Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹‹ዶቅዶቄዎቹ››

በተጨናነቁት የከተማችን ጎዳናዎች ከሌሎች ተሽከርካሪዎች በተሻለ የሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ ሞተር ብስክሌቶችን የሚወዳደር የለም ይባላል፡፡ በቀደመው ዘመን  ‹‹ዶቅዶቄ›› እያልን በልማድ የምንጠራቸው ባለሁለት ጎማ ተሽከርካሪዎች፣ በሕግ የተፈቀደው የተሽከርካሪዎች መጓጓዣ መንገድ ካልተመቻቸው አውራ ጎዳናውን  ጥሰው በእግረኞች መንገድ እንዳሻቸው ነድተው ይሄዳሉ፡፡ እንዲህ ባለው ሕገወጥ እንቅስቃሴያቸው አዘውትረን የምናያቸው የሞተር ብስክሌት ነጅዎች ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ እንደውም ታዳጊዎች ሳይበዙበት ይቀራሉ?

የሞተር ሳይክሉ ኮርቻ ላይ ተፈናጠው በመኪኖች መካከል ሲሽሎኮሎኩ የሚተርፉ አይመስሉም፡፡ ጥድፊያቸው አጀብ ያስብላል፡፡ ጎዳናው የትራፊክ መጨናነቅ ከሌለበት ደግሞ ለእነሱ ሠርግና ምላሽ ሆኖ ‹‹እፍ›› ብለው ይፈተለካሉ፡፡ እንዲህ ባለው አነዳዳቸው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የምንታዘባቸው ሞተር ብስክሌቶች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፡፡ በሞተር ብስክሌቶቹ አማካነት የሚጓጓዘው ሰው ብቻም ሳይሆን ዕቃም ጭምር ነው፡፡ በእነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚሠራው ‹‹ሥራ››ም ጨምሯል፡፡ በቀድሞው ጊዜ ሞተር ብስክሌት ይዘወተር የነበረው በትራፊክ ፖሊሶችና በፖስተኞች ነበር፡፡ አልፎ አልፎም አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ለጉዳይ አስፈጻሚዎች አገልግሎት የሚውል ሞተር ብስክሌት ይኖራቸዋል እንጂ በግለሰቦች ባለቤትነት የሚሽከረከሩ ሞተር በብስከሌቶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡

አሁን ግን ከተቋማት ይልቅ በግለሰቦች ለግል አገልግሎት የሚውሉ የሞተር ብስክሌቶች በርክተዋል፡፡ የዶቅዶቄ አስመጪዎች ቁጥር መጨመሩንም ልብ ይሏል፡፡ የዶቅዶቄ ገበያ በመስፋፋቱ ምክንያት በአገር ውስጥ ለመገጣጠም መታሰቡ በራሱ የተሽከርካሪዎቹ ቁጥር ወደፊትም እየጨመረ እንደሚቀጥል ይመሰክርልናል፡፡

 ለማንኛውም ሞተር ብስኬቶቹ ለምን ዓይነት አገልግሎትና ለምን ያለው ጥቅም እየዋሉ ነው? የሚለውን ጥያቄ በቅጡ መፈተሽ ተገቢ የሆነበት ወቅት መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞች ዶቅዶቄዎች እየተረማመሱ ይገኛሉ፡፡ ታክሲዎችን ተክተው እየሠሩም ነው፡፡ እንደውም በአንዳንድ አካባቢዎች ሦስት ተሳፋሪዎችን አፈናጠው ሲንቀሳቀሱም ተመልክቻለሁ፡፡ በአዲስ አበባም ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሞተር ብስክሌቶችን ተኮናትረው የሚገለገሉ ነዋሪዎች እየተበራከቱ ነው፡፡

የራሳቸው መናኸሪያ የፈጠሩም አሉ፡፡ የሚፈልጋቸው ተገልጋይ ሲኖርም ስልክ ይደውላሉ አለያም ያሉበት ድረስ ይሄዳሉ፡፡ በዚህም በዚያም የራሳቸውን ደንበኞች ማፍራት ችለዋል፡፡ እንደሚባለውማ የከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ታች ሲጋልቡ የሚውሉት ሞተር ብስክሌቶች አብዛኞቹ በተለያዩ ቢዝነሶች ውስጥ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ልዩ ልዩ ‹‹ሽቀላዎች›› አሏቸው፡፡ ቢዝነሱ የሰጠ በመሆኑም ብዙዎች እየገቡበት ነው፡፡ ትልቁ ችግር ግን እነዚህን ሞተር ብስክሌቶች የሚነዱ ወጣቶች መንጃ ፈቃድ የላቸውም ከሚለው ጀምሮ፣ የሕገወጥ ግብይት አስተላላፊ እየሆኑ ነው መባሉ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ዕውቅና ያልተሰጣቸው አሽከርካሪዎች በዝተዋል ለሚለው ስሞታ ጥሩ ማረጋገጫ የሚሆነው፣ ብዙዎቹ ባለሁለት ጎማ አሽከርካሪዎችን ትራፊክ ሲያስቆማቸው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ‹‹እፍ›› ማለት እያበዙ መታየታቸው ነው፡፡ ይህንን በተደጋጋሚ አይቻለሁ፡፡ የብዙዎቹን ታርጋዎች ልብ ብላችሁ ካያችሁ እንኳስ ከሩቁ ጠጋ ብሎ ለመለየትም ይቸግራሉ፡፡ ይህ ደግሞ አደጋ ቢያደርሱና ለማምለጥ ቢሞክሩ ታርጋውን ይዞ ወደ ሕግ ለመውሰድ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ ሞተረኞች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው መልዕክቶችንና ትናንሽ ዕቃዎችን በማመላለስ አንጀት የሚያደርስ ሥራ ይሠራሉ ቢባልም፣ በአንፃሩ ተገቢ ያልሆነ ሥራ የሚሠሩም አሉ፡፡

ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሚሆነው ግን እነዚህ ሞተሮችና ሞተረኞች ለሕገወጥ ንግድ ዝውውር ምቹ መሆንና በዚህ ተግባር ላይ የተሰማሩ አሽከርካሪዎች መበራከት ነው፡፡

አንዳንድ ሞተረኞች ማልደው በመነሳት ወደ ተለያዩ ቦታዎች በሚያደርጉት እንቅስሴ ‹‹የቄራን ሥራ ተክተው እየሠሩ ነው፤›› ተብለው የሚወቀሱበትን ሥራ ተክነውበታል እየተባለ ነው፡፡ ማልደው ከሚነሱና በጥድፊያ ወዲህና ወዲያ ከሚሉ ባለዶቅዶቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ምስጢራዊ በሆነ ሥፍራ የታረደ የበግ ወይም የሌላ እንስሳ ሥጋ ወደ ሆቴሎች ያመላልሳሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ ታርዶ የመጣውን ሥጋ የሚረከቡት ሆቴሎች ሲያልቅባቸውም፣ በፍጥነት በመደወል እንዲመጣላቸው የሚያዙት ሞተረኞቹን ነው፡፡ ሥጋውን ከየት ያመጠት ይሆን? ብሎ የሚጠይቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሆቴሎች ጤነኛ ይሁን አይሁን ሳያረጋግጡ ይረከባሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሥጋው በቄራ መኪና የመጣ ነው ወይስ በዶቅዶቄ? እንጀራው ከንፁህ ጤፍ የተዘጋጀ ነው ወይስ ጄሶ የተደባለቀበት? ብሎ  ምንጩን ጠይቆ የመመገብ ባህል ያላዳበረው ሸማች ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን አደጋ ሳስብ የሸማቾች ህልውና አሳሳቢነት ይሰማኛል፡፡

ለማንኛውም ኃላፊነት በማይሰማቸው በአንዳንድ ባለዶቅዶቄዎች ሕገወጥ ግብይት ሲፈጸም፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ባለሆቴሎችም የዚህ ሕገወጥ ተግባር ቀንደኛ ተሳታፊ መሆን ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው፡፡ በጎዳናዎች ታክሲን በመተካት የማገልገላቸው ጉዳይም በቸልታ መታለፉና የፍጥነታቸው ለከት አልባነትም ለአደጋ የሚዳርግ መሆኑ ታውቆ፣ የከፋ አደጋ ከመድረሱ በፊት መጠንቀቅ ያሻል፡፡ ለነገሩ በየጊዜው የተገጩ ሞተረኞችን ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በርካቶችም ለህልፈት ሲዳረጉ፣ አጓጉል ሲሞቱ ማየት የሰርክ ልማድ መስሏል፡፡  

አደጋ ሲያደርሱም አሳዶ ለመያዝ እያስቸገሩ መሆኑን በየጊዜው የምንሰማው ተረት ሆኖ መዝለቅ እንደሌለበት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ቢያንስ የዶቅዶቄዎቹ ባለቤት ማነው? የሚያሽከረክራቸውስ ማነው? ብሎ መለየትና ማወቅንም ይጠይቃል፡፡ በሕግ የተፈቀደውን የመንጃ ፈቃድ አግኝተው የሚሠሩትን ከማይሠሩት መለየትስ አያስፈልግም? አደጋ አድርሰው ለማምለጥ ሲሞክሩም ይህንን ለመከላከል ለዕይታ ምቹ ታርጋ እንዲኖቸው ማድረግስ የማን ኃላፊነት ነው?

ምነው አንድ ሰሞን አንዳንድ ሞተረኛ ሌቦች ከመንገደኛው ላይ ሞባይልና ቦርሳ መንትፈው እብስ ማለት ተለምዶ መነጋገሪያችን አልነበረም ወይ? እርግጥ በዚያን ወቅት ፖሊስ ጣቢያዎች ከሞተረኛ ሌቦች በተያዙ ሞተሮች ተጣበው ነበር፡፡

 በእርግጥ ሁሉም በተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ናቸው ባይባልም፣ ገዥ ሕግና መቆጣጠሪያ ሥልት ከሌለ ዛሬ ከምንሰማው በላይ ወንጀል ሊፈጸምባቸው

ከማይታወቅ ቦታ እየተበለተ የሚቀርበውን ሥጋ ምንጩን ማድረቅም በትኩረት መታየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ባለሆቴሎችንም አደብ ማስገዛት፣ በእምነት የሚመገብላቸውን ተገልጋይም መታደግ ተገቢ ነው፡፡ ከተማው ከአጣዳፊና ተቅማጥ ወረርሽኝ በቅጡ ማገገም አለመጀሩን ልብ ይሏል፡፡ ንጽህናው ያልተጠበቀ ምግብ መመገብ ለበሽታው መዛመት አንዱ ምክንያትም አይደል፡፡

በሌላ በኩል በጥሩ ሥነ ምግባር ይህን ዕቃ ለእከሌ አድርስ የተባለ ሞተረኛ ትዕዛዙን በአግባቡ ፈጽሞ ተገቢውን ክፍያ ሲያገኝ የሚያስደስት ቢሆንም፣ ከሕግ አንፃር ይህ አሠራር ይፈቀዳል ወይ? በየትኛው ሕግስ ይገዛል ብሎ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በቶሎ ለመድረስ የሞተር ብስክሌት ኮርቻ ላይ የተቀመጠ ተጓዥ አደጋ ቢደርስበት የመድን ዋስትና አለው? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ዶቅዶቄዎች ሥርዓት ይዘርጋላቸው፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት