Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየመልካም አስተዳደር ማስፈኛ ሕጎችና የጥልቅ ተሃድሶ አራምባና ቆቦነት

የመልካም አስተዳደር ማስፈኛ ሕጎችና የጥልቅ ተሃድሶ አራምባና ቆቦነት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ሰፊ መጠን ያለው ተቃውሞ ካስተናገደባቸው ዓመታት ውስጥ አንዱ፣ 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ በትግራይ ክልል የወረዳ ማቋቋም ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡ በወልቃይት አካባቢ ደግሞ ከአማራ ማንነት ጋር ተያይዞ ወደ አማራ ክልል እንካለል የሚል ችግር በመከሰቱና ውሎ አድሮም ወደ አማራ ክልል ተስፋፍቶና ተዛምቶ የአማራና የትግራይ ተወላጆችን የሚያቃቅር ድርጊት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ሰዎችም ሞቱ፡፡ ንብረትም ወደመ፡፡  በኦሮሚያ ክልል ደግሞ ምንም እንኳን በተወሰነ መልኩ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እንደ መነሻ ቢሆንም፣ የችግሮቹና የሕዝቡ ብሶት ፈርጁ እየበዛ በመሄዱ የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱ ይታወቃል፡፡ እጅግ በርካታ ንብረትም ወድሟል፡፡ በደቡብ ክልል ደግሞ የኮንሶ ብሔረሰብ የልዩ ዞን ምሥረታ ጋር በተያያዘ በርካታ መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ሰዎች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡ በጌዲኦና በሌሎች ብሔረሰቦች መካከል በተነሳው ግጭት ምክንያትም እንዲሁ የሰው ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል፡፡ የችግሩ መጠን እየሰፋና ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ እየሆነ በመምጣቱ ወይንም ደግሞ መንግሥት የማስተዳደር ኃላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ ተቃውሞውን ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፡፡ የሕዝቡን የተቃውሞ መነሻ ናቸው በማለት መንግሥት ለሕዝቡ ካሳወቃቸው ውስጥ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል አዝማሚያና ድርጊት እንደሆኑ በመግለጽ እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት ‹‹በጥልቀት መታደስ››ን እንደ  በመፍትሔነት አቅርቧል፡፡

ይህ ጽሑፍ የሚያጠነጥነው ከላይ የቀረቡትን ችግሮች በፌዴራልና በክልሎች ይፈቱበታል ተብሎ በመፍትሔነት የቀረበውን በጥልቀት መታደስ ሕጋዊ አንድምታ መፈተሽ ነው፡፡ በተለይም የሕግ አስፈጻሚው የሚያከናውናቸውን ተግባራት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ፣ ውሳኔዎች ከመወሰናቸው በፊት ሕዝብ በማሳተፍና የሕግ የበላይነትን በማስፈን መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ከሚረዱ ሕግጋትና ተቋማት አንፃር ቅኝት ያደርጋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. በተደረገው የፌዴራልና የክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ምርጫ፣ መቶ በመቶ ኢሕአዴግና አጋሮቹ እንዳሸነፉ ስለተገለጸ በዚያ ዓመት መጨረሻና በቀጣዩ ዓመት የመጀመሪያ ወራት ላይ በሁለቱም እርከኖች ላይ ምክር ቤቶች ሥራቸውን በመጀመር፤ የሕግ አስፈጻሚውም ተዋቀሯል፡፡ እንደ አዲስ የተቋቋመው መንግሥት ለአንድ ዓመት ያክል እንኳን ሳይመራ መረጠ የተባለው ሕዝብ አመራሩን ተቃወመ፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ መቶ ፐርሰንት እንደተመረጠ የገለጸው የኢሕአዴግ መንግሥት በተቃውሞ ተናጠ፡፡ በአፀፌታው፣ መንግሥት አስቀድሞ በፓርቲ ደረጃ በመወያየትና በመወሰን ችግሮችን ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ወደሚሉ ፈርጆች በማጠቃለል መፍትሔውን ደግሞ አንድ ፖለቲካዊ ኮረጆ ውስጥ ከትቶታል፡፡ ችግሮቹንም ይሁን መፍትሔ በማለት ያስቀመጠው፣ በዋናነት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እንጂ ሕግን መሠረት ያደረገ አይደለም፡፡ ከፓርቲ ውሳኔ እንጂ ሕግን መሠረት አድርጎ ከሚሠራበት መንግሥታዊ አሠራርና አካሄድ አይደለም፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትም ይሁን በጥልቀት መታደስ የሕግ ጽንሰ ሐሳቦች አይደሉም፡፡ በእርግጥ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ሕጋዊ አሠራርን ላይጥሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን፣ ለውሳኔ መነሻ የሚሆኑት ጉዳዮች በሕግ አስቀድመው ስለማይቀመጡ ለሕዝብ ግልጽ አይደሉም፡፡ ተገማችም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ በመሆኑም ፓርቲው በየጊዜውና እንደ ሁኔታው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችን ወደ መንግሥታዊ አሠራር  ስለሚቀላቅላቸው ዱብዳዊ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂ የሆኑ ሥርዓትንና ተቋማትን ከመመሥርት ይልቅ ጊዜያዊ የሆኑ እልባቶችን መስጠት ላይ የተጠመደ ያደርገዋል፡፡ 

