Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለውስብስብ ችግሮች ተዳርገናል ያሉ የግብርና ኢንቨስተሮች ምሬታቸውን ገለጹ

ለውስብስብ ችግሮች ተዳርገናል ያሉ የግብርና ኢንቨስተሮች ምሬታቸውን ገለጹ

ቀን:

በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ተንሰራፍቶ የቆየውን ችግር በቅጡ ለመረዳትና መፍትሔ ለመስጠት አዲሱ የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር እያሱ አብረሃ፣ ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በጠሩት ስብሰባ ባለሀብቶች ምሬታቸውን ገለጹ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ካቢኔ ውስጥ ከተካተቱ አዳዲስ ሚኒስትሮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር እያሱ፣ በበርካታ ችግሮች የተተበተበው የግብርና ኢንቨስትመንት ያለበትን ደረጃ ለማወቅና መፍትሔም ለማበጀት ይህንን ስብሰባ ቢጠሩም፣ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሟቸው ስብሰባውን አቋርጠው ሄደዋል፡፡

በእሳቸው ምትክ ከአንድ ዓመት በፊት የተሾሙት የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር ስብሰባውን መርተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ 100 የሚጠጉ ከፌዴራል መንግሥት መሬት የወሰዱ የግብርና ኢንቨስተሮች የተገኙ ሲሆን፣ የመናገር ዕድል የተሰጣቸው ኢንቨስተሮች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የተዘፈቁ ቢሆኑም መፍትሔ የሚሰጥ አካል በመጥፋቱ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ እየመከነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ካሉት ችግሮች መካከል የመሬት አሰጣጥ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የመሠረተ ልማት፣ የብድር አቅርቦት ላይ ያሉ ችግሮች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

በመሬት አሰጣጥ በኩል የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች በውክልና የወሰደውን መሬት፣ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ለባለሀብቶች ይሰጣል፣ ያስተዳድራልም፡፡

ነገር ግን ኤጀንሲው በሰጠው መሬት ላይ ችግር ሲያጋጥም መፍትሔ እንዲሰጡ የሚጠበቁት ክልሎች ናቸው፡፡ ይህ አሠራር ለዘርፉ ማነቆ ሆኗል በማለት በስብሰባው ላይ ተነስቷል፡፡

የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲው በተለይ በጋምቤላ ክልል የሰጣቸው ቦታዎች መደራረብ የሚታይባቸው በመሆኑ ከፍተኛ ችግር አጋጥሟል፡፡ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት በዘርፉ ችግር እንዳለ አምነው፣ በተለይ በጋምቤላ ክልል በታችኛው መዋቅር የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ለዘርፉም ብድር እየቀረበ አለመሆኑን አቶ አበራ ጠቅሰው፣ የብድር አቅርቦት ግን የእሳቸውን መሥሪያ ቤት እንደማይመለከት አስረድተዋል፡፡

በስብሰባው ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሀብቶች በመጀመሪያ ደረጃ ኤጀንሲው በትክክል የማያስተዳድረውን የእርሻ መሬት ለምን ይሰጣል? ኤጀንሲው በሰጠው መሬት ላይ ችግር ሲፈጠር ክልሎቹ እንዲፈቱት መጠበቅ አግባብ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ለግብርና ኢንቨስትመንት ብድር እንዳይቀርብ በደብዳቤ የጠየቀው መሬት አስተዳደር ኤጀንሲው ራሱ መሆኑን ባለሀብቶቹ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ቢያቆም እንኳ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፉ በመንግሥት ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ እንደመሆኑ፣ የታገደው ብድር አሰጣጥ እንዲጀመር ማድረግስ አልነበረበትም ወይ?›› በማለት አንድ ባለሀብት ጠይቀዋል፡፡

የጥጥ ኢንቨስትመንት የግብርና ሥራ ቢሆንም፣ የጥጥ ጉዳይን የሚከታተለው ዳይሬክቶሬት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር በሚገኙ ተቋማት ውስጥ እንዲገባ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢንቨስትመንት አዋጁ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለሀብቶችን በመወከል የፋይናንስ አቅርቦት፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲሟሉ ያደርጋል የሚል ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ይህንን አድርጎ እንደማያውቅ ባለሀብቶች በምሬት ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ኦሞ ኢንቨስት ለማድረግ ቦታ የወሰዱ ኢንቨስተሮችም ምሬታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ በደቡብ ኦሞ ለዓመታት መጠናቀቅ ያልቻለውና በአንድ ወቅት በመገንባት ላይ የነበረው የኦሞ ድልድይ በድጋሚ ችግር ውስጥ በመሆኑ፣ በጥልቀት ወደ እርሻ ሥራ መግባት አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ እያሉ ግን የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲው ማስጠንቀቂያ ከሰጣቸው ኩባንያዎች መካከል ኦሞ ቫሊ፣ ዳሰኒ እርሻ፣ ዶ/ር ጠአመ እርሻ፣ ዳሰነች እርሻ፣ ጉቲት እርሻ ልማት ይገኙበታል፡፡

እነዚህ የእርሻ ልማት ድርጅቶች በራሳቸው ፋይናንስ በተወሰነ ደረጃ ሥራ እየሠሩ ቢሆንም፣ ድልድዩ ተጠናቆ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ሰጥቷቸው በስፋት ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተስፋ ቢያደርጉም፣ ድልድዩ መጠናቀቅ ካለመቻሉም በላይ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ኤጀንሲው ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ማስጠንቀቂያ መጻፉ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡

የባለሀብቶቹን ቅሬታ የሰሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰዓዳ ችግሮቹን መረዳታቸውን በመግለጽ፣ መንግሥት ለባለሀብቶቹ ዕገዛ ለማድረግ የሚያስችለውን ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ቃል ገብተዋል፡፡

መንግሥት ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚመለከተውና በአጭር ጊዜም መፍትሔ እንደሚሰጥ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...