– 101 ጥቅል ብረት በቁጥጥር ሥር ውሏል
መንግሥት በልዩ ፕሮግራም ከያዛቸው የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች አንዱ ለሆነው የ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል፣ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ የአርማታ ብረት በመዝረፍ የተጠረጠሩ 30 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ወንጀሉን በዋናነት ያቀናበሩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የግብዓት፣ ክምችትና ሥርጭት ሙያተኛ፣ ባለሀብቶችና ተባባሪዎች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አባላትና በሌሎች የፀጥታ ሠራተኞች ትብብር በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡
የኢንተርፕራይዙ ባልደረባ ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለእያንዳንዳቸው የሲኖትራክ ሾፌሮች 2,000 ብር ለመክፈል በመስማማት በ15 ሲኖትራኮች ጎፋ ከሚገኘው የኢንተርፕራይዙ ማዕከላዊ መጋዘን ባለ 8 የብረት ዓይነት 67 ጥቅልና ባለ 6 የብረት ዓይነት 34 ጥቅል፣ በድምሩ 101 ጥቅል ብረት እንዲጫን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
ስማቸው ለጊዜው እንዲገለጽ ያልተፈለገ ባለሀብት በ15 ሲኖትራኮች የተጫኑትን ብረቶች ሰበታ አካባቢ ከሚገኘው ፋብሪካቸው ውስጥ እንዲወርድ ካደረጉ በኋላ፣ መርካቶ አካባቢ ለሚገኙ ግብረ አበሮቻቸውና ወደ አዳማ በሽያጭ እንዲሠራጭ ማድረጋቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ፖሊሶች ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት ትብብር፣ ከኢንተርፕራይዙ ወጥቶ የተበተነው የአርማታ ብረት ደብዛው ሳይጠፋ በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን ምንጮች አክለዋል፡፡ የኢንተርፕራይዙ ባለሙያ ለጊዜው ተሰውረው እንደነበር ምንጮች አክለዋል፡፡
ባለሀብቶቹን፣ ሌሎች ተጠርጣሪዎችንና ብረቱን በአጭር ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ያዋለው ፖሊስ፣ የኢንተርፕራይዙ ባለሙያ ለጊዜው ከተሸሸጉበት ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደ አዲስ አበባ እንዳመጣቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ቀርበው የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸውና ሌሎች ተባባሪዎችን ለመያዝ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራዎች እያደረገ መሆኑም ታውቋል፡፡ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ብረትም በኤግዚቢትነት ተይዞ በፖሊስ ልዩ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዕትም ‹‹ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል በ15 ሲኖትራኮች የተጫነ ብረት መጥፋቱ ተጠቆመ›› በሚል ርዕስ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