መንግሥት፣ አስተዳዳራዊ እንከኖችን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶችን ለማስተካከል ከተጠቀመባቸው ሥልቶች ውስጥ የተወሰኑት ሙስናን መከላከል፣ ኪራይ ሰብሳነትን መዋጋት፣ በጥልቀት መታደስ፣ ሂስና ግለሂስ ማድረግ፣ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ መተግበር፣ የዜጎች ቻርተር ሥራ ላይ ማዋል፣ ቢኤስሲ (Balanced Score Card)፣ ካይዘንንን መተግበርና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ በየጊዜው ሥራ ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ በተለይም ከሙስና ድርጊቶች በስተቀር ሌሎቹ እምብዛም የሕግ ድጋፍ ወይንም መሠረት የላቸውም፡፡ ከእዚህ በተጨማሪም አንዳንዶቹን ስንመለከት ሳይንሳዊ አሠራር ናቸው ማለት ይቸግራል፡፡ ይዘታቸውም፣ ምን እንደሆነ በውል ለመለየት ይከብዳል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በጥልቀት መታደስና ኪራይ ሰብሳቢነትን መውሰድ ይቻላል፡፡

በጥልቀት መታደስ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን?

መልካም አስተዳደር በሌለበት ሁኔታ ዴሞክራሲ ይኖራል ማለት ዘበት ነው፡፡ መልካም አስተዳደር፣ የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ አንድን የመንግሥት የማስተዳደር ዘዬ፣ ‹‹መልካም›› ወይንም ‹‹መጥፎ›› ለማለት የሚያገለግሉ የተለያዩ መለኪያዎች አሉ፡፡ በሌላ አገላለጽ መንግሥት የማስተዳደር ኃላፊነቱን ሲያከናውን ምን ዓይነት መርሆችን መከተል እንዳለበት በመለኪያነት ሊጠቅምባቸው የሚገባ መሥፈርቶች አሉ፡፡ የእነዚህ መሥፈርቶች መሟላት ወይንም አለመሟላት የአስተዳደር ሒደቱን ‹‹መልካም›› ወይንም ‹‹መጥፎ›› ያሰኘዋል ማለት ነው፡፡ ከእነዚህ መካከልም የተወሰኑት ግልጽነት፣ ኃላፊነት፣ ተጠያቂነት፣ የሕዝብ ተሳትፎ፣ ምላሽ ሰጪነት፣ የሕግ የበላይነት የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህን መርሆች መከተልና መለኪያዎች ማስፈን የሚችል ሥርዓት መዘርጋት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡  ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12 ላይ ሠፍረዋል፡፡

መልካም አስተደዳርን ማስፈን  የሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና አለው፡፡ የአንዱ መጎልበት ሌላውን ይደግፋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ መልካም አስተዳደር በራሱ እንደ መብት መታየት ጀምሯል፡፡ ለአብነት፣ የአውሮፓ ኅብረት ቻርተር አንቀጽ 41 ላይ ዜጎች በመልካም ሁኔታ የመተዳደር መብት እንዳላቸው በመግለጽ መንግሥት ደግሞ ይሄንን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ደንግጓል፡፡ መልካም አስተደዳር ሰብዓዊ መብትን ከማረጋገጥ በዘለለ ልማትን እውን ለማድረግ ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሙስናን ለመቀነስ፣ ችጋርን ለማስወገድና ልማትን ለማፋጠን ይጠቅማል፡፡ መልካም አስተዳደርን የሚቃረኑ ተግባራትን በመፈጸም ረገድ የሕግ አስፈጻሚ የሆነውን መንግሥት የሚወዳደር ያለ አይመስልም፡፡ በመሆኑም፣ አገሮች የተለያዩ ተቋማትን በማቋቋም አድራጎቱን ለመግራት ጥረት አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል ደግሞ ፓርላማው በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነው፡፡

