Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች እጃችሁ ከምን?

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች እጃችሁ ከምን?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

በተሃድሶው ዜና ሒደት ውስጥ ኢሕአዴግ ብዝኃነት ያለው ኅብረተሰብ መኖሩን መገንዘቡን፣ ይህ ብዝኃነት በብሔርና በሃይማኖት ብዝኃነት ላይ ብቻ እንዳልተወሰነና በኢኮኖሚና በፖለቲካ ፍላጎቶችም ብዝኃነት እንዳለ መረዳቱን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል የሚችል ኅብረተሰብ አይደለም ማለቱን በአደባባይ ሰምተናል፡፡ ይኼ በገዢው ፓርቲ በኩል የተሰጠ ታላቅ የዕምነት ቃል ነው፡፡

ለዘላቂነቱና ለተግባራዊነቱ (በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል የሚዋደቁለት) ታላቅ መርህ ነው፡፡

- Advertisement -

የዚህ እውነትና ዕምነት ሌላው ገጽታ በኅብረተሰቡ መሠረታዊ ሀቆችና ልዩ ልዩነቶች ላይ የተፈተለ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ልዩ ልዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ዓርማ አበጅቶ፣ ስም ሰጥቶ፣ አቅጣጫ ቀይሶ ከተለያዩ ሐሳቦች ጋር ውድድር እየገጠመ ሐሳብን በሐሳብ እየረታ ተቀባይነት እያገኘ፣ ይኼንንም ላረጋግጥ ብሎ ቆርጦ የተነሳ የተቃውሞ ኃይል ግድ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ታላቁ ጉድለትም ይኼንን ግዴታ መወጣት የሚያስችል የተሳካለት ትግል አለማድረጋቸው ነው፡፡ ትናንሽ ቡድን እየፈጠሩ ካብ ለካብ እየተያዩ የመያያዝን ኃላፊነት እምቢ እያሉና በተናጠል እየቆሙ፣ እርስ በርስ እየተጠላለፉ ለሚገኙበት ውድቀትና ድክመት ተዳረጉ፡፡

በፖለቲካው ሜዳ ውስጥና በምርጫ ቦርድ የፓርቲዎች ምዝገባ ስታትክስቲክስ ውስጥ ከስድሳ በላይ ወይም ሰባ ምናምን ያህል ፓርቲዎች ወይም የፖለቲካ ቡድኖች መኖራቸውን እንሰማለን፡፡ በእነዚህ ቡድኖች መካከል የመተባበር፣ የመሰባሰብ፣ ኅብረት የመፍጠር ጥያቄና ጥሪ ሰሞኑን የሚሰማ አጀንዳ ሆኗል፡፡

በጠራ የፖለቲካ ግብ ላይ ጠንካራ ኅብረት ፈጥሮ የአገሪቷን ሕዝቦች ተቀባይነት ለማግኘት በቁርጠኝነት ከመታገል የተሻለ አማራጭ ስለሌለ መበረታታት የሚገባው ነው፡፡ ዘላቂ ትብብር የመፍጠር ነገር ደግሞ ወሳኝ ባልሆኑ ዓላማዎች ከመወሰን ወጥቶ፣ ተቀዳሚ በሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጉዳዮች ላይ ለመረባረብ የማያወላውል ስምምነት ማድረግ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ አቅጣጫ ለመጓዝ ተቃዋሚ ኃይሎች መጀመርያ ኢዴሞክራሲያዊነትን ማራገፍ፣ መስመሮቻቸውን በአግባቡ ማቀራረብ፣ በየፀበላቸው መሰባሰብ፣ ከተጠርጣሪና ከመሰሪ ሥሌትና ከጠባብ ሥልጣን አፍቃሪነት መላቀቅ፣ የአገሪቱ መላ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተያያዙበትን ጠንካራ የትግል ትብብር ማበጀት፣ ከጥላቻ የፀዳ ፊት ለፊት ለመግለጽ የማያፍሩበትና ተከራክረው የሚረቱበት አቋም የላቸውም ከሚል ሐሜትና ክስ ራሳቸውን ነፃ ማድረግ አለባቸው፡፡

