በአምስት ቀናት ውስጥ 130 የሚደርሱ ኩባንያዎች በኦሮሚያ በከፊልና ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ሰለባ ከሆኑ የውጭ ኩባንያዎች ውስጥ የቱርክ ይገኙበታል፡፡ ይሁንና ከዚህ ችግር በፊት በግጭት በሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት የተጎናፀፈች፣ ከአሥር ዓመት በላይ በተከታታይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ እንደ ዓለም ባንክ ሪፖርቶች በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ አገሮችን ለመቀላቀል የበቃች አገር ነበረች፡፡

በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ አያሌው ጎበዜ ከኅዳር 6 እስከ ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በቱርክ መንግሥት ጋባዥነት ቱርክን ለጎበኘው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ቡድን አንካራ ላይ እንደገለጹት፣ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተከሰተው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መሠረታዊ በሚባል ደረጃ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ የቱርክ ባለሀብቶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም፡፡ አምባሳደር አያሌው በታኅሳስ ወር የቱርክ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኒሃት ዘይቤኪ በርካታ የቱርክ ባለሀብቶችን ይዘው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ፕሮግራም መያዛቸው የዚህ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አምባሳደር አያሌው፣ ‹‹የቱርክ ባለሀብቶችና ባለሥልጣናት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ተገንዝበውታል፡፡ ሁኔታው እንዳይደገምና የባለሀብቱን ቅስም እንዳይሰብር የኢትዮጵያ መንግሥት በርትቶ እንዲሠራ ጠይቀዋል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሉሶይ በበኩላቸው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በርካታ የቱርክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ የቱርክ ኢንቨስትመንት እያደገ ይሄዳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015  ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የወጪ ንግድ 400 ሚሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ሲሆን፣ በቅርቡ አንድ ቢሊዮን ዶላር የማድረስ ዕቅድ አላት፡፡

ሁለቱ አገሮች ጥሩ የሚባል ግንኙነት ያላቸው ቢሆንም አሁን ቱርክ የፈቱላህ ጉለን ንቅናቄን ወይም ቱርክ ድርጅቱን በአሸባሪነት ከፈረጀች በኋላ የፈቱላህ ጉለን አሸባሪ ድርጅት (ፈቶ)ን፣ ከቱርክም ሆነ ከመላው ዓለም ጠራርጋ ለማጥፋት በምታደርገው ትግል ከኢትዮጵያ ብዙ ትጠብቃለች፡፡ እርግጥ ነው ቱርክ ከመሰል ወዳጅ አገሮች ተመሳሳይ ቁርጠኝነትን እየጠየቀች ነው፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከናይጄሪያና ከጋምቢያ ለተውጣጣው የአፍሪካ የጋዜጠኞች ቡድን የቱርክ የፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የቱርክ ዓለም አቀፍ ልማትና ትብብር ኤጀንሲ (ቲካ) እና የቱርክ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያና መሰል ወዳጅ አገሮች በጉዳዩ ላይ ከቱርክ ጋር መሥራት ያለባቸው ለቱርክ ደኅንነት ብቻ ሳይሆን ለራሳቸውም ደኅንነት ሲሉ ነው፡፡ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና እሱን ተከትሎ ቱርክ እየወሰደቻቸው ባሉ ዕርምጃዎች፣ ለሙከራው ዋነኛ ተጠያቂ ከተደረገው ፈቶ ጋር በተያያዘ በአሜሪካና በአውሮፓ ኅብረት ላይ ያላትን ጨምሮ ቱርክ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ከዚሁ አንፃር ዳግም ለመቃኘት የተገደደች ትመስላለች፡፡

ከዚሁ አንፃር ቱርክ በኢትዮጵያና በሌሎች አፍሪካ አገሮች ቅድሚያ ትኩረት የሰጠችው ከፈቶ ጋር ግንኙነት አላቸው ብላ የምታምንባቸው ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉላት ነው፡፡ ቱርክ በቅርቡ ያቋቋመችው ማሪፍ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ የሚገኙ እነዚህን ትምህርት ቤቶች እንዲረከብ ትፈልጋለች፡፡ ፋውንዴሽኑ በቱርክ ፓርላማ ባለፈው መስከረም ወር የተቋቋመው ለዚሁ ዓላማ ነው፡፡

አምባሳደር አያሌው ስለቱርክ ዕቅድ ግንዛቤው እንዳላቸው አመልክተው ኢትዮጵያ በይፋ ምላሽ እንዳልሰጠች፣ ቱርክም ቢሆን በይፋ ጥያቄውን እንዳላቀረበች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ጥያቄው በተለያየ መንገድ እንደሚቀርብ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የቱርክን አቤቱታ በራሷ መንገድ እያጣራች ነው፡፡ ጉዳዩ ከሕግ አንፃር ያለውን ተፅዕኖም እናያለን፤›› ብለው፣ በጉዳዩ ላይ ከዚህ በላይ ለመግለጽ እንደማይችሉም አስገንዝበዋል፡፡    

