Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፊርማ በየፈርጁ

ፊርማ በየፈርጁ

ቀን:

ከአሥር ዓመታት በፊት አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሳለች የሆነ ነው፡፡ ስድስት ወር ገደማ በሰው ኃይል አደረጃጀት ኤክስፐርትነት እየሠራች ከነበረችበት መሥሪያ ቤት የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንደምትፈለግ የሚገልጽ ደብዳቤ ተለጥፎ ታያለች፡፡ ነገሩ ደንገጥ እንድትል አድርጓት እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ብዙ ነገሮችን አስባ ጉዳዩ ሊሆን የሚችለው በሰዓቱ የሥራ ገበታ ላይ አለመገኘትን የሚመለከት እንደሚሆን ደመደመች፡፡ ከአስተዳደር ቢሮ ተገኝታ የተገለጸላት ነገር ግን ፈጽሞ ያልጠበቀችው ነበር፡፡ ከተቀጠረች ጀምሮ ደመወዝ ስትወስድ ፔሮል ላይ ያስቀጠቻቸው ፊርማዎች የተለያዩ መሆናቸው በአስተዳደር ኃላፊው ሲገለጽላት ፈገግ ሁሉ አስብሏት ነበር፡፡ ይህ ኃላፊው እንዲቆጡም አድርጐ ነበር፡፡ ይህ ማለትም እንደ ሁኔታው የፊርማ መለያየት የሌሎችም አጋጣሚ እንደሆነ በተለያየ መልኩ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ብዙ ጊዜ ይህ ችግር ባይኖርባቸውም ሲቸኩሉ ወይም አንዳንድ ለየት ያሉ ሁኔታዎች ውስጥ (ለምሳሌ ባንክ ውስጥ) ፊርማቸውን በትክክል ማስቀመጥ የተቸገሩበት ጊዜያት እንደነበሩ የገለጹልን አሉ፡፡

እንደ ኮፒ መደረግ ያሉ አጋጣሚዎች ሰዎች ፊርማቸው ቀላል ወይስ ኮፒ ለመደረግ የሚያስቸግሩ መሆናቸውን ራሳቸውን እንዲጠይቁ የግድ ሊሉ ይችለሉ፡፡ አቶ እያሱ አሰፋ የአሁኑ ፊርማቸው ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የሚጠቀሙት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህ ማለት ፊርማውን ከሁለት አሠርት በላይ ተጠቅመውበታል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ፊርማ የፈረሙት ልጅ ሳሉ ከነበሩበት ትምህርት ቤት ወደ ሌላ ተቀይረው አራተኛ ክፍልን በአዲሱ ትምህርት ቤት በተመዘገቡበት ወቅት እንደነበር በደንብ ያስታውሳሉ፡፡ መምህር ይሁን የአስተዳደር ሠራተኛ በምዝገባቸው ወቅት ‹‹እዚህ ጋር ፊርማህን አኑር›› ሲላቸው ግራ ተጋብተው ነበር፡፡ ስለዚህም እንዴት ነው የምፈርመው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ሰውየውም በስምህ ፈርም ይሏቸዋል፡፡ ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ስማቸውን ጽፈው ፈረሙ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ሰባት የሚሆኑ ፊርማዎችን በተለያየ ምክንያትና አጋጣሚ ቀይረዋል፡፡

አሁን የሚፈርሙት ሙሉ ስማቸውን በማያያዝ ሲሆን፣ ፊርማቸው በቀላሉ ኮፒ የሚደረግ እንዳልሆነ ያምናሉ፡፡ ከዚህኛው በፊት የነበረው ፊርማቸው ስማቸው በሩስኪ ነበር፡፡ ፊርማቸው እንዴት እንደዚያ ሊሆን እንደቻለ ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ‹‹በወቅቱ ሩሲያና ኢትዮጵያ ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው፡፡ እኔም የሩሲያኛ ቋንቋ እማር ነበር›› ሲሉ በማስታወስ የዚያ ፊርማቸው መሠረትን ለማብራራት ይሞክራሉ፡፡