ለዚህ ይረዳቸወ ዘንድ የሚከተለውን ሐሳብ አቀርባለሁ፡፡ 

 1. አሳሳቢ ችግሮችና አጣዳፊ ተግባራት
 • በየክፍለ ዓለሙ አገሮች በተለየየ መልክ የሚያካሄዱት የመሰባሰብ ሒደት የመነጠል እንቅስቃሴን ከዓለም የጉዞ አቅጣጫ ጋር የሚቃረን አድርጎታል፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥም ከኤርትራ ልምድ ወዲህ የከሰረ እንቅስቃሴ ሆኗል፡፡ የታሪክ ቅሬታን ለመወጣት ሲባል ካልሆነ ወይም ውጤቱ ምንም ሆነ ምንም መነጠል ፍላጎቴ ነው ካልተባለ በቀር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች መሠረታዊ ችግሮች በመለየት /በመለያየት የሚፈቱ አይደሉም፡፡ መለየት/መለያየት መፍትሔ አያስገኝም ብቻ ሳይሆን፣ ዴሞክራሲና ዕድገትን ከመንሳትም በላይ ሕግና ሥርዓት የሚያሲዝ መንግሥት የማግኘት ዕድልን በሚያሳጡና የማያልቅ የግዛት መናጠቅን በሚያስከትሉ ጦርነቶች ውስጥ ሊያስገባ ይችላል፡፡ ሲጠራቀም የቆየው የኢኮኖሚና የአዕምሮ ድህነት በራሱ የመፋጀት እብደት ውስጥ ሊከት ይችላል፡፡
 • በአንድ ወቅት የታወቀ የቅኝ ግዛት ወሰን የነበራት የዳር አገሯ ኤርትራ እንኳን ተነጥላም ከኢትዮጵያ ጋር ከጠብ ግንኙነት አለመውጣቷ፣ መለያየት ቀላል እንዳልሆነ፣ የሁለቱም ኢኮኖሚያዊ ህልውናና ዕድገት የተጣበቀ መሆኑን፣ ይኼን ሀቅ ክደው እስከቆዩ ድረስም በክፉ ላለመደራረስ ቢማማሉ እንኳን አንዳቸውም ሰላምና መረጋጋት እንደማያገኙ አረጋግጧል፡፡
 • ከኤርትራ ቀጥሎ ረጅም ጊዜ የመነጠል ጥያቄ የተነሳበት፣ ዛሬ ባለው አወቃቀር መሠረት ከትግራይ በቀር ከሁሉም ክልሎች ጋር የሚዋሰነውና የአገሪቱ ሕዝቦችና መልክዓ ምድር ዋንጫ የሆነው ኦሮሚያ ቢነጠል ደግሞ የሚፈጠረውን ትርምስ መገመት አያዳግትም፡፡ የኦሮሚያ መነጠል ማለት አንድ አገር ራሷን የምታጠፋበት ሒደት ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ኦሮሚያ ከዙሪያው ክልሎች ጋር ይተጋተጋል በሚል ብቻ የሚታሰብ አይደለም፡፡ አንዴ ማዕበሉ ውስጥ ከተገባ በራሱ በኦሮሚያ ውስጥ ከብሔረሰቦች ግንኙነት፣ ጎጠኝነት፣ ከሃይማኖትና ከሥልጣን ጋር የተያያዙ ጣጣዎች ብዙ ነገር ሊያመጡ የሚችሉ ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም ነገን በማያስቡ ተንኮሎች ተቃዋሚዎችን እያደቀቀ የተሻለ የፖለቲካ አማራጭ በማሳጣትና ‹‹ብቻ እንዳንተላለቅ›› በሚል ሥጋት ኅብረተሰቡን ተጨብጦ እንዲቆይ ባደረገ ተግባሩ አገሪቱን ለምናወራለት አስፈሪ ሁኔታ እያዘጋጃት እንዳይሆን ቢሠጋ ጥሩ ነው፡፡ የተቃውሞን ሽውታና ልውሻ ለማሳደድ የአፈና መረቡን ከዳር ዳር ሲያንቀሳቅስ ተራ ሕገወጥነትን መቆጣጠርና የዕምነት መብትን ማስከበር ግን ተሳነውና ተንኳሽ ስብከቶችን ማካሄድ፣ የአንድ ሃይማኖት የዕምነት ቦታን ወይም ክብረ በዓልን የሌላ ሃይማኖት ሰዎች የሚዳፈሩበት አጉል ጠበኝነት እየተበራከተ፣ በመቻቻል የሚታወቁት ሃይማኖቶች አስፈሪ ቅያሜዎችና ግጭቶች ወደ መውለድ እንዲያመሩ ሆነዋል፡፡
 • ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ውጊያ ውስጥ ከገባች የግዛት ጥያቄ አለን የሚሉም ሆኑ በግርግር መሬት ልመንትፍ ያሉ አገሮች ቅርጫ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም፡፡ መቀራረጡ ተካሂዶ አቅመ ቢስና ፍርስራሽ የበዛባቸው ትንንሽ አገሮች መፈጠር ቢችሉ እንኳን፣ የዓለም የአየር ንብረት መዛባትና የበረሃማነት መስፋፋት ያባባሰው የውኃዎችና የመሬት ንትርክ አይለቃቸውም፡፡ ከኢትዮጵያ በሚወጡ ወንዞች ላይ የተደገፈ ህልውና ያላቸው አገሮችም፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከአዙሪት እንዳይወጡና ውኃዎቹን ለማልማት የሚያስችል መረጋጋት እንዳያገኙ ለማድረግ ከበፊቱ የበለጠ ይቀላቸዋል፡፡ ይኼንንም ከማድረግ አይመለሱም፡፡ በብሔረሰባዊ በሃይማኖታዊ ቅራኔዎች ውስጥ መግባት የጠላቶችን ፍላጎት መሙላት ነው፡፡ በውኃዎች ላይ ያለው የጥቅም ግጭት እንኳንስ ኢትዮጵያ ተቆራርሳ አሁን ባለችበትም ይዞታ ቢሆን ብዙ ትግል ያለበት ነው፡፡ በትልልቅ ወንዞች ላይ የሚካሄድን የኤሌክትሪክ ኃይልና የመስኖ ልማትን ወደ ጎን ትተን፣ ተንደርዳሪ የዝናብ ጎርፍን ጥፋት ለመግታት የሚካሄደው ልማትና ውኃን የመሰብሰብ እንቅስቃሴም በዋዛ የሚታይ አይሆንም፡፡ የዝናብ ዕጥረት የሚያደርሰው ለውጥ ሳይቀር በደባ ሊጠረጠር የሚችል ነው፡፡ የቱርካና ሐይቅ በመጉደሉ ምክንያት ኬንያ ውስጥ ተከስቶ የነበረው ማንገራገር ተቃሎ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ የልማት ተግባራችን ትርፉ ከጎረቤት እየተናጩ መዳከር ብቻ እንዳይሆን በጥንቃቄ መቀየስንና የጋራ ጥቅም ላይ መመርኮዝን፣ ቀዳዳ የማይሰጥ የውስጥ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሰላም መፍጠርን፣ ፈጣን የኢንዱስትሪ ዕድገት ውስጥ መግባትን በዚያው ልክ ወታደራዊ አቅምን ማሳደግን ይጠይቃል፡፡
 • በዚህ መስመር ውስጥ ኢትዮጵያ መግባት ችላም ቢሆን በቅርብ ጎረቤቶቿ ዘንድ የመረጋጋትና የዕድገት አዝማሚያ እስከሌለ ድረስ ስኬቷ በአደጋ ውስጥ ነው፡፡ ከጎረቤት የሚዛመት ግጭትና ጦርነት፣ በሃይማኖት የተሸፈነ ተስፋፊነትና ሰላም አደፍራሽነት ከድህነት ጋር ተጋግዞ የሚያስከትለው ጥፋት ሊያበጣብጥ የሚችል መሆኑ እየታየ ነው፡፡ እናም አገራዊ አንድነትንና ዴሞክራሲን የጨበጠ የዕድገት ትግልም ቢሆን በቀንዱ አካባቢ መረጋጋትና ዕድገት እንዲመጣ ከመጣጣርና ከመተጋገዝ ጋር የማይነጣጠል ነው፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ነጥቦች የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብሮ መሆንና ለተሻለ ሕይወት መፍጨርጨር በአሁኑ ደረጃ በድምፅ ሳጥን የሚለካ፣ ወይም የተወሰኑ ቡድኖች በሬፈረንደም እንጨርስ ብለው የሚማማሉበት የውዴታ ነገር ሳይሆን የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ይኼንን መሳት ኢትዮጵያውያን ከድህነት እንዳይወጡ የሚሹ ወገኖች በሚፈልጉት መንገድ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል፡፡ ረሃብንና ፀረ ዴሞክራሲን የመላቀቅ ፍላጎታችን ያስቀመጠልን የሚያወጣ አማራጭ በተባበረ ኃይል ሕዝቦችን አንቀሳቅሶ መታገልን ነው፡፡ የቅስቀሳና የኅብረት ትግል ማደራጂያ ምሰሶ መሆን ያለበትም፡፡ ይኼ አጣዳፊና ወሳኝ ተግባር ነው፡፡ ኅብረትን በማይታጠፍ የአገር አንድነት ቅድመ ሁኔታ ውስጥ የሚሰነቅሩ ወይም በ1997 ዓ.ም. ይሉት እንደነበረው በተመድ መመዘኛ መሠረት መገንጠል ተቀባይነት የሚኖረው በቅኝ መገዛት ወይም በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠቃት ካለ ስለሆነ፣ እነዚህ በሌሉበት መገንጠልን አንቀበልም (በውስጠ ታዋቂ መመዘኛውን አሟልታችሁ ኑ) እያሉ ያሉ፣ በሌላ በኩል ‹‹ሕዝባችን በባርነት ቀንበር ውስጥ ይገኛል›› የሚል የተናጠል ጩኸት እያጦዙ ገዢዎች ለሚፈልጉት የተቃውሞ መከፋፈል ዕድሜ የሚሰጡ ወገኖች ሁሉ አስተሳሰባቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፡፡

 1. በኅብረት ጉዞ ላይ የሚደነቀሩ አንዳንድ ጉዳዮች

ሀ. የብሔረሰቦች መብት መነጠልን ይጨምራል ወይስ አይጨምርም?

ኅብረ ብሔራዊና ብሔረተኛ ቡድኖች ጉድኝት ለመፍጠር ሲሞክሩ በብሔረሰቦች ጉዳይ ላይ የመግባባት ጥያቄ ይነሳል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለች የብዙ ብሔረሰቦች አገር ውስጥ ሆኖ የብሔረሰቦችን መብት አላውቅም ወይም ያሰጋኛል የሚል ካለ ከተጨባጩ እውነታ ውጪ ለመሆን የወሰነ ነውና ያንን ለማሳመን አንደክምም፡፡ ዋናው ችግር ያለው የመገንጠል መብት ላይ አቋምህ ምንድነው የሚባል ነገር ሲመጣ ነው፡፡

‹‹መብት እስከ መገንጠል›› የሚባል ነገር የአድሃሪና የተራማጅ ወይም የፀረ ዴሞክራትና የዴሞክራት መለያ አይደለም፡፡ ስለእውነቱ እንነጋገር ከተባለ የመገንጠል ‹‹መብት›› ጠበቃ የሆኑና ሌላውም እንደነሱ እንዲያስብ የሚፈልጉ ቡድኖች ጥብቅናቸው ለመገንጠል ዋስትና ይሆነኛል፣ ወይም አንድነትን ለማዝለቅ ይጠቅመኛል ከሚል የመጣ እንጂ መጓደል የሌለበት አስፈላጊ መብት ነው ከሚል የልብ ዕምነት የመጣ አይደለም፡፡ መገንጠልን መብት አድርገው በሕገ መንግሥት የጻፉ አገሮች በተግባር መብቱን ሲያረጋግጡ አልታዩም፡፡ በምሥራቅ አውሮፓ ያየነው መለያየት የመፈራረስ እንጂ የዚህ መብት ውጤት አልነበረም፡፡ ኢሕአዴግም ቢሆን የመገንጠልን ‹‹መብት›› በሕገ መንግሥቱ ያሰፈረው የመገንጠል ፍላጎቶችን ‹‹ለማታለል›› እንጂ በተግባር እንደማያውለው የታወቀ ነው፡፡ ለመነጠል የሚፈልጉም የተነጠለ አገር ለመፍጠር በቅተው መንግሥት ቢሆኑና በውስጣቸው ካሉ አናሳ ብሔረሰቦች ወይም በቋንቋ አንድ ከሆነ የሕዝብ ክፍላቸው የተወሰነው አካባቢ መነጠል እሻለሁ ቢል መብቱ ነው ብለው ሕዝበ ውሳኔ ለማስደረግ እንደማይከጅሉ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

እንደዚያም ሆኖ ለመነጠል በመፈለግም ይሁን በአንድነት ለመቀጠል ዋስትና ይሆናል በሚል ምክንያት ‹‹የመነጠል መብት››ን አቋማቸው ያደረጉ፣ በአንፃሩም መብትነቱን የማይቀበሉና ጭራሽ የኢትዮጵያ አንድነት ላይ ድርድር የለም የሚሉ የፖለቲካ ወገኖች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ቦታ ይዘው ይገኛሉ፡፡ የሁሉንም ሕዝቦች ህልውና የሚመለከተው የኢትዮጵያ አሳሳቢ እውነታ ደግሞ በትግል መተባበርን የግዴታ ተግባር አድርጎታል፡፡ ይኼንን ተቀዳሚ ተግባር ከመወጣት አኳያ ሲታይ ከትግል ኅብረት በፊት በመገንጠል መብት ላይ ወይም በሪፈረንደም ላይ መስማማትን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ ማስቀመጥ ስህተት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ነን በሚሉት በኩልም በቅድሚያ በአንድነት ላይ መስማማትን ከመነጠል ጣጣ መገላገያ አድርጎ መውሰድ ያው ነው፡፡ በተባበረ ትግል ዴሞክራሲን ሥር ማስያዝ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑ ላይ መስማማት ከተቻለ፣ ድርጅቶች በየበኩላቸው የመነጠልን መብትነት ማመንና አለማመናቸው ለኅብረት እንቅፋት መሆን የማይገባው መወዛገቢያ መሆን የሌለበት ትርፍ ነገር ነው፡፡ በሁለቱም በኩል ያሉ ሥጋቶችን የሚያስወግደው ቡድናዊ ውል ሳይሆን አምባገነንነትን አሸንፎ ዴሞክራሲና የተመጣጠነ ዕድገት ውስጥ መግባት ነው፡፡

ዴሞክራሲና የተመጣጠነ ዕድገት ውስጥ እስከተገባ ድረስ በኢትዮጵያ ያለው የብሔረሰቦች ሥርጭት ተቻችሎ ለመኖር የሚያመች ነው፡፡ ኦሮሞ በቁጥር እዋጣለሁ የሚል ሥጋት እንደሌለበት ሁሉ፣ በቁጥር አናሳዎቹ በኦሮሞ ወይም በኦሮሞና በአማራ የመዋጥ ሥጋትን የሚያስወግድ የብዛት ክምችት አላቸው፡፡ ዴሞክራሲ ፍላጎቶችን ለማስማማትና በደሎችንና ዝንፈቶችን ታግሎ ለማቃናት የተሻለ ነፃነት ይሰጣል፡፡ ፍትሕ፣ እኩልነትና ዕድገት እስከጎለበቱ የሕዝቦች ድምፅ እስከሠራና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በጠመንጃ ድጬ እገላገላለሁ እስካልተባለ ድረስ የመነጠል ጥያቄ ይደክማል፡፡ ማለትም በአንድነት ጠንክሮ ለመዝለቅ ዋስትና የሚሆነው (ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪዎች አዋጪ የሆነው) መንገድ ይኼ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአዲስ ወይ በነባር ምክንያቶች የመነጠል ጥያቄ የሚነሳ ቢሆን፣ ጥያቄው የፍለጠው ቁረጠው አገዛዝ ወይም የመተላለቂያ መዘዝ ሳይሆን በሰላምና በሪፈረንደም የመፈታትን ዕድል እንዲያገኝ የሚያስችለው (ከየትኛውም ሁኔታ በተሻለ) የዴሞክራሲ አስተዳደርና ባህል መገንባት ነው፡፡ እውነታዊ አስተሳሰብ ያለው ፖለቲከኛ ይኼንን አይስተውም፡፡

ለ. የብሔረሰብ መብትና የዴሞክራሲ ግንኙነት

በኢትዮጵያ ልምድ የብሔረሰቦች መብት የተወሰነ ተግባራዊነት ያገኘው ከዴሞክራሲና ከሰብዓዊ መብቶች ጋር ተጣጥሞ ባለመሆኑ ብልሽቶች ተፈጥረዋል፡፡  ብሔረሰባዊ አድሎና ጥቅም አባራሪነት ብሔረሰባዊ መብትን እንደ መተግበር ወይም ለብሔረሰብ እንደ መቆም እየተደረገ ይፈጸማል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነኝ የሚሉም ብሔርተኛ ቡድኖች ይኼንን ጥፋት በአግባቡ ለመቃወም አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት የብሔረሰብ መብቶችና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚፋለሱ አድርጎ የማየት ብዥታ ተፈጥሯል፡፡ ብሔረተኛው ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን የሚያጠብቀውን ቡድን በብሔረሰብ መብቶች ላይ አያምነውም፡፡ የኋለኛውም ብሔርተኛውን በሰብዓዊና በዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ አያምነውም፡፡

የብሔረሰብ መብቶች የዴሞክራሲ አካል ቢሆኑም መብቶቹ በቁማቸው ቅርፆች ናቸው፡፡ በራስ ቋንቋ የሚነበበውና የሚደመጠው የአፋኞች ውዳሴና ገናዥ ፕሮፓጋንዳ ወይም ነፃነትንና ፍትሐዊነትን የማስከበር መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ የራስ በራስ አስተዳደሩ ግፈኞች የሚፈነጩበት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ፣ በሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ሿሚነትና ጠያቂነት የሚቃኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን፣ ፍትሕንና ዕድገትን ለማረጋገጥ ያልቆረጠ ብሔረሰባዊ ታጋይነት ባዶ ልፋት ነው፡፡ ወሳኙ ጉዳይ ቀፎው ሳይሆን በቀፎው ውስጥ ያለው/እንዲኖር የሚፈለገው ሕይወት ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ሁለት ተፈጥሮ መያዝ (ለራስ ብሔረሰብ ዴሞክራሲንና ፍትሕን አዳይ፣ ከዚያ ውጪ ላለው በደልን አዳይ መሆን) አይቻልም፡፡ በየብሔረሰብ ወገን በኩል የሚፈጸሙ ጎሰኛ በደሎችን ያለማወላወል መታገል ውስጥ እስካልተገባ ድረስ፣ ኅብረ ብሔር ድርጅት ነን የሚሉትም የብሔረሰብ መብትንና ጎሰኝነትን አጥርተው መለየት እስካልቻሉ ድረስ ዜጎች ሁሉ በብሔረሰብ፣ በፆታ፣ በሃይማኖት የማይበላለጡበት ከሕግ ውጪ የማይከሰሱበትና የማይታሰሩበት፣ ቤታቸው የማይደፈርበትና ከስቃይ የሚጠበቁበት፣ ህሊናና አንደበታቸው የማይለጎምበት ሕዝባዊ አስተዳደር ማደራጀትና ማስቀጠል አይቻልም፡፡

መ. ባለው ሕገ መንግሥትና አከላለል ላይ አቋም መጠያየቅ

ባለው ሕገ መንግሥትና አከላለል ላይ ያሉት አቋሞች ብዙ ናቸው፡፡ አንዳንዱ ሕገ መንግሥቱንና አከላለሉን ተቀብሎ የኢሕአዴግን አገዛዝ ይቃወማል፡፡ አንዳንዱ የተወሰኑ ጉዳዮች ከሕገ መንግሥቱ ውጪ እንዲሆኑና በተወሰነ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ እንዲታረም ይፈልጋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተሽሮ በአዲስ እንዲተካ፣ የአካባቢዎች አከላለልም ልማትና አስተዳደርን በሚያቀላጥፍ ሁኔታ እንዲስተካከል የሚሻም አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከወዲሁ ካልተነጋገርን ማለት ቀዳሚና ተከታዩን ማምታታት ይሆናል፡፡ ያለውን መዋቅርና ሕገ መንግሥት እንዳለ ማቆየት፣ ማሻሻል ወይም መቀየር ሕዝቦች ወደፊት የሚጨነቁበት ሥራ ነው፡፡ ዛሬ ዋናው ፖለቲካዊ ጉዳይ ነፃና ሚዛናዊ ምርጫን መሠረት ያደረገ የዴሞክራሲ አስተዳደርን ታሪክ ለማስጀመር ተሰባስቦና አሰባስቦ መታገል ነው፡፡

አንዳንዶች ይኼንን ተግባር ከሽግግር መንግሥት መፈክር ጋር ያጣብቁታል፡፡ ይኼ የራሱ ችግር አለው፡፡ ኢሕአዴግ አምባገነንት ‹ዴሞክራሲ›› ለበስ በመሆኑ ከደርግ ይለያል፣ በምዕራባዊ ረጂዎቹም ዘንድ ከፋም ለማም የዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ተገብቷል የሚል አመለካከት አለ፡፡ ስለዚህ የሽግግር መንግሥት መፈክር እንደ ደርግ ጊዜ ሁሉን ሊያስማማ የሚችል አይሆንም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የ‹‹ሽግግር መንግሥት›› ሕገ መንግሥታዊ አይደለም፡፡ የተፈለገው ሕገ መንግሥቱን በሕገወጥ መንገድ ለመናድ ነው እያለ ለማወናበድና ውስጣዊ መከፋፈልን ለመፍጠር እንዲችል፣ ብሎም ኢሕገመንግሥታዊ ለሆነ የሥልጣን አያያዝ ድጋፍ ያለመስጠትን ዓለም አቀፋዊ አዝማሚያ መነገጃ በማድረግ ከድርድር ግፊት እንዲያመልጥ የሚመች ነው፡፡ ሕገ መንግሥት አክባሪና በሕጋዊ መንገድ የምንታገል ነን የሚሉትን ወገኖች ‹‹ሕገወጥነትን አጣቀሱ›› ለሚል ውንጀላ የሚያጋልጥና በዚህም ምክንያት ከጥያቄው እንዲርቁ የሚያደርግ ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ የሚሆኑ የጥገና ለውጦች በኃይል መንገድ ወይም ሕጋዊ ምርጫን ተከትለው የሚመጡ ስለመሆንና አለመሆናቸው አስቀድሞ አይታወቅም፡፡ የታሪክ ሁነቶች የሚወስዱት መንገድ በማንኛችንም ቁጥጥር ውስጥ እንዳለመሆኑ፣ እንደ ሁኔታዎችና እንደ ድርጊቶች አመጣጥ ምቹ በሚሆነው አማራጭ ለመጓዝ ክፍትና ንቁ መሆን ተገቢ ነው፡፡

 1. ለወቅታዊ የትግል ዕቅድ መነሻ ሐሳብ

ለምርጫ መሯሯጥ የሰላማዊ (የጠመንጃ አልባ) ትግል ብቸኛም ዋነኛም አካል አይደለም፡፡ ወደ ሕገወጥ ትግል መዞርም ብዙዎች እንደሚያስቡት ጠመንጃ ላይ መጠምጠም ማለት አይደለም፡፡ የሕጋዊም ሆነ የኅቡዕ ትግል ዋልታና ማገራቸው የፖለቲካና የማደራጀት ሥራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድኖች ትልቁ ችግራቸው ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ በሁለቱም መንገድ ያሉ ተቃዋሚዎች በየፊናቸው፡-

 • የኢሕአዴግን ቡድን እስከመጣል ድረስ ብቻ ባላጠረ (አምባገነንነትን ሽሮ ዴሞክራሲን በማቋቋም) ግብ ላይ መያያዝ፣
 • የሐሳብ መከፋፈልና ጥርጣሬ በመፍጠር የሕዝቦችን ዓብይ ትኩረት ሊበትኑ የሚችሉ የፖለቲካ ቀዳዳዎችን የደፈነ፣ አምባገነናዊ የሥልጣን ስስት እያደረሰ ያለውን ጉዳት በየፈርጁ የሚዘከዝክና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ የሚያስገኘውን ጥቅም ከአማራጭ ዕቅድ ጋር አገናዝቦ የሚያሳይ ፖለቲካና ፕሮፓጋንዳ መቀየስ፤
 • የቀየሱትንም ከእውነታዊ መረጃዎች ጋር አላልሶ በየኅብረት ልሳኖችና በድርጅታዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ሕዝብ እያደረሱ ያልተበጣጠሰ ሕዝባዊ ንቃትንና ተቀባይነትን መገንባት ይፈለግባቸዋል፡፡

ቀጥሎ የቀረበው ንድፍ ለሁሉም መታገያ መሆን ይችላል ብለን እናምናለን?

 • ከክልላዊ ‹‹ይዞታ›› ከብሔረሰባዊና ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ሰበቦች ሕዝቦች እየተጠመዱባቸው ያሉ ቅራኔዎችና መራራ ስሜቶች የዴሞክራሲን ጥያቄ አስጥለው በተስፋ ማጣት ያለውን አገዛዝ ሙጥኝ የሚያስብሉ፣ ብሎም መውጫ ወደሌለው የእርስ በርስ መተላለቅ የሚወስዱ በመሆናቸው በቶሎ እንዲቀጩ፣
 • የብቻ ሥልጣን በማስጠበቅና በጠላታዊ የፖለቲካ ትንቅንቅ ምክንያት በአገሪቱ የታጣው የፖለቲካ ሰላም ተገኝቶ የአገሪቱ ፖለቲከኞችና ሕዝቦች የይስሙላ ያልሆነ ዴሞክራሲንና ነፃነትን እየተነፈሱ የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስና የአየር ንብረት መዛባት ጎጂነት የተጨመረባቸውንና እንኳን በአንድ ቡድን በተባበረ ርብርብም በቀላሉ የማይበገሩ የአገሪቱን ችግሮች በሙሉ ኃይል ለመጋፈጥ እንዲችሉ የሚከተሉትን ማከናወን፡፡
 1. በሕዝቦች ውስጥ አስፈላጊውን የማንቃትና የቅስቀሳ ሥራ እያካሄዱ የትኛውንም ዓይነት ከፋፋይነት፣ ፀብ አጫሪነትና አምባገነናዊ ወከባ መታገል፣ ከዚሁ ጋር ገዢው ቡድንና ተቃዋሚዎች (በሕጋዊና በሕገወጥ መድረክ ውስጥ ያሉ) ሁሉ ወደ ድርድር እንዲመጡና ከየትኛውም ቡድን ሎሌነት አስገዳጅነት ነፃ በሆነ አስመራጭ አካል የሚከናወን ምርጫ እንዲያዘጋጁ፣ ለዚህም ተግባራዊነት የውስጥና የውጭ ግፊት መፍጠር፣
 2. ግፊቱ ውጤት አስገኝቶ በሚዘጋጀው ምርጫ ማንም አብላጫ ውጤት ያግኝ ተበላጩ ያልተገለለበት የትብብር መንግሥት ማደራጀት፣ አብሮም ከመንግሥት ሥልጣን ውጪ ነባርና አዲስ መጥ የፖለቲካ ቡድኖች የሚቀራረቡበት የጋራ መድረክ እንዲኖር ማድረግ፡፡
 3. የተደራጀው መንግሥት አደራዎች፡-
 • ልማትን ሁለገብነትና የሕዝብ ተነሳሽነት በተለቀቀበት ትጋት ማስቀጠል፣
 • የአገሪቱን መንግሥታዊ አውታሮች ከየትኛውም ቡድን ቁጥጥር ነፃ የሚያደርግ እነፃ (መንግሥት በተቀየረ ቁጥር አዲስ መተራመስ በማይኖርበት ደረጃ) ማካሄድ፣ ይኼንንም የሙያተኛ ብክነትም ሆነ ሠራተኞችን ጉርስ የማሳጣት ታሪክ በማይደገምበት ሁኔታ መፈጸም፣
 • በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተካሄዱ ነባር በጎ ለውጦችን ያካተተ ቀልጣፋና ሥነ ምግባራዊ የሥራ ባህል ግንባታን ማቀጣጠል፡፡
 • የዜጎች መሠረታዊ የጋራና የግል መብቶችን አጣጥሞ ተግባራዊ ማድረግ፣ ቅሬታዎችንና ጥላቻዎችን እያሟሸሹ የሕዝቦችንና የዜጎችን መፈቃቀርና መከባበር ማጠናከር፡፡
 • የአገሪቱ የእስካሁን የፖለቲካ ልምዶች ከዓለምና ከጊዜው አገራዊ እውነታዎችና ፍላጎቶች ጋር እየተገናዘቡ ያላንዳች ገደብ በጥናቶች በውይይቶችና በክርክሮች የሚመረመሩበትን ሒደት ማስጀመር፤ በዚህም አማካይነት ሕዝቦች አሸማቃቂና አክለፍላፊ ሳይኖርባቸው የጋራ ቤታቸውን በወደዱት መልክ የሚያደራጁበት አዲስ ምዕራፍ ውስጥ መግባት፡፡
 • ከጎረቤት አገሮች ጋር በጋራ ጥቅም ላይ ለተመሠረተ ወዳጅነት ያለ ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ፤ በዚሁ መሠረትም ግንኙነቶችን ለማቀናት ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...