የቱርክ ዓለም አቀፍ ትብብርና ልማት ኤጀንሲ (ቲካ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሴርዳር ካም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋውንዴሽኑ እ.ኤ.አ. ለ2017 በጀት ዓመት ከመንግሥት 150 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦለታል፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ መሪዎች ስለፈቶ ትምህርት ቤቶች ዕጣ ፈንታ ሊጨነቁ እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ካም፣ ‹‹የአፍሪካ መሪዎች ለትምህርት ቤቶቹ የተሳለጠ ሽግግር እንደሚፈልጉ እንረዳለን፡፡ ፋውንዴሽኑን ያቋቋምነውም ለዚህ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የጉለን ዓለም አቀፍ የትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች መረብ ከ100 በላይ አገሮች ውስጥ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና ውጤቶቹ

እ.ኤ.አ. ሐምሌ 15 ቀን 2016 በቱርክ ጦር ኃይሎች ሥር በድብቅ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ወታደሮች መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሞክረው፡፡ ወታደሮቹ ተዋጊ ጄቶች፣ ታንኮችና ሔሊኮፕተሮችን በመጠቀም ሙከራቸውን ለማሳካት ጥረዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት፣ የፓርላማ፣ የፖሊስና ሌሎች የመንግሥት ሕንፃዎችን በቦምብ አጥቅተዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንንም ለመግደል ሞክረዋል፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ከ246 በላይ ሰዎች ሕይወት ካጠፋና ከ2,500 በላይ ሰዎችን ለጉዳት ካጋለጠ በኋላ ከሽፏል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ካደረጉት መካከልም 100 የሚሆኑት ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በቱርክ ባለፉት 50 ዓመታት በአማካይ በየአሥር ዓመቱ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960፣ በ1971፣ በ1980 እና በ1997 የተከናወኑት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች ስኬታማ ነበሩ፡፡ እንደ ቱርክ ባለሥልጣናት ገለጻ የመጨረሻው ሙከራ ካለፉት ጋር ሲነፃፀር ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ በማያጠራጥር ሁኔታ መፈንቅለ መንግሥቱን ያከሸፈው የዜጎች እምቢተኝነትና ከመንግሥት ተቋማት ጋር ያደረጉት ትብብር ነው፡፡ ባለሥልጣናቱም ይህ የሕዝብ ምላሽ የተለየ እንዳደረገው ይገልጻሉ፡፡

ሕዝቡ ወደ አደባባይ በመትመም ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎቹ ጋር እንዲተናነቅ ያደረገው የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የቴሌቪዥን መልዕክት ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሲኤንኤን ቱርክ በፌስታይም ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹ለእነዚህ ከሃዲዎች ምርጡ ምላሽ ኅብረታችንን ማሳየትና እንደ አገር ተባብረን መቆም ነው፡፡ ለዚች አገር ዕድገት ሲባል የአገሬ ሕዝቦች በአደባባይ በመውጣት እንድትታገሏቸው ጥሪ አደርጋለሁ፡፡ የሕዝብ ኃይል ከማንም በላይ እንደሆነ ሁሌም አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ጥሪ በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወደ አደባባይ ወጥቷል፡፡ ሕዝቡም ሆነ የፀጥታ ኃይሎች ተተኩሶባቸዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን ቢያጡም፣ ሕዝቡ በጀግንነት ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎች ጋር ተፋልሟል፡፡ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ቢኖራቸውም ዜጎች በአንድነት ሙከራውን አክሽፈውታል፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ከከሸፈ በኋላ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ‹‹ለሚሊዮኖች እምነት ምሥጋና ይግባና ሙከራው ከሽፏል፡፡ ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ለዴሞክራሲና ለሕግ የበላይነት ያላቸውን ቁርጠኝነት ለማረጋገጥ ለዓለም አስፈላጊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ሙከራው ሕዝባችን ለዴሞክራሲ ያለውን መታመን አልቀነሰውም፡፡ በተቃራኒው ዴሞክራሲ በቱርክ በተሻለ ሁኔታ የተደራጀና ሥር የሰደደ መሆኑን ያረጋግጣል፤›› ብለዋል፡፡

ቱርክ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተመራው በፈቶ እንደሆነ ታምናለች፡፡ እንደ ባለሥልጣናቱ ገለጻ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎቹ በምርመራ ወቅት የፈቶ አባላት መሆናቸውን አምነዋል፡፡

