Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተዛወሩ

የሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደ ኦሮሚያ ክልል ተዛወሩ

ቀን:

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ቱሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ፡፡

በኦሮሚያ ክልል አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ፊርማ ሰኞ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣ ደብዳቤ፣ አቶ አህመድ ቱሳ ለአምስት ዓመታት በኃላፊነት ከሠሩበት ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ተነስተው ወደ ኦሮሚያ ክልል ተዛውረዋል፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥት ባለሁበት ቦታ እንድቆይ ቢፈልግም፣ የኦሮሚያ ክልል መዋቅሮችን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሶ እንድዛወር ተደርጓል፤›› ሲሉ አቶ አህመድ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ አህመድ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩ ሲሆን፣ በኋላም የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ኮርፖሬሽን፣ የደረቅ ወደብ አስተዳደርና የባህር ትራንዚት ባለሥልጣን አንድ ላይ ሆነው የተቋቋመውን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግለዋል፡፡

አቶ አህመድ የአምስት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸውን ውጤታማ እንደነበር ቢገልጹም፣ የማይስማሙ አሉ፡፡ እነሱም በአምስት ዓመት ውስጥ በርካታ ሙያተኛ ሠራተኞች ድርጅቱን መልቀቃቸውን፣ የደረቅ ወደቦችና የባቡር መስመር ሳይጣጣሙ መቅረታቸውን፣ የደንበኞች እርካታ መቀነሱንና የማኔጅመንትና የሠራተኞች ግንኙነት መዳከሙን ይጠቅሳሉ፡፡

በእነዚህ ነጥቦች ላይ የኢንተርፕራይዙ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኩሪያ ኃይሌ በነበሩበት ዘመን ግምገማ መደረጉን፣ ሰሞኑን በኦሮሚያና በፌዴራል መንግሥት መዋቅሮች በተካሄዱ ግምገማዎችም እነዚህ ነጥቦች ነጥረው መውጣታቸውን ያስረዳሉ ይላሉ፡፡

ነገር ግን አቶ አህመድ እነዚህን ክሶች አይቀበሏቸውም፡፡ አቶ አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፋይናንስን በተመለከተ በ2003 ዓ.ም. የመሥሪያ ቤቱ ገቢ አንድ ላይ ተደምሮ 4.7 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም. ግን ይህ ገቢ በአራት እጥፍ ጨምሮ 16.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል ሲሉም ያክላሉ፡፡

የመልቲ ሞዳል አሠራር በ2004 ዓ.ም. ሲጀመር በዓመት አሥር ሺሕ ኮንቴይነር የማንሳት አቅም ነበር፡፡ ነገር ግን በ2008 ዓ.ም. ኮንቴይነር የማንሳት አቅም 175 ሺሕ ደርሷል፡፡

የደንበኞች እርካታን በሚመለከት አቶ አህመድ ሲያስረዱ፣ በ2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የደንበኞች እርካታን በሚመለከት ጥናት ተካሂዷል፡፡

በገለልተኛ ባለሙያዎች በተካሄደው በዚህ ጥናት 71.6 በመቶ የሚሆኑ ደንበኞች በድርጅቱ አገልግሎት እንደረኩ መግለጻቸውን በመጥቀስ፣ ውጤት ተመዝግቧል ሲሉ አቶ አህመድ የደንበኞች እርካታ የደረሰበትን ደረጃ አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለምሳሌ ወደቡ ሲጨናነቅና የትራንስፖርት እጥረት ሲያጋጥም ደንበኞች ሊማረሩ እንደሚችሉ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