የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራሞች ባደጉትና የተሻለ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚተገበር ቢሆንም፣ ባላደጉትና ይልቁንም ሕፃናት ተማሪዎች በምግብ እጦት ምክንያት ከትምህርት ቤት በሚቀሩበት፣ ትምህርት ቤት ደርሰው በሚዝለፈለፉበትና ራሳቸውን በሚስቱበት አገሮች አቀርቦቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ለችግር የተጋለጡ ተማሪዎችን በምግብ አለመድረስ፣ ምግብ ለሚቀርብላቸው ተማሪዎችም ቢሆን የተመጣጠነ ምግብ አለማቅረብ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምገባ ሥርዓቱ በተለያዩ አካላት የሚከናወን በመሆኑ የምግብ አቅርቦት ወጥነት አለመኖር፣ ተባብሮ ለመሥራት አለመቻል፣ ታዳጊ አገሮችን በትምህርት ቤት ምገባው ስርዓት የሚፈትኑ ችግሮች ናቸው፡፡ በእንደዚህ አይነት ችግሮች ከሚፈተኑ አገሮችም ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡
ከኢትዮጵያ አዲስ አበባን ብቻ ብንወስድ በመንግሥት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከሚገኙ ተማሪዎች 90 በመቶ ያህሉ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊ መሆናው ከዓመት በፊት በተደረገ ዳሰሳ ታውቋል፡፡
ይህ የዳሰሳ ጥናት ከመደረጉ አስቀድሞ በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ ተቋማት የምግብ፣ የዩኒፎርም፣ የትምህርት መረጃና ሌሎችም ድጋፎች ሲሰጡ የነበረ ቢሆንም፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፣ ሁሉንም ችግረኛ ተማሪዎችም ለመድረስ አልተቻለም፡፡
በመሆኑም ተማሪዎች በረሃብ ምክንያት ክፍል ገብተው ራሳቸውን ሲስቱ፣ ትምህርት መማር ሲያቅታቸው፣ ሲተኙ አልያም ከትምህርት ገበታ ሲቀሩ ማየቱ ብዙ መምህራንን ያሳቀቀ፣ ያላቸውን ምግብ እንዲካፍሉ ያደረገ ክስተት ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ በመምህራኑ ብቻ የሚፈታም አልነበረም፡፡
የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ግለሰቦችና መምህራን የሚያደርጉትን እገዛ ለመደገፍ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮና በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የበላይ ጠባቂነት የሚንቀሳቀሰው የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የመጀመሪያ ደረጃ የሚማሩና በጣም ችግረኛ የሆኑ 20 ሺሕ ተማሪዎችን በመመገብ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ መምህራንና የትምህርት ቤት ክበባት ደግሞ ከ10 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ይመግባሉ፡፡
የምግብ ድጋፍ የሚያገኙት ተማሪዎች የከፋ ችግር እንዳለባቸው በመንግሥት ተረጋግጦ ሲሆን፣ ተቋማትም ምገባውን የሚያካሂዱት በመንግሥት በኩል ለተመረጡ ተማሪዎች ነው፡፡
የተማሪዎቹ አመጋገብ ምን ይመስላል?
የጤና ሁኔታና የተመጣጠነ ምግብ በተማሪዎች የመማር አቅም ላይ ወሳኝ ናቸው፡፡ በባዶ ሆድ ትምህርት ቤት የሚመጡ ታዳጊዎችን ረሃብ ማስታገስ አንዱ ሆኖ፣ ረሃብ ማስታገሱ በተመጣጠነ ምግብ ያልታጀበ ከሆነ የተማሪዎቹን ትምህርት የመቀበል አቅም ደካማ ከማድረጉም በላይ ወደፊት አገራቸውን የማይረዱና ራሳቸውን የማይደግፉ የመሆን ዕድላቸውን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም የተማሪዎች ምገባ የተመጣጠነ ምግብ ላይ ያተኮረ መሆን፣ አገሪቷ ወደፊት የሚገጥማትን ጫናም መቀነስ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የትምህርት ቤት ምገባ መመሪያ ተማሪዎች እንደ ዕድሜያቸውና ፆታቸው የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት እንዳለባቸው አስፍሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በአራቱ፣ በእያንዳንዱ 100፤ በጅሩ አንድ ትምህርት ቤት 100 በአጠቃላይ 500 ተማሪዎችን የሚመግበው የኢንተርናሽናል ፈንድ ፎር አፍሪካ ኦፕሬቲንግ ማናጀር ወይዘሪት ሰብለ ነብየ ልዑል፣ የተማሪዎች ምገባ የተመጣጠነ ምግብ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት ይላሉ፡፡
