Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊለታዳጊዎች የአልኮል መጠጥ መሸጥ ክልክል ነው የሚለውን ገደብ መጣስ ተበራክቷል

  ለታዳጊዎች የአልኮል መጠጥ መሸጥ ክልክል ነው የሚለውን ገደብ መጣስ ተበራክቷል

  ቀን:

  ከ18 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች የአልሎል መጠጥ መሸጥ ክልክል ነው የሚለውን ገደብ በመተላለፍ መጠጥ የሚሸጡ ንግድ ቤቶችና መጠጥ የሚጠጡ ታዳጊዎች መበራከታቸው ተገለጸ፡፡

  በየካና በአቃቂ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 13 የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በሚማሩ 530 ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት 31.9 በመቶ የሚሆኑ የአልኮል መጠጥ ጠጥተው እንደሚያዉቁ፣ 22.8 በመቶ የሚሆኑት አልኮል መጠጥ እንደሚያዘወትሩ፣ 24.7 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የአልኮል መጠጣት  እንደጀመሩ፣ 32 በመቶ የሚሆኑት በመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ 18 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩ መሆናቸውን፣ የተማሪዎቹ አማካይ ዕድሜም 16.8 መሆኑን ረዕቡ ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ይፋ በተደረገው ጥናት ላይ ተመልክቷል፡፡

  በጥናቱ መሠረት ከሰባት ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎች አለምንም ችግር መጠጥ የሚገዙበት ሁኔታ በስፋት ያታያል፡፡ 43 በመቶ የሚሆኑት መጠጥ የሚያዘወትሩ ታዳጊዎች ከግሮሰሪ፣ 13 በመቶ ከባርና ሬስቶራንት መጠጥ ያገኛሉ፡፡ የቤተሰብ አባላትም ለታዳጊዎቹ መጠጥ የሚያቀርቡበት ሁኔታ መኖሩም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ 17 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች ቤተሰቦቻቸው መጠጥ እንደሚያቀርቡላቸው በመጠይቁ የሰጡት ምላሽ ያሳያል፡፡

  መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ የምግብ የመድኃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደር የቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ወረቲ፣ ሕጉን ተላልፈው ከ18 ዓመት በታች ለሚገኙ ታዳጊዎች የአልኮል መጠጥ እንዳይሸጥ ሚከለክለውን ሕግ ለማስፈጸም የሚረዳ መመሪያ ለማፅደቅ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

  ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች የአልኮል መጠጥ መሸጥ የተከለከለ መሆኑ በተለያዩ ድንጋጌዎች ላይ ሰፍሯል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ታዳጊዎቹ በግሮሠሪና ከሌሎችም የመጠጥ መሸጫ ቦታዎች አለምንም ችግር መጠጥ ገዝተው የሚጠቀሙበት ሁኔታ ተለምዷል፡፡

  የአልኮል መጠጦች በሰዎች ላይ አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት የማድረስ አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣንም ከጤና ጋር በተያያዘ እንዲሠራበት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በደንብ ቁጥር 60/2006 ላይ አልኮል ለታዳጊዎች መሸጥ ክልክል መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ደንቡን ተግባራዊ ለማድረግ መመሪያ ያስፈልገዋል፡፡ ‹‹ደንቡ ላይ ክልክል መሆኑን ነው የሚያስቀምጠው ወደ አፈጻጸም ለማውጣት ደግሞ መመሪያ ያስፈልገዋል፤›› ሲሉ ዋና ዳሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የሚወጣው መመሪያ ከዚህ ቀደም የነበረውን አስተዳደራዊ ዕርምጃ ከበድ እንደሚያደርገውም አክለዋል፡፡

  በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረፅ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ፍፁም አባይነህ እንደሚሉት፣ ከ18 ዓመት በታች ላሉት ታዳጊዎች መጠጥ መሸጥን በተመለከተ በወንጀለኛ ሕጉ የተቀመጡ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በወንጀል ሕጉ ላይ የሠፈረው አንቀጽ 531 ላይ የአልኮል መጠጥ በመስጠት የታዳጊዎቹን ጤንነት ለአደጋ ማጋለጥ በቀላል እስራትና በገንዘብ መቀጫ እንደሚያስቀጣ የሚዘረዝረው ነው፡፡

  ‹‹ማንኛውም ሰው ይኼንን አውቆም ይሁን ሳያውቅ ተላልፎ ቢገኝ፣ በወንጀል ሕጉ ይቀጣል›› ብለዋል፡፡ በአፈጻጸም ረገድ ግን ክፍተት ይስተዋላል፡፡ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ ድንጋጌውን ተላልፈው ለ18 ዓመት በታች ላሉ ታዳጊዎች የአልኮል መጠጥ የሚሸጡ ተገቢውን ቅጣት እያገኙ አለመሆኑን ዓቃቤ ሕጉ ይናገራሉ፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የንቃተ ሕግ አነስተኛ መሆን፣ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የተገኙ ሰዎችን ለሚመለከተው የሕግ አስፈጻሚ አካል ሪፖርት ማድረግ አለመለመዱም እየታየ ላለው ችግር መንስዔ መሆን አቶ ፍፁም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

  በሕግ የተፈቀደውን አልኮል የመጠጫ ዕድሜ ሕግ አፈጻጸም ለማጠንከር በሚል በተዘጋጀው የአንድ ቀን የምክክር መድረክ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡  የምክክር መድረኩ ሜታ አቦ ቢራ በ2008 ዓ.ም. የካቲት ወር ላይ፣ ከተፈቀደው ዕድሜ በታች የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ለመቀነስ የጀመረው ዘመቻ አካል ነው፡ በዕለቱ ይፋ የተደረገውን የዳሰሳ ጥናት ያካሄደው የዘመቻው አካል የሆነውና በጤና ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ጂአይኤስ የተባለው ድርጅት ነው፡፡

  በዕለቱ የሜታ አቦ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ኮርፖሬት ግንኙነቶች ዳይሬክተሩ አቶ በሃከል አባተ ‹‹ከተፈቀደው ዕድሜ በታች የአልኮል መጠጥ መጠጣት ለማኅበረሰባችን ትልቅ ሥጋት እንደሆነና ዲያጆም ይኼንን ለመከላከል ያለሙ እንቅስቃሴዎችን በመላው ዓለም በሚገኙ አገራት ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img