Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናዶ/ር መረራ ጉዲና በእስር ላይ ሆነው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው

ዶ/ር መረራ ጉዲና በእስር ላይ ሆነው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው

ቀን:

‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰው በመገኘታቸው ዕርምጃው ተገቢ ነው››   መንግሥት

‹‹ጉዳዩን በቅርበት እንከታተላለን››  የአሜሪካ መንግሥት

የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ባደረገላቸው ግብዣ ወደ ቤልጂየም ብራሰልስ አቅንተው የነበሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮና) ሊቀመንበሩና የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደተመለሱ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየካሄደባቸው ነው፡፡

ዶ/ር መረራ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንቀጽ ሁለትን ተላልፈው በመገኘታቸው፣ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ዓርብ ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ አዲስ ባዋቀሩት ካቢኔ ውስጥ የተካተቱት ዶ/ር ነገሪ እንደተናገሩት፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ ሁለት መሠረት በሽብር ከተሰየሙ ድርጅቶችና ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ ክልክል ነው፡፡

ሆኖም ዶ/ር መረራ ይህንን ድንጋጌ ተላልፈው በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው የማጣራት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ግብዣ በተደረገላቸው ቤልጂየም ብራሰልስ ተገኝተው፣ በኢትዮጵያ ስለሰብዓዊ መብት አያያዝና ሌሎች ጉዳዮች ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ሌላው የተጋበዙት በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር መረራ ከእነ ዶ/ር ብርሃኑ ጋር በመገናኘታቸው፣ በመወያየታቸውና በጋራ መግለጫ በመስጠታቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጣሳቸው ተገልጿል፡፡

በመሆኑም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንቀጽ 28(1) መሠረት ኮማንድ ፖስቱ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር አውሏቸው፣ በንዑስ አንቀጽ (4) መሠረት በቤታቸው ብርበራ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ዶ/ር መረራ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በመኖሪያ ቤታቸው ሲሆን ስድስት ሰዓት የፈጀ ብርበራ በቤታቸው ውስጥ መደረጉንና በመጨረሻ እሳቸው እንደሚያሳድጓቸው ከተገለጸ ሁለት ወጣቶች ጋር ወደ ማዕከላዊ መወሰዳቸውን ቤተሰቦቻቸው እንደነገሯቸው የኦፌኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ጥሩነህ ገምጣ ተናግረዋል፡፡ ቤታቸው ሲበረበር የተገኙ በርካታ መጻሕፍት፣ ላፕቶፖች፣ ኮምፒዩተሮችና መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ በኤግዚቢትነት መወሰዱንም ቤተሰቦቻቸው እንደነገሯቸው አቶ ጥሩነህ አክለዋል፡፡

በአዋጁ መሠረት አዋጁን ተላልፎ የተገኘን ተገቢ የተሃድሶ ትምህርት በመስጠት ከመልቀቅ አንስቶ፣ ፍርድ ቤት የማቅረብና የአዋጁ ተፈጻሚነት እስከሚያበቃ ድረስ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስንበት ቦታ ሊያቆይ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምክትል ቃል አቀባይ ማርክ ቶነር ባለፈው ሐሙስ በነበራቸው ዕለታዊ የፕሬስ ማብራሪያ፣ የዶ/ር መረራን ጉዳይ አንስተው የእሳቸውን የመታሰር ሪፖርት መስማታቸውንና የኢትዮጵያ መንግሥት የሚመሠረትባቸውን ክስ ለሕዝብ ግልጽ እንዲያደርግ መንግሥታቸው እንደሚጠይቅ አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩንም መንግሥታቸው በቅርበት እንደሚከታተል ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ...

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

በአበበ ፍቅር ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች...