Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንግሥት በመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የግሉን ዘርፍ ለማስገባት የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ ነው

መንግሥት በመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ የግሉን ዘርፍ ለማስገባት የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ ነው

ቀን:

የአገሪቱን የመሠረተ ልማት አውታሮችን በብቸኝነት በመገንባት ላይ የሚገኘው መንግሥት፣ በዘርፉ የግል ባለሀብቶችን ማስገባት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ጀመረ፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ዘርፍ የግሉ ዘርፍ በባለቤትነት ገንብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የሚያስችል ሥራ ተጀምሯል፡፡

‹‹የውጭ ኩባንያዎች የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘው መጥተው ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር ወይም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በሽርክና ሊሰማሩ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል፤›› ሲሉ ዶ/ር ይናገር አስረድተዋል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት በተጀመረው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አብዛኛዎቹ መሠረተ ልማቶችና በኢኮኖሚው ላይ መዋቅራዊ ለውጥ የሚያመጡ ፕሮጀክቶች በመንግሥት የሚካሄዱ ቢሆንም፣ የተመረጡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በመንግሥትና በግል አጋርነት ወይም በግሉ ዘርፍ አቅም ብቻ ሊገነቡ የሚችሉበት ጥናት እንደሚካሄድ ይገልጻል፡፡

በዚህ መሠረት የአገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ ዕቅዶች የሚያዘጋጀው ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን፣ ይህንኑ ሥራ የሚያስጀምሩ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት መጀመሩ ታውቋል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በተለይ አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር ለውጥ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ተብለው በተመረጡ ዘርፎች ላይ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ ታቅዷል፡፡

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የባቡር፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የስኳር፣ የማዳበሪያ፣ የኬሚካልና ፕላስቲክ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ከመንግሥት ጋር በሚደረግ ሽርክና ወይም በግሉ ዘርፍ አቅም ለመገንባት ፍላጎት ያለው ኩባንያ ማሳተፍና ማበረታታት የሚያስችሉ፣ የሕግና የአፈጻጸም መመርያዎች በመዘጋጀት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ እንደተገለጸው፣ የግሉ ዘርፍ በመሠረተ ልማት ዘርፎች የሚጠበቅበት ተሳትፎ ከፍተኛ ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ በተፈቀዱ ንዑሳን ዘርፎች ውስጥ ያለው ተሳትፎ እንዲያድግ አስፈላጊው ማበረታቻና ድጋፍ ትኩረት እንደሚሰጠው ይገልጻል፡፡

‹‹ከዚህ አንፃር ከግሉ ዘርፍ የሚጠበቀው ጥራት ያለው የውጭ ምንዛሪ፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማምጣት ነው፤›› ሲል ዕቅዱ ያስገነዝባል፡፡

በዕቅዱ ዘመኑ 1.04 ትሪሊዮን ብር (62.0 በመቶ) የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ፍላጎት ለማሟላት የሚውል ሲሆን፣ 640 ቢሊዮን ብር ደግሞ በመንግሥት ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የሚውል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዶ/ር ይናገር እንደገለጹት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየሰፋ በመሄድ ላይ የሚገኝ በመሆኑ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ በመንግሥት ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ታቅዷል፡፡

በመንግሥትና በግል አጋርነት በተለይም በግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር እየተሞከረ ይገኛል፡፡   

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...