ረሃብ በማስታገስና የተመጣጠነ ምግብ በማቅረብ መካከል ከአዕምሮ እድገት ጋር ተያይዞ የጎላ ልዩነት እንዳሉት ያስታወሱት ወይዘሪት ሰብለ፣ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ምግብ የማግኘት ችግር ያለባቸው ብዙ ልጆች ቢኖሩም፣ ልጆች በትምህርታቸውም ሆነ ኋላ ሥራ ላይ ውጤታማ የሚሆኑት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ሲችሉ በመሆኑ የምገባ ሥርዓቱ የተመጣጠነ ምግብ ላይ ማተኮር እንዳልበት ይመክራሉ፡፡
ድርጅቱ ዓለምዓቀፍ የጤና ድርጅት ባስቀመጠው የተመጣጠነ ምግብ መስፈርት መሠረት፣ ለሚመግባቸው ተማሪዎች በሙሉ ከ80 በመቶ በላይ የተመጣጠነ ምግብ እንደሚያቀርብ ከዚህ በተጨማሪ የዓይን ሕክምናና የመነፅር ድጋፍ፣ ቫይታሚን ኤ እንዲሁም የሆድ ትላትል ማስወገጃ መድኃኒቶችንም እንደሚሰጥ ያክላሉ፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተማሪዎች ምገባ ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚሠጥ የምግብ ድጋፍ የሆድ ትላትልና ሌሎች በሽታዎችን ማከምንና የተመጣጠነ ምግብን ያካተተ እንደሆነ፣ ተማሪዎቹ በትምህርት አቀባበላቸው የጎበዙና በኋላም ኃላፊነት መሸከም የሚችሉ ዜጎች ማፍራት ይቻላል፡፡
አቅሙ ካለ ለተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ፣ ሕክምናና ሌሎች ድጋፎች መስጠት ወሳኝ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ደረጃ ግን ይህንን ለማድረግ ውስንነት እንዳለ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ ይገልጻል፡፡
በቢሮው የሕፃናት ጤናና ምገባ ባለሙያ ወይዘሪት ሜቲ ታምራት እንደሚሉት፣ በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በርካታ ተማሪዎች ችግር አለባቸው፡፡ ትምህርት ቢሮው፣ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር በመቀናጀት ከሚመግቧቸው 20 ሺሕ ከሚደርሱ ተማሪዎች በተጨማሪ 10,192 ሕፃናት በተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት ይረዳሉ፡፡ ሆኖም ብዙ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ተማሪዎችን መድረስ አልተቻለም፡፡
የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ ያለው ጠቀሜታ ቢታወቅም ትምህርት ቤቶች ጋ ሲሄድ የሚታየው መጠነ ሰፊ ችግር ካለው አቅም ጋር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ የችግሩ ስፋት ሲታይም ጥቂት ተማሪዎችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተመጣጠነ ምግብ ማብላት ወይስ? ብዙዎችን አነስተኛ የምግብ ይዘት ያለው መመገብ? የሚለው ሊታይ ይገባል ይላሉ፡፡
የተማሪዎች ምገባ በብዙ አገሮች ያለ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያለውን ለየት የሚያደርገው እጅግ በከፋ ችግር ያሉት ላይ ማነጣጠሩ ነው፡፡ በሌላም በኩል በጣም ጥሩ የሚባል የተመጣጠነ ምግብ አይቀርብላቸውም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የአቅም ውስንነት ነው፡፡
አብዛኞቹ ግብረሰናይ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎችም ጥቂት ተማሪ ይዘው ወተት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ጭምር የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ይህንን በማያቀርቡ ተቋማት በሚረዱ ተማሪዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ተማሪዎቹ ታዳጊ ሕፃናት ከመሆናቸው አንፃር ይጓጓሉ፡፡ ከሚመግባቸው ድርጅት ወጥተውም የተሸለ ምግብ ወደሚቀርብበት መሄድን ይመኛሉ፡፡
የእናት ወግ በጎ አድራጎት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ደብረወርቅ ልዑልሰገድ እንደሚሉት፣ ማኅበሩ በጣም የተመጣጠነ ወይም የተጋነነ ምግብ አያቀርብም፡፡ ከችግሩ ስፋትና ምግብ ከሚፈልጉ ተማሪዎች አንፃርም ይህንን ማድረግ አይቻልም፡፡ ባለው ውስጥ አቅም መድረስ የተቻለውም ለ20 ሺሕ ተማሪዎች በቀን ቁርስና ምሳ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም በአዲስ አበባ ከሚገኙ ከ800 በላይ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ ተማሪዎች 90 በመቶ ያህሉ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ የተጠቃሚውን ቁጥር ከፍ አድርጎ በዝቅተኛ ወጪ መመገብ የአሁን እቅዳቸው ሲሆን፣ የተመጣጠነ ምግብ ማቅረብ ደግሞ ወደፊት አቅም ሲፈቅድ የሚተገበር ይሆናል፡፡
በአንድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ሁለት ወይም ሦስት የተለያዩ ተቋማት ለየብቻ በተዘጋጁላቸው ክፍሎች ቁርስና ምሳ የሚያቀርቡ መሆኑ፣ የምግብ ዓይነት እንደየድርጅቶቹ አቅም መለያየቱ በልጆቹ ላይ የሥነልቦና ችግር ማስከተሉን፣ ልጆች ዓይኖቻቸውን ወደ ሌሎች እንዲያተኩሩ ማድረጉን ወ/ሮ ደብረወርቅ ይናገራሉ፡፡ ለምሳ ሥጋ ከዚያ በኋላ ፍራፍሬ የሚመግቡም አሉ፡፡ ይህ መልካምና ለልጆቹ ዕድገት ተብሎ የሚደረግ ቢሆንም የሌሎችን ሥነልቦና እየነካ ነው፡፡
የተመጣጠነ ምግብ መቅረቡን እንደሚደግፉት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍም እንዲቀጥል እንደሚፈለግ የሚናገሩት ወ/ት ሜቲ፣ ሁሉም በምግብ የተቸገሩ ተማሪዎችን ለመመገብ፣ ከትምህርት እንዳይርቁና ብቁ ዜጋ ለማድረግ እየሠሩ እስካሉ ድረስ፣ በመቀራረብ በተማሪዎች መሃል ልዩነት በማይፈጥር መልኩ መመገብ የሚቻልበት መንገድ ላይ መወያየት እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ፡፡
ወጥ የአመጋገብ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ መዘጋጀቱን፣ መመሪያውን በምን መልኩ እናሻሽለው በሚለው ላይ ደግሞ በምገባው ላይ ከተሰማሩ ተቋማት ጋር እንደሚወያዩበትም አክለዋል፡፡
ምግቡን ተመሳሳይ እንዲሁም የምገባ ፕሮግራሙን ቀጣይ ለማድረግ የተማሪዎችን ሁኔታ አይተንና ተቀራርበን የምንሠራበት ሁኔታ እንዲፈጠርና በምገባ ያልተዳረሱ ልጆችን እንድንመግብ እንፈልጋለንም ብለዋል፡፡
በእርዳታ ብቻ ከማተኮር፣ ራስን በራስ ችሎ በየትምህርት ቤቱ የምግብ ችግር ላለባቸው ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ ለማቅረብ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን ለችግሩ መፍትሔ እንደሚሆን ደግሞ ወይዘሪት ሰብለ ይናገራሉ፡፡
ድርጅታቸው የምገባ አገልግሎት በሚሰጥባቸው የአግዓዝያን ቁጥር ሁለት አፀደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ እንዲሁም በስብስቴ ነጋሴ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ከተማሪ አልፈው ለውጭ ገበያ በመዋል ገቢው ተጨማሪ ተማሪዎችን ለማካተት የሚያስችል ሁለት ዘመናዊ ዳቦ ቤቶች አደራጅቷል፡፡ በየአግዓዝያን ትምህርት ቤት ገንብተው፣ ስብስቴ ነጋሲው ደግሞ ትምህርት ቤቱ የሰጣቸውን ክፍል መልሰው አድሰው ለአገልግሎቱ ቢያዘጋጁም፣ ዳቦ ቤቶቹ ሥራ መጀመር አልቻሉም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ማን ያስተዳድረው የሚለው ላይ ትምህርት ቤቶቹና ድርጅቱ ከየተመዘገቡባቸው የሥራ ዘርፍ አንፃር መስማማት ባለመቻላቸው ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የንጥረ ነገር ክምችት የያዘውን መሽሩም በምገባ ሥርዓቱ ለማስገባት በስብስቴ ነጋሲ በተሰጣቸው ክፍል ማብቀል ጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ መርዛማ ነው በሚል ምክንያት እንደተቋረጠ ይናገራሉ፡፡ መሽሩሙም መርዛማ እንዳልሆነ፣ ተማሪዎች ቢመገቡት መልካም መሆኑን ቢናገሩም የሰማቸው አላገኙም፡፡ ዳቦ ቤቶቹም ከሥራ ተስተጓጉለዋል፡፡
የእሳቸው ድርጅት ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ተማሪን የሚመግብ ተቋም በመተባበር በትምህርት ቤት በሚገኙ ባዶ ሥፍራዎች የጓሮ አትክልት ቢያበቅል፣ የገቢ ማግኛ ዘዴ ቢፈጥር ሁሉን ተማሪዎች የተመጣጠነ ምግብ መመገብ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ፡፡
ወይዘሪት ሜጢ በበኩላቸው ተማሪዎችን ለመርዳት የታሰበ ሥራ ለምን እንደተስተጓጎለ እንደሚያጣሩ፣ የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ግን የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡
የምግብ ድጋፍ እያገኙ የሚማሩ ተማሪዎች የተረጂነትና የበታችነት መንፈስ እንዳይኖራቸውም የሥነ ልቦና ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