ከዚያ ደግሞ የሩስኪ ስማቸው ፊርማን ቀይረው እንደገና ሙሉ ስማቸውን በአማርኛ አደረጉ፡፡ እሳቸው እንደሚያስታውሱት የቀየሩበት ወቅት ስሞች ፊርማዎችም ይበልጥ ማንነትን ያንፀባርቁ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ፊርማቸው ስማቸውን ብቻ ሳይሆን ማዕረጋቸውን ጭምር መሠረት እንዲያደርግ የሚያደርጉ ሰዎችም እንዳሉ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ረገድ የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ፊርማን ይጠቅሳሉ፡፡ ፋርማቸው ‹‹ሻ››ን (ሻለቃ) መነሻ ያደረገ ነበር፡፡ ስልሳዎቹ ጀነራሎች እንዲረሸኑ ትእዛዝ በሰጡበት ደብዳቤ ላይ ይህ ፊርማቸው መኖሩንም ያስታውሳሉ፡፡ ብላቴን ጌታ ህሩይም የብላታ ማዕረጋቸውን የፊርማቸው አካል አድርገው እንደነበር ሠነዶች ይመክራሉ፡፡ የሚያጋጥም ባይሆንም በተለያየ ቋንቋ የተለያዩ ፊርማዎች የሚኖሯቸው ሰዎችም አልፎ አልፎ ያጋጥማሉ፡፡ አቶ እያሱ በዚህ ረገድ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ይጠቅሳሉ፡፡ እዚህ ላይ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ስፔንን ለሁለተኛ ጊዜ ሲጐበኙ ፈረንሳይኛ የተቀየጠበትን ፊርማቸውን እንዳኖሩ ያስታውሳሉ፡፡

የፊርማዎች ቀላልና ከበድ ማለትን በሚመለከት በተለይም በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ደብዳቤዎች፣ ውሎችና ስምምነቶች ላይ የሚፈርሙ ሰዎች ፊርማ ቀላልና ኮፒ መደረግ የሚችል መሆን የለበትም የሚል አቋም አላቸው፡፡ ነገር ግን በጠቀሱት ደረጃ ላይ ሆነው ማንም በቀላሉ ፊርማቸውን ሊያስመስለው የሚችል ሰዎች እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡ በተለያየ ጊዜ በመንግሥት ተቋማት ኃላፊነት ደረጃ ላይ የነበሩ ሰዎችን ስም ይጠቅሳሉ፡፡

በሰባዎቹ መጨረሻ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ ሥራ ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ፊርማቸው አንድ ዓይነት ነው፡፡ ፊርማቸው ቀላል የሚባል እንደሆነ የሚናገሩት አባት በአንዳንድ የተለዩ አጋጣሚዎች ግን ፊርማቸውን በትክክል ማስቀመጥ መቸገራቸውን ያስታውሳሉ፡፡ ከዓመታት በፊት በተደጋጋሚ ባንክ ገንዘብ የሚያስገቡበትና የሚያወጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ፊርማቸውን በትክክል ማስቀመጥ እያቃታቸው በተደጋጋሚ እንዲፈርሙ ተደርገው ነበር፡፡ በተመሳሳይ ችኮላ ውስጥ ሆነው ተቸግረው የሚያውቁባቸው ጊዜአትም ነበሩ፡፡ እሳቸውም ኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ፊርማ ቀላል መሆን እንደሌለበት በአቶ እያሱ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡

ልሳን አድማሱ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት ነች፡፡ በአንድ ድርጅት ውስጥ የሒሳብ ሠራተኛ ነች፡፡ በስሟ የሚሠሩ ቼኮችን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ሠነዶች ላይ ትፈርማለች፡፡ የምትሠራበት ድርጅት በተሰማራበት ዘርፍ ምክንያት በየዕለቱ የገንዘብ ማውጣት ማስገባት ነገር መኖሩን የምትናገረው ልሳን አሁን ሌላ ሠራተኛ ተቀጥሮ የሠራተኛ ደመወዝ ክፍያን ይመለከት የነበረው ኃላፊነቷ ስለተቀነሰላት እንጂ ቀደም ሲል ብዙ ሠነዶች ላይ ትፈርም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ፊርማሽ እንዴት ያለ ነው? አልናት ዴስኳ ላይ የነበረ የደረሰኝ ደብተር ገልበጥ አድርጋ ጀርባው ላይ በመፈረም ፊርማዋ በጣም ቀላል የሚባል እንደሆነ በመግለጽ መለሰችልን፡፡ እንደገና ደግሞ ዘወር ብላ ከመሳቢያ ሌሎች ሁለት ሠነዶችን በማውጣት የሁለት የበላይ አለቆቿን ፊርማ አሳይታን የእሷ በንፅፅር ምን ያህል ቀላል ሊባል የሚችል እንደሆነ ልታስረዳን ሞከረች፡፡