ሕግ አውጪው አስፈጻሚውን ከሚቆጣጠርባቸው ሥልቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ፓርቲያዊ ቁጥጥር ሲሆን፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ባሉበት ፓርላማ የገዥው ፓርቲ የሚፈጽማቸውን አስተዳደራዊ እንከኖችና ሕግን ያለማስፈጸም አድራጎቶችን የሚያጋልጡበትንና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚደረግበት አካሄድ ነው፡፡ ከፓርቲያዊ ቁጥጥር ውጪ ደግሞ በቋሚና ልዩ ኮሚቴዎች አማካይነት የሚደረጉ ቁጥጥሮችም አሉ፡፡ ሹመኞችን ጠርቶ በመጠየቅና ሪፖርት እንዲያቀርቡ በማድረግ፤ የመተማመኛ ድምፅ በመንፈግና ባለሥልጣናት ሲሾሙ የማጽደቅ፣ ኋላም የማውረድ ሥልጣን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ የቁጥጥር ሥልቶች ጥንካሬና ውጤታማነት የሕግ አውጪውና አስፈጻሚው ያላቸው ግንኙነት በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ከአስፈጻሚው ይልቅ ሕግ አውጪው ጠንካራ፣ ብሎም ጫና ፈጣሪ ሲሆን፣ በበርካታ አገሮች ግን የዚህ ተገላቢጦሽ ነው፡፡ በአንዳንድ አገሮች ደግሞ ሁለቱም ተቋማት የተመጣጠነ ሥልጣን አላቸው፡፡ እንደ እንግሊዝ ዓይነት ግትር ያልሆነ ሕገ መንግሥት ያለው አገር ደግሞ ፓርላማው ከአስፈጻሚው ጋር ሁልጊዜም ተገዳዳሪና ተነፃፃሪ ሥልጣን እንዲኖረው ይጥራል፡፡ በመሆኑም ሥልጣናቸው በሕግ ከተገደቡት በተሻለ ሁኔታ ፓርላማው አስፈጻሚውን ሊቆጣጠር ይችላል፡፡

በፓርላሜንታሪያዊ ሥርዓት የተወሰኑ የአስፈጻሚው አካል የፓርላማ አባላት ስለሚሆኑ ከሥልጣን ክፍፍል አንፃር የተዛነቀ ነው፡፡ ከፍተኛ የፓርቲ ባለሥልጣናት የሆኑት በሁለቱም ቦታዎች ስለሚገኙ የቁጥጥሩ ሒደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ የገዥው ፓርቲ ሊቀመንበር እንደ ምክትል ከሆኑና እንደ ኢሕአዴግ በጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚመራ ከሆነ በፓርቲው መዋቅር የበታች እርከን ላይ የሚገኙ አባላት ምንም እንኳን የፓርላማ አባል ቢሆኑም ቅሉ አለቆቻቸውን ይቆጣጠራሉ ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፡፡

ፓርላሜንታያዊ ሥርዓት መገለጫው ሚኒስትሮችን ወይንም ካቢኔዎችን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ሹመት የማጽደቅ ሥልጣን መኖር ነው፡፡ የሾማቸውን ሚኒስትሮችም በመጥራት አፈጻጸማቸውን ሊገመግም ይችላል፡፡ ሲወርዱም እንዲሁ ማጽደቅ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ፣ ሚኒስትሮችም ሆኑ የክልል የቢሮ ኃላፊዎች ሹመት በምክር ቤቶቹ መጽደቅ እንዳባቸው በሕግጋት መንግሥታቱ ላይ ተደንግጓል፡፡ የሾመው አካል ነው ተመልሶ ከሹመት መነሳትን ማጽደቅ የሚችለው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት የተደረጉት የሹመኞች ሽረት ከዚህ በተፃራሪው ነው፡፡ የወረዱበትን ምክንያትም ይሁን መሻራቸውን ምክር ቤቶች ሲያጸድቁ አልተስተዋለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ አስፈጻሚው አካል የተጣለበትን ኃላፊነት ሳይወጣ ቢቀር ሕዝብ የቱንም ያህል ቢቃወም የመተማመኛ ድምፅ እንዲጠይቅ የሚያስገድድ ሕግ የለም፡፡ ምናልባት በፓርቲ ደረጃ የመተማመኛ ድምፅ ሊሰጥ ይችል ይሆናል፡፡ ከዚያ ውጪ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማውረድ ቢፈለግ ምርጫ በተደረገበት ወረዳ የሚኖሩ መራጮች ሊያወርዱት ከሚችሉት በስተቀር የመተማመኛ ድምፅ በመንፈግ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይሁን ካቢኔውን ማፍረስ አይቻልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በተቃራኒው ፓርላማውን የመበተን ሥልጣን አለው፡፡

መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሲባል የተዋቀሩት ተቋማት ውስጥ የእንባ ጠባቂና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሰብዓዊ መብትን ከማስፋፋትና ከማስጠበቅ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማረምና ለማስተካከል ሲባል የተቋቋሙ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ባለፈው ዓመት የተነሳውን ችግር ከመቅረፍ አኳያ እምብዛም የጎላ ድርሻ አልነበራቸውም ማለት ይቻላል፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በተወሰነ መልኩ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እስከተወሰነ ጊዜያት ድረስ የተፈጸሙትን መንግሥታዊ ችግሮች ማጣራቱ እርግጥ ነው፡፡ የእንባ ጠባቂው ተቋም ግን መንግሥት ያስለቀሰውን ሰው እንባ ሲጠርግ አልታየም፡፡

ባለፈው ዓመት ላይ የሕዝብ አጀንዳ ከነበሩ የመጥፎ አስተዳደር ምሳሌዎች ውስጥ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ወጥቶባቸው ስኳር ማምረት ያልጀመሩት ፕሮጀክቶች ለዚህም በዋና እንቅፋትነቱ ስሙ የተነሳው ሜይቴክ አንዱ ሲሆን፣ የቤቶችና የከተማ ልማት ሚኒስቴር ደግሞ ከኮንዶሚኒየም ግንባታ ጋር በተያያዘ ከሰማንያ በላይ ሳይገነቡ ቀርተዋል  ወይንም ጠፍተዋል መባላቸው ሌላው ነው፡፡ እነዚህ ሪፖርቶች ፓርላማ ላይ የቀረቡ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በአደባባይ ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶችን የሰማው ወንጀልን የመመርመር ግዴታ ያለበት የፖሊስ ተቋም ምርመራ ስለማካሄዱ ወይንም ስለመጀመሩ የተሰማ ነገር ወይንም ፍንጭ የለም፡፡ የፌዴራሉ ኦዲተር ጀኔራል የበርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን የሒሳብ አያያዝና የግዥ ዝርክርክነት ለፓርላማው ሪፖርት ቢያቀርብም ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ግን አልተሰማም፡፡ ፖሊስም ከዚሁ ጋር የሚያያዙ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ምርመራ ስለማድረጉ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ የቀድሞው የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋም እንዲሁም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉም እንዲሁ ምንም ማድረጉ አይታወቅም፡፡ የሕግ ተጠያቂነትን በጥልቀት በመታደስ የተለወጠ ካልሆነ በስተቀር እነዚህ ግዴታዎች አለመወጣት የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አንፃር ዳተኛ መሆን ነው፡፡

በጥልቀት መታደስና የባለሥልጣናቱ ሀብት

ከላይ የተገለጹት ተቋማት የመንግሥትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የራሳቸው ድርሻ አላቸው፡፡ ‹‹ተጠያቂነት የጥንቃቄ እናት ናት›› ይባላል፡፡ ተጠያቂነት የሠሩትን ሥራ የወሰኑትን ውሳኔ ለምን እንደወሰኑ በፖለቲካ ከፍ ላለው አካል፣ ለአብነት ለሕግ አውጪው፣ አሊያም በሕግ የመጠየቅ ሥልጣን ላላው አካል ማስረዳትን ያስከትላል፡፡ ስህተት ከተፈጸመም ኃላፊነትን ያመጣል፡፡ በሥራ ኃላፊ የሆነበትን ሥልጣን በውክልና ማስተላለፍ የሚቻል ቢሆንም፣ ተጠያቂነትን ግን አይቻልም፡፡ በተለያዩ መንገዶች የመንግሥትን ሀብት ወደ ግል ሊዞር ስለሚችል፣ ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠርና ተጠያቂነት ያለበትን አሠራር ለመዘርጋት እንዲረዳ ከተቀየሱት ሥልቶች አንዱ የባለሥልጣንን ሀብት ለሕዝብ ማሳወቅ ነው፡፡  