ነገር ግን በስደት አሜሪካ የሚገኙት ፈቱላህ ጉለን ባወጡት መግለጫ ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን፣ ሁኔታው ራሱ በመንግሥት የተቀናበረ ሊሆን እንደሚችልም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ጉለን በዚሁ መግለጫ፣ ‹‹ይህን አድርገናል አልልም፡፡ ልናደርገው ግን እንችል ነበር፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በበርካታ ወታደራዊ መፈንቀለ መንግሥቶች እንደተሰቃየ አንድ ሰው ከእንዲህ ዓይነት መፈንቅለ መንግሥት ጋር ግንኙነት አለህ መባሌን እንደ ስድብ እቆጥረዋለሁ፡፡ ይህን ክስ ሙሉ በሙሉ እክዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ጉለን በ55 የወንጀል ክሶች ተቀዳሚ ተከሳሽ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን አሁን ጉለንና ደጋፊዎቻቸውን እንደ አገሪቱ ጠላት ይወስዷቸዋል፡፡ ይሁንና ከዓመታት በፊት ፈቱላህ ጉለን የፕሬዚዳንት ኤርዶጋን የቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ የጉለን ንቅናቄ የኤርዶጋን ደጋፊ እንደነበረም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኤርዶጋን የአሁኑን ገዥ ፓርቲ እ.ኤ.አ. በ2001 የመሠረቱ ሲሆን፣ ሊበራልና መቻቻልን የሚሰብክ ሥነ መለኮትን የሚያገል የፖለቲካ ፕሮግራም እንደያዘ ይታመናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2000 በተደረገው ምርጫ የአርዶጋን ኤኬ ፓርቲ በከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ወደ ሥልጣን መጥቷል፡፡ እንደ በርካታ ምንጮች ገለጻ፣ ኤርዶጋን ያለ ጉለን ዕርዳታ የሕዝቡን ድጋፍ በአጭር ጊዜ ለማግኘት ይቸገሩ ነበር፡፡ ኤርዶጋንም ሆኑ ጉለን ሴኩላር ፖለቲካን (ዓለማዊ) የሚቃወሙ አማኝ ሙስሊሞች እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ ነገር ግን በሒደት በአቀራረባቸው ላይ ልዩነት እያዳበሩ በመምጣታቸው መቃቃራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ፕሬዚዳንት ኤርዶጋንና ቤተሰባቸው በሙስና ወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸው ጥረት ያደረጉት ጉሊኒስቶች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ከዚህ ሙከራ በኋላ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩም ይነገራል፡፡ ከ2013 በኋላ በተደረጉ ምርጫዎች ጉለኒስቶች ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ መስጠታቸውን ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

ከመንግሥት ግምገማ በተቃራኒ ጉለን በደጋፊዎቻቸው እንደ መንፈሳዊ መሪ ይታያሉ፡፡ ደጋፊዎቻቸው ጉለንን በተለያዩ እምነቶች መካከል ውይይትን የሚደግፉ ለዘብተኛ የእስልምና አስተማሪ ሲሉም ይገልጿቸዋል፡፡ የጉለን አስተምህሮዎችና ጽሑፎች ለዘብተኛ፣ ለምዕራቡ ዓለም የተመቸ ሱኒ እስልምናን የሚሰብክና ለተማሩና ባለሙያ ቱርካዊያን እጅግ የሚስብ እንደሆነም ይነገራል፡፡ ጉለን እስልምናን ከምክንያታዊ አስተሳሰብና ሳይንሳዊ ምርመራ ጋር ማዛመዳቸውን የሚወዱላቸውም አሉ፡፡ በአጠቃላይ የጉለን ሰበካዎች ለዘብተኛ እስልምናን ከበጎ አድራጎትና ሕዝባዊ አገልግሎት፣ ከጠንካራ ሠራተኝነትና ከቢዝነስ እንዲሁም ከትምህርት ጋር እንዳያያዙም ይገለጻል፡፡ ለብዙ ሰዎች ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና የዕርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ በጉለኒስቶች የተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የቱርካውያኑን ማኅበራዊ ችግር ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡

የቱርክ መንግሥት ጉለኒስቶች ጥሩ ሥራ የሚሠሩ በመምሰል የድብቅ አጀንዳቸውን ለማሳካት ይጥሩ እንደነበር ያምናል፡፡ መንግሥት ለአገሪቱ አደጋ መሆናቸውን እንደተገነዘበም የፈቶ አባላትን ከመንግሥት ተቋማት ጠራርጎ ለማስወገድ መንቀሳቀሱን የቱርክ ባለሥልጣናት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ድርጅቱ በሚስጥር የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ይህን በቀላሉ ማሳካት አልተቻለም፡፡