ካሳየችን ፊርማዎች አንደኛው አስመስሎ ለመፈረም ማሰብ ይቅርና ምን ዓይነት ፊርማ ነው (ማለትም በስም ወይስ …)  የሚለውን እንኳ ለመረዳት ትንሽ ጊዜ የሚወስድ ይምስላል፡፡ የብዙዎች የፊርማ መነሻ ስማቸው ነው ማለት ስህተት ባይሆንም የሚፈርሙበትን ቀን ከስማቸው ጐን ለጐን መነሻ የሚያደርጉም አጋጥመውናል፡፡ በሥራቸው የተለየ ሁኔታ (ለምሳሌ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ) ፊርማቸውን በተደጋጋሚ በማሻሻል ፊርማቸው ቀላል የሚባል እንዳይሆን እንዳደረጉ የነገሩንም ጥቂት አይደሉም፡፡

ፊርማዋ ቀላል የሚባል ቢሆንም ቀላል መሆኑ አሳስቧት እንደማያውቅ ልሳን ትናገራለች፡፡ ፊርማዋ እንዲህ ባይሆን ጥሩ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ይህ እንዲያሳስባት ግድ ያለ ሁኔታ አላጋጠማትም፡፡ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገችና በአንድ ማየት ለተሳናቸው የትምህርት ድጋፍ በሚሰጥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በፋይናንስ ኃላፊነት የምትሠራ ወይዘሮ ደግሞ ፊርማዋ ከልሳን በተቃራኒው ከባድ የሚባል እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ከታች ዝም ብለን የለመድነውን ፊርማ ይዘን መጥተን እንደዚህ ያለ ትልቅ ኃላፊነት ላይም በዚያ መቀጠል አስቸጋሪ ይሆናል›› ትላለች፡፡

እሷ እንደምትለው በተለያዩ ተቋማት ስትሠራ እንዳስተዋለችው በተቋማት በባንኮችም የሒሳብ ሠራተኛ ፊርማ በቀላሉ ኮፒ የሚደረግ መሆን እንዲሁ የሚታለፍ አይደለም፡፡ በጣም ቀላል ፊርማ ስለነበራት በባንኮች የተሻለ ፊርማ ተለማምዳ እንድትመለስ የተነገራት የፋይናንስ ሠራተኛ ታውቃለች፡፡

የግለሰቦችን ፊርማ አስመስለው ባንክን ለማጭበርበር የሚመጡ እንዳሉ በአንድ ባንክ በኃላፊነት ደረጃ የሚሠሩ ነግረውናል፡፡ በተለይ ቼክ ላይ ተመሳሳይ ፊርማ ተጠቅሞ ለማጭበርበር መሞከር ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ቀደምም ቼክ ላይ የተጭበረበረ ዓርማ ተጠቅሞ የመጣ ግለሰብ ስልክ ተደውሎ ለማረጋገጥ በሚሞከርበት ወቅት ድንገት ከባንኩ ወጥቶ ማምለጡን፣ ጉዳዩንም ለፍትህ አካል ማሳወቃቸውን ያስታውሳሉ፡፡

የቁጠባ ሒሳብ ላይ በፊርማ የማጭበርበር ዕድሉ አናሳ መሆኑን ሆኖም ለረዥም ጊዜ ሳይንቀሳቀስ በመቆየቱ በባንኩ እንዳይንቀሳቀስ (Inactive) የተደረገን የሒሳብ ደብተር ባንክ ውስጥ ከሚሠሩ ጋር በመመሳጠርና ፊርማን በማስመሰል ወደሌላ አካውንት እንዲገባ በማድረግ ወንጀል የሚፈጽሙ እንዳጋጠሙም ይናገራሉ፡፡

የባንክ ደብተር በፊርማ ብቻ ይንቀሳቀስበት ከነበረው ጊዜ ሲነፃፀር ግን ፊርማና ፎቶ አንድ ላይ የባንክ ሲስተም ውስጥ መግባቱ በፊርማ የመጭበርበር ዕድለን መቀነሱን ይገልጻሉ፡፡ 

እንደ ፒን ኮድ እንዲሁም አሻራ ያሉ ነገሮች በስፋት አገልግሎት ላይ እየዋሉ ባሉበት በዚህ ጊዜ የፊርማ አስፈላጊነት እምብዛም እንደሆነ ብዙዎች ቢያስቡም፣ ዛሬም ከሒሳብ እንዲሁም ከሕግ ጋር በተገናኘ የፊርማ አስፈላጊነት ወሳኝ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፊርማዎች ዛሬም ሰዎች ቃላቸውን፣ ስምምነታቸውን የሚያረጋግጡበት ነገር ነው፡፡ ይህ በሽያጭ፣ በውልና በሌሎች ነገሮች ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ከእነዚህ ነገሮች ጋር በተያያዘ በፊርማዎች ኮፒ መደረግ ባልጠበቁት መንገድ የተጐዱ በተቃራኒው ያልደከሙበትንና የማይገባቸውን ያገኙና ለማግኘት ሲሉ የተደረሰባቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