በመላ አገሪቱ የደን ልማት ሥራን ውጤታማ ለማድረግና ማኅበረሰቡ የደን መራቆትን በመከላከል በደን ልማት ሥራ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችሉ የምርምር ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር በዘርፉ የተሰማሩ የምርምር ተቋማት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ማዕከል ከሌሎች ተባባሪ አካላት ጋር ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ሕሩይ አዳራሽ ባካሄደው ዐውደ ጥናት ላይ በርካታ በመስኩ የተካሄዱ የጥናትና ምርምር ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
ለሁለት ቀናት የቆየው ይህ ዐውደ ጥናት በደን ምርምር ውጤቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን፣ በማዕከሉ የ40 ዓመታት ጥናትና ምርምር ሥራዎች በተመዘገቡ ውጤቶችና ባጋጠሙ ተግዳሮቶች ላይ መክሯል፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ገመዳ ዳሌ የምርምር ተቋሙ የአገራችንን የተራቆቱ መሬቶች በደን ለመሸፈን እንዲሁም ለተለያዩ የአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የደን ውጤቶችን ለማስተዋወቅና ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል በሚያደርገው ጥረት ሁሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በዐውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ውባለም ታደሰ ደግሞ ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ሥራ የጀመረው ማዕከሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በደን ልማት፣ በአግሮ ፎረስተሪ፣ ለደን ልማት የሚውል የዘር አቅርቦት፣ የደን ጥበቃ፣ የደን ውጤቶች አጠቃቀም እንዲሁም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት፣ በዘርፉ የሚያስፈልገውን ዕውቀትና መረጃዎች ወደ ማኅበረሰቡ ማድረስና በሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ በርካታ ጥናትና ምርምሮች ማካሄዱን አስታውቀዋል፡፡
ዶ/ር ውባለም አያይዘውም የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች ባካሄዷቸው ጥናትና ምርምሮች የተገኙ ቴክኖሎጂዎችና የወጡ መረጃዎች በተለያዩ መንገዶች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ሆነው በአገር አቀፍ ደረጃ የኅብረተሰቡን አኗኗር በማሻሻል ዘርፉ ለብሔራዊ ኢኮኖሚው የበኩሉን ድርሻ እንዲጫወት፣ የተራቆቱ የአገሪቱ መሬቶች በደን እንዲሸፈኑ፣ አዋጭ ማኅበረሰብ አቀፍ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራዎች እንዲካሄዱ የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ የአካባቢና የደን ምርምር ማዕከል በአሁኑ ወቅት ከ65 በላይ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያቀፈ ተቋም ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታት በመላው አገሪቱ ከ160 በላይ የውጭ አገር የዛፍ ዝርያዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና በማላመድ አሰራጭቷል፡፡ ማዕከሉ ለደን ልማት ኢንቨስትመንት አመቺ የሆኑ ዝርያዎችን ለይቶ በማውጣት ለዝርያዎቹ ተስማሚ የሆኑ አካባቢዎችን አጥንቶ ወደ ሥራ የሚገባበትን ሁኔታም እያመቻቸ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በተቋሙ በየዓመቱ በአማካይ ከስምንት ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ የዛፍ ዘር በመላ አገሪቱ የሚሰራጭ ሲሆን፣ የተለያዩ የደን ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ በማስተዋወቅ በጥምር እርሻ እንዲሁም የፍራፍሬ ዛፎችን በማልማት፣ በዕጣንና ሙጫ፣ በቀርከሃ፣ በመድኃኒት ዕፅዋት እንዲሁም በሞሪንጋ ተክል ልማት የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግና የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ለማስቻል በተነደፉ ማዕቀፎች ተጠቃሚ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሕይወት የቀየሩ ሥራዎች መከናወናቸው በዐውደ ጥናቱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
የማዕከሉ የ40 ዓመታት የደን ምርምር ሥራዎችና ውጤቶች በተገመገሙበት በዚህ የሁለት ቀናት ዐውደ ርዕይ ላይ የተካፈሉ አስተያየት ሰጪዎችም የደን ምርምር ተቋማት ማኅበረሰብ አቀፍ አዋጪ የደን ልማት ምርምር እንዲያካሂዱ ጠይቀዋል፡፡