ቱርክ የፈቶ አባላት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሰግሰጋቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ‹‹የጎንዮሽ የመንግሥት መዋቅር›› ፈጥረው እንደነበር ትገልጻለች፡፡ የፈቶ አባላት ማንነታቸውን በመደበቅ እንደ ጦር ኃይል፣ ፍርድ ቤት፣ የደኅንነት ተቋምና በመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡ በተለይ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በደኅንነት አገልግሎትና በፍርድ ቤቶች የነበራቸው ሚና ጉልህ እንደነበርም ተመልክቷል፡፡ ከቢዝነስም አንፃር ጉለኒስቶች በቱርክ ውስጥ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችንና ትልልቅ ጋዜጦችን፣ የወርቅ ማዕድን ማውጫዎችንና ባንኮችን በባለቤትነት ተቆጣጥረው ነበር፡፡

ቱርክ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 120 መሠረት ፈቶንና አባላቱን ለማጥፋት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች፡፡ ፓርላማው አዋጁን እንዲያፀድቀው ሐሳብ ባቀረቡበት ወቅት ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን፣ ‹‹ይህ አዋጅ በምንም ዓይነት መንገድ ዴሞክራሲን፣ የሕግ የበላይነትንና የቱርክ ዜጎች መሠረታዊ ነፃነቶችን የሚጥስ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ከአዋጁ መፅደቅ በኋላ ቱርክ ከፈቶ ጋር ግንኙነት አላቸው ብላ በጠረጠረቻቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ላይ ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከ6,000 በላይ ወታደሮች ታስረዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች፣ ዓቃቤ ሕጎችና ዳኞች ወይ ተባረዋል አሊያም ታግደዋል፡፡ ምሁራን፣ መምህራንና የመንግሥት ሠራተኞችም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ገጥሟቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ዕርምጃው 125,000 ሰዎችን ከ375 ተቋማት እንዳባረረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 36,000 ያህሉ በእስር ቤት ሆነው የፍርድ ቤት ቀጠሮ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ ጉዳዩን ለመከታተል 70 ዓቃቤ ሕጎች እንደተሰማሩም ተገልጿል፡፡

የቱርክ ባለሥልጣናት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ቱርክ እነዚህን ዕርምጃዎች መውሰዷ ተፈጥሯዊ ምላሽ ነው፡፡ ይሁንና በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና በቱርክ ዕርምጃ ዙሪያ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ ለአንዳንዶች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ከምንም የተነሳ አይደለም፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎቹ ለድርጊታቸው የሰጡት ምክንያት መንግሥት በሙስና መዘፈቁንና ከሃይማኖት ነፃ መሆን አለመቻሉን ነው፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እነዚህ ሥጋቶች በተወሰነ የቱርክ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚታመንባቸው እንደሆኑ ይከራከራሉ፡፡

ዕርምጃዎቹም ያለበቂና አስተማማኝ ማስረጃ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየጣሱ ናቸው በማለት የሚተቹ አሉ፡፡ ከመንግሥት የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ሁሉ በመጨፍለቅ ከፈቶ ጋር በማያያዝ የሚወሰዱ ዕርምጃዎችም፣ የቱርክ ዴሞክራሲና ብዝኃነት ያለው አስተሳሰብ የማራመድ መብት ላይ ትልቅ ጉዳት እየደረሰ ነው በማለት ቅሬታ የሚያቀርቡም በርካቶች ናቸው፡፡

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውና የቱርክ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

ቱርክ ከአፍሪካ ጋር በበርካታ ጉዳቶች ላይ በጋራ እየሠራች ትገኛለች፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በባህልና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ግንኙነት መሥርታለች፡፡

ከዚህ ጠንካራ ግንኙነት አንፃር ፈቶ ጋር እያደረገች ላለው ጦርነት የአፍሪካን ድጋፍ እጅግ ትሻለች፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የፈቶ ትምህርት ቤቶችን ለማሪፍ ፋውንዴሽን እንዲያስረክቡ ትፈልጋለች፡፡ ይሁንና ከጥቂት አገሮች ውጪ ብዙዎቹ መልስ አልሰጡም፡፡

ከአሜሪካ ጋር ጠንካራ ግንኙነት የነበራት ቱርክ፣ አሜሪካ ፈቱላህ ጉለን ከሚኖሩበት ፔንሳልቫኒያ አሳልፋ ለቱርክ ካልሰጠች ያላትን ግንኙነት ለማጤን እንደምትገደድ ገልጻለች፡፡

ወደ አውሮፓ ኅብረት ለመቀላቀል ቱርክ ስታደርገው የነበረው ጥረትም እክል የገጠመው ይመስላል፡፡ የቱርክ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ ስፋትና ጥልቀት ከተቹት የአውሮፓ አገሮች መካከል የአውሮፓ ፓርላማ የሕግ አውጭ አካላት የቱርክ አባልነት ድርድር በዚሁ ምክንያት እንዲቋረጥ ጠይቀዋል፡፡   

        

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -