በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለስምንት ወራት በመደራጀት፣ ማረሚያ ቤቱን በማቃጠልና 23 ታራሚዎችን በመግደል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች፣ በገለልተኛ አካል እንዲጠበቁ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤትን ጠየቁ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ለተከሾች ሰጥቶ እንደጨረሰ ክሱን በንባብ እንደሚያሰማ ሲያስታውቅ፣ ተከሳሾቹ አቤቱታ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን አቤቱታቸውን የሚሰማው ክሱን ካነበበ በኋላ መሆኑን ገልጾ የ37 ተከሳሾችን የወንጀል ተሳትፎ የሚገልጸውን ዝርዝር ክስ አንብቧል፡፡ ፍርድ ቤቱ ንባቡን እንደጨረሰ ተከሳሾቹ እንደገለጹት፣ በመስቀል አደባባይ ለቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት ሲሠራ ‹‹መቼም መቼም አይደገምም›› የተባለው በእነሱ ላይ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ እጃቸውን ከፍ በማድረግ የሚናገሩት እንዲቀዳላቸው፣ ሰውነታቸው ፎቶግራፍ እንዲነሳና ለማስረጃ እንዲቀመጥላቸውም ጠይቀዋል፡፡ አንድ ተከሳሽ ራቁቱን መገረፉንና በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 27 መሠረት በፍላጎቱ ለፖሊስ ቃሉን መስጠት ሲገባው በግዳጅ መስጠቱን ተናግሯል፡፡
ተከሳሾቹ ማንም እንደፈለገው እንደሚያደርጋቸውና ለሕይወታቸው ወይም በሕይወት ለመኖር ዋስትና እንደሌላቸው ገልጸው፣ በገለልተኛ አካል ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡
ክሱ የውሸት ክስ መሆኑንና ነገም ሌላ ሴራ ተሠርቶ እነሱ ናቸው ሊባል እንደሚችል ተከሳሾቹ ገልጸው፣ በድጋሚ በገለልተኛ አካል መጠበቅ እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ በሰጠው ምላሽ ተፈጸመ የሚሉትን ኢሰብዓዊ ድርጊት በጽሑፍ ቢያቀርቡ ወደፊትም ለማስረጃ እንደሚጠቅማቸው አስታውቋል፡፡ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንና ማንኛውንም ችግር አለ የሚሉትን በጽሑፍ ካቀረቡ በኋላ አስፈላጊውን ትዕዛዝ እንደሚሰጥላቸውም ገልጿል፡፡ በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው ጠበቃ በራሳቸው የሚያቆሙ መሆን አለመሆኑን ለመጠባበቅ ለታኅሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