Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተሽከርካሪዎቻቸው በሁከት የወደሙባቸው ባለንብረቶች መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ

ተሽከርካሪዎቻቸው በሁከት የወደሙባቸው ባለንብረቶች መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ

ቀን:

–  የትራንስፖርት ባለሥልጣን ዕድሜ ጠገብ አውቶቡሶችን ለማዘመን ጥናት ጀመረ

በቅርቡ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተከስቶ በነበረው ሁከት ሳቢያ የደረቅና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች የወደሙባቸው ባለንብረቶች፣ መንግሥት ድግፍ እንዲያደርግላቸው ጠየቁ፡፡

ባለንብረቶቹ ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሐሙስ ኅዳር 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡ በስብሰባው ላይ የተካፈሉ የሕዝብ ማመላለሻና የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ማኅበራት ተወካዮች ተሽከርካሪዎቻቸው ለወደሙባቸው ባለንብረቶች እገዛ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ምን የታሰበ ነገር አለ? ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ከማኅበራቱ ለተሰነዘረው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለ ማርያም፣ ንብረታቸው ከተጎዱባቸው ባለሀብቶች ጋር ባለሥልጣኑ ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ መስታወት መሰበርና ሌሎች አነስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ባለንብረቶች ወጪውን በራሳቸው እንዲሸፍኑ ስምምነት ላይ መደረሱን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ የአንዳንዱ ተሽከርካሪ መስታወት ከ100,000 ብር በላይ የሚያስወጣ በመሆኑ ተጨማሪ የመስመር ሥራዎች በመስጠት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ተሽከርካሪዎቻቸው ሙሉ በሙሉ የወደሙባቸው ባለንብረቶች መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው በትራንስፖርት ሚኒስቴር በኩል ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ተሽከርካሪዎቻቸው የወደሙባቸው ባለንብረቶች ዝርዝር፣ አድራሻ፣ የመድን ዋስትና የገቡበት ኩባንያ፣ በተሽከርካሪዎቻቸው ላይ የደረሰው ውድመት ዝርዝር ሪፖርት ተሠርቶ ለመንግሥት ቀርቧል፡፡ 

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ኮማንድ ፖስት የተቋቋመ ኮሚቴ የቀረበውን ሪፖርት በመገምገም ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ ኮሚቴው የደረሰውን ውድመት የሚገመግም የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ ድርጊቱ ወደ ተፈጸመባቸው ሥፍራዎች መላኩን አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት የሪፖርቱን ትክክለኛነት ካጣራ በኋላ በአቅሙ የሚችለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተከሰተው አለመረጋጋት 15 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች የወደሙ መሆናቸውን ከእነዚህ ውስጥ 11 ሙሉ በሙሉ፣ አራቱ በከፊል መውደማቸውን አቶ ካሳሁን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በደረቅ ጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በኩል 29 ተሽከርካሪዎች የወደሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 12 ተሳቢ ያላቸው ናቸው፡፡

በተያያዘ ዜና የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመን የሚያስችለውን ጥናት መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ጥናቱ ለረዥም ዘመን ሕዝብ ሲያመላልሱ የነበሩ ዕድሜ ጠገብ አውቶቡሶችን በዘመናዊ አውቶቡሶች ለመለወጥ ያለመ፣ የአውቶቡስ መናኸሪያዎችን ለማዘመንና ዘመናዊ የአውቶቡስ ቲኬት ሽያጭ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አሁን ያሉት አውቶቡሶች በአብዛኛው ኋላቀር፣ ለተሳፋሪዎች ምቹ ያልሆኑ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር የማይተዋወቁ፣ የነዳጅ ወጪያቸው ከፍተኛ፣ ለአካባቢ ብክለት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርጉና ለመለዋወጫ የሚወጣውም ወጪ ቀላል እንዳልሆነ አቶ ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከፍተኛ አገር አቋራጭ አውቶቡሶችና መለስተኛ አውቶቡሶች ጭምር በዘመናዊ ተሽከርካሪዎች መለወጥ አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አነስተኛ መቀመጫ ያላቸው የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ለኢኮኖሚው ጠቃሚ አይደሉም ብለን ነው የምናምነው፡፡ ይዘውት ከሚጓዙት መንገደኛ አንፃር 12 እና 60 መቀመጫ ያላቸው አውቶቡሶች ጠቀሜታ ይለያያል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ባለንብረቶች ተደራጅተው አክሲዮን ማኅበር በማቋቋም የዘመናዊ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉበት መንገድ እየተጠና እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዋና ድርሻ የባለሀብቱ ነው፡፡ የባለሀብቱ ተሳትፎ እንደተጠበቀ ሆኖ የመንግሥትም ድጋፍ ታክሎበት ምን ሊደረግ ይችላል የሚለውን የሚጠቁም ጥናት እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የሕዝብ ማመላለሻ ማኅበራት ተወካዮች ጥናቱ በመጀመሩ ደስታቸውን ገልጸው፣ ጅምሩ ከዳር እንዲደርስ ስብሰባውን የመሩትን ሚኒስትር ዴኤታዎች አቶ አብዲሳ ያደታና አቶ ደሳለኝ አምባውን ተማፅነዋል፡፡ ‹‹ከዛሬ ነገ እንሞታለን ብለን ስንጠብቅ ዛሬ የተስፋ ጭላንጭል አይተናልና የተጀመረው ጥረት እንዳይቋረጥ አደራ፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ በአጠቃላይ 30,000 አውቶቡሶች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ 1,200 ያህሉ አገር አቋራጭ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በስብሰባው ላይ ታዋቂ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ባለቤቶች የተካፈሉ ቢሆንም፣ በመንገድ ኮንስትራክሽን ዘርፍ በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ ጥያቄ ሳያነሱ ቀርተዋል፡፡ በስብሰባው ላይ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ሆነ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር በመንገድ ግንባታ ዘርፉ ከኮንትራክተሮች የቀረበ ጥያቄ አልነበረም፡፡ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ብዙ ፈተናዎች ያሉ ቢሆንም፣ ኮንትራክተሮቹ በስብሰባው ወቅት ዝምታን መርጠዋል፡፡

አዲሱ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ስብሰባውን እንደ መተዋወቂያ መድረክ ተጠቅመውበታል፡፡ አቶ አህመድ መንግሥታቸው የትራንስፖርቱን ዘርፍ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ የባቡርና የመንገድ መሠረተ ልማቶች በመዘርጋት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ለመመለስ መንግሥት ከፍተኛ ርብርብ መጀመሩን ጠቁመው፣ በትራንስፖርቱ ዘርፍም የሚነሱ ጥያቄዎችን አድምጦ ምላሽ ለመስጠትና በጋራ ተባብሮ ለመሥራት ቁርጠኝነት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዎቹ አቶ አብዲሳና አቶ ደሳለኝ ባለፈው ዓመት ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ጭነት አመላላሾች ከጂቡቲ ወደብ የዕርዳታ እህልና ማዳበሪያ በርብርብ በማንሳታቸው ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በተመሳሳይ በቅርቡ በአገሪቱ አለመረጋጋት በተፈጠረበት ወቅት የሕዝብ ማመላለሻ ባለንብረቶች ለሕዝቡ የሚሰጡት አገልግሎት እንዳይቋረጥ ላደረጉት ጥረት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...