በበርካታ አገሮች ባለሥልጣናት ሀብታቸውን የማሳወቅ ግዴታ የሚጥል ሕግና ይሄንኑ የሚያስፈጽሙበት ተቋማትና ሥልት አላቸው፡፡ ሀብትን ከማሳወቅ በተጨማሪም በተለያየ እርከን ላይ የሚገኙ ወይንም የሚሾሙ ባለሥልጣናት እንደ አመራር ባለሙያ ሥራቸውን እንዴት ማከናውን እንዳለባቸው የሚገልጽ የሥነ ምግባር ደንብ አላቸው፡፡ ሀብት የማሳወቅም ይሁን የአመራር የሥነ ምግባር ደንብ በርካታ ዓላማዎች ቢኖሯቸውም፣ በጥቅሉ ግን መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የአስፈጻሚውን አካል አሠራር ግልጽ ተጠያቂና ምላሽ ሰጪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

በኢትዮጵያም፣ በፌዴራልም ይሁን በክልል ያሉ ሹመኞች ሀብታቸውን ማሳወቅ እንዳለባቸው የሚያስገድዱ ሕጎች ከወጡ ሰንብተዋል፡፡ ሹመኞቹም አለን ያሉትን ሀብት ሲያስመዘግቡ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ መዝጋቢው አካል ካልሆነ በስተቀር ሕዝቡ ግን እስካሁን ሊያውቅ የሚችልበት ሁኔታ አልተበጀም፡፡ ሀብትን ማሳወቅ ግልጽነትን ስለሚጭምር ዜጎች በመንግሥት አስተደዳር አመኔታ እንዲኖራቸው ይረዳል፡፡ ፖለቲከኞችም በሕጋዊ መንገድና ከሹመታቸው በፊት ያፈሩትን ሀብት ካሳወቁ ኋላ ላይ በሕገወጥ መንገድ፣ ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀምና በፖለቲካዊ ብልግና የሚያጋብሱትን በቀላሉ ለመለየት ያስችላል፡፡ በመሆኑም በሹመት ምክንያት የመንግሥትና የሕዝብን ሀብት በመዝረፍ የሚመጣ የሀብት ልዩነትን ለመቀነስ ይጠቅማል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሹመኞች የጥቅም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ተግባራት ውስጥ እንዳይሳተፉ ለመከላከል ይረዳል፡፡ በእርግጥ ሀብትን ማሳወቅ የታለመለትን ግብ የሚመታው ነፃ ሚዲያ ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማት ታማኝ የመንግሥት ሠራተኛ/ሲቪል ሰርቫንትና ኃላፊነት የሚሰማው መሪ ሲኖር ነው፡፡

ባለሥልጣናት ሀብታቸውን እንዲያሳውቁ የሚያስገድደው ሕግ ከወጣ ዓመታት ቢቆጠሩም ብሎም እንደ ሕጉ ቢዘመገብም ለሕዝብ ግን ግልጽ አልሆነም፡፡ በበርካታ አገሮች አንድ ሹመኛ ሲመቱ ከመጽደቁ አስቀድሞ የራሱን ብቻ ሳይሆን የቅርብ ዘመዶቹንም ሀብት ጭምር የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ የኢትዮጵያው ሕግ ይህ እንዲሆን ባያስገድድም፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዞ መገኘት ግን ወንጀል የሚሆነበትን ሥርዓት አብጅቷል፡፡ በሕጋዊ መንገድ እንደተገኘ እስካላስረዳ ድረስ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡

የአስተዳደር ሕግ ማውጣት ለምን ተፈራ?

የሥልጣን ክፍፍል ባለበትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሕግ አውጪው እንዴት ሕግ ማውጣት እንዳለበት ሕግ አስፈጻሚው እንዴት ሕግ አውጪው ያወጣውን ሕግ እንዴት ማስፈጸም ወይንም ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት እንዲሁም ሕግ ተርጓሚው ደግሞ ሕግ የሚተረጉምበትን ሥርዓት የሚወሰን ሕግ አላቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ሕግን በማስፈጸም ሥራ ላይ የተሰማራው የመንግሥትን አካል አሠራር የሚደነግግ ሕግ ከሌለ በቅድሚያ ሕግ አውጪው ያወጣው ሕግ በአግባቡ ላይፈጸም ስለሚችል ዓላማውን ማሳካት ይሳነዋል፡፡ ሁለተኛ ዜጎች ከአስተዳደራዊ ተቋማት የሚያገኟቸውን አገልግሎቶች በፍትኃዊነት፣ በገለልተኝነት፣ ግልጽነት በተሞላበት መንገድ ለማግኘት እንቅፋት ይሆናል፡፡ ሦስተኛ ደግሞ ዜጎች አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚያገኙበትን ሥርዓት ስለሚዘረጋ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡ በመሆኑም፣ የአስተዳደራዊ ሕግ አለመኖር ባለሥልጣናት ተጠያቂ እንዳይሆኑ ማመቻቻ ዘዴ ነው፡፡ ስለሆነም፣ የአስተዳደር ሕግ መኖር መልካም አስተዳዳር ለማስፈን ዓይነተኛ ሚና አለው ማለት ይቻላል፡፡

የአስተዳደር ሕግ መነሻ በመንግሥት መካከል የሥልጣን ክፍፍል መኖሩ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ፓርላማው (ሕግ አውጪው) አስፈጻሚውን ከሚቆጣጠርበት ዘዴ አንዱ ሕግ የሚያስፈጽምበትን ሥርዓት በማስቀመጥ ነው፡፡ የሚያስፈጽምበትን አሠራር አለማስቀመጥ ወይንም በተለያየና በተበጣጠሱ ሕጎች ማስቀመጥ ተገልጋዩ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚውም በአግባቡ እንዳያውቃቸው ማበረታታት ነው፡፡ የአስተዳዳር ሥርዓት በግልጽ አለመታወቁ መጥፎ አስተዳደርን ስለሚያመጣ ሹመኞችና ባለሥልጣናት እንዳሻቸው እንዲሆኑ ስለሚረዳቸው የሕዝብን ጥቅም ወደ ግል በማዞር ሀብት ለማካበት መንገድ ያሳልጣል፡፡

የአስተዳደር ሕግ የሚያካትታቸው ሥርዓቶች አሉት፡፡ እነዚህም አስፈጻሚው አካል ውሳኔ የሚወስንበትን የሕግ ማዕቀፍ እንዲሁም ሒደቱንና ቅደም ተከተሉን የሚተልም ብሎም የሚስገድድ ሥርዓት ማበጀት የመጀመሪያው ነው፡፡ በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሰጡ ውሳኔዎች በዚያው በመሥሪያ ቤቱ የሚከለሱበትን ዘዴም ይዘረጋል፡፡ በመሥሪያ ቤቱ በራሱ ከሚደረገው ክለሳ በኋላ በፍርድ ቤት የሚታይበትን ሥርዓትንም ይይዛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፓርላማው፣ እንባ ጠባቂው፣ የሰብዓዊ መብት፣ በኦዲተር ጀኔራልና በሌሎች ተቋማት ቁጥጥር የሚደረግበትንም ሁኔታ ያካትታል፡፡ የአስተዳደር ሕግ ዓላማዎች፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ጥራት ያለውና ፍትኃዊ ውሳኔ ዜጎች እንዲያገኙ ማድረግ፤ አስፈጻሚው አካል የሰጣቸው ውሳኔዎች ቅልጥፍና ከገደላቸው፣ እንከን ካለባቸው፣ ኢፍትሐዊ ከሆኑ በመደበኛ ወይንም በአስተዳደራዊ ፍርድ ቤቶች ዜጎች የሚያስከልሱበትን ሥርዓት ይዘረጋል፡፡ አስፈጻሚው አካልም ለሚወስናቸው ውሳኔዎችንም ሆኑ ለየትኞቹም ድርጊቶቹ ተጠያቂ እንዲሆን ስለሚያደርግ የመንግሥትን አመል ይገራል፡፡ ሕዝቡም ስለ መንግሥት አሠራርና ውሳኔዎች፣ ግለሰቦችም ስለ ራሳቸው ጉዳይ መረጃ የሚያገኙበትን ሥልት በመቀየስ መንግሥት ላይ ግዴታ ይጥላል፡፡

የአስተዳዳር ሥነ ሥርዓት ሕግ ማውጣትና መተግበር በርካታ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ውሳኔ ሰጪዎች በሕግ የተሰጧቸውን የመወሰን ሥልጣን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የሚያሳይ መመርያዎችን ያስቀምጣል፡፡ ሌላው ደግሞ በተለይ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ባሉባቸው አገሮች የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን የሥራ ጫና ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም በአንድ አገር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ተመሳሳይ የሆነ አስተዳደራዊ ፍትሕ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ ቦታና አካባቢን መሠረት ያደረገ ልዩነት ያስቀራል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ አስተዳደር ሕግ መኖር ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ ይረዳል፡፡ የዜጎችን ተሳትፎ ያሳድጋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ያረጋግጣልል፡፡ መንግሥታዊ ተቀባይነትን እንዲሻሻልም ያደርጋል፡፡ መብቶችንና ጥቅሞችን ማስከበሪያና እንዳይጣሱ መከላከያ ጋሻም ይሆናል፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ላይ በመልካም ሁኔታ የማስተዳዳር ግዴታን ይጥላል ማለት ነው፡፡ አስተዳደር ሕግ ቢኖር ኖሮ መንግሥትም በየጊዜው መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ፣ የዜጎች ቻርተር፣ በጥልቀት መታደስ ወዘተ. በማለት ራሱም እነዚህ ነገሮችን በመቀያየርና ሥራ ላይ በመጠመድ ፋንታ ጊዜውንም ሀብቱንም ለሌላ ጉዳይ ማዋል ይችል ነበር፡፡ ሕዝብም በየጊዜው አይደነጋገርም፤ መብትና ግዴታውንም በአግባቡ መለየት ያስችለው ነበር፡፡

የአስተዳደር ሕግ የሚመለከተው የአስፈጻሚውን አካል በመሆኑ ፖለቲካን መግሪያ በመሆን ያገለግላል፡፡ ፖለቲከኛ በሕግ ካልታረቀ ብሩም ጉልበቱም ስላለው በባህርይው  የዜጎችን መብት ይጥሳል፡፡ ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ሕጎች ደግሞ ይህንን ባህርይ በመግሪያነት ያገለግላሉ፡፡ በመሆኑም፣ የተለያዩ ጊዜያዊ አሠራሮችን በተደጋጋሚ ከመቀያየር በርካታ አገሮች የሚሠሩበትን የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግን በማጽደቅ ሹመኞችና ሠራተኞች በምን ዓይነት ሁኔታ ሥራቸውን ማከናውን እንዳለባቸው፣ ዜጎችም ከዚህ አንፃር ያላቸውን መብቶች እንዲያውቁ ማድረግ ተመራጭ ነው፡፡

መንግሥታዊ አሠራር የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና ሥርዓትንና ተቋማትን በመገንባት ብሎም እነዚህን በታማኝነት ማክበርን ይጠይቃል፡፡ መንግሥታዊ አሠራር በፓርቲያዊ ብሂሎችና ውሳኔዎች የሚገዙና የበታች መሆን የለባቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲም ቢሆን ከሕግ በታች መሆን አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ለተቀመጡ ግዴታዎች ታማኝ በመሆን ማስፈጸም የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን ለፓርቲ ጥቅም እንዲውል ማድረግና የሕግ መሠረት የሌላቸውን ነገር ግን ተጠያቂነትን የሚያድበሰብሱና የሚሸፍኑ ድርጊቶችን ማስቀረት ተገቢ ነው፡፡ የሕግ ተጠያቂነትን የማያሰፍን የወንጀልና የአስተዳደር ኃላፊነትን የማያመጣ አሠራርን መከተል ለሙሰኞች ሽፋንና ከለላ መሆን ነው፡፡ በጥልቀት በመታደስ በሂስና በግለ ሂስ ከመጠየቅ ከታዳነ፡-

‹‹ … ሰው እየገደሉ ይማራል ወይ ነፍስ፣

ሰው እየገደሉ ከተማረ ነፍስ፣

ቱቦሽን ዘግቼ ደብረ ሊባኖስ::››  እንዳለው አዝማሪ ነው ትርፉ፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነት የወደመውን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠገን ተቋራጮች ሊመረጡ ነው

ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ምትክ...

ለአደጋ መከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ የድንገተኛ እሳትና አደጋን ለመከላከልና በፍጥነት ምላሽ...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ...

ብሔራዊ ባንክ ኅብረተሰቡና ባንኮች በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች እንዳይጭበረበሩ አሳሰበ

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በማሳተምና በማሠራጨት ግብይት ላይ ለማዋል ጥረት...