የአሜሪካ ኤምባሲ በጨለንቆና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተነሱ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት በመጥፋቱና የአካል ጉዳት በመድረሱ እጅግ እንዳሳሰበውና እንዳዘነ ገለጸ፡፡ ኤምባሲው በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም በተለያዩ ምክንያቶች በአማራ፣ በትግራይና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሥራ እንደ ተስተጓጎለ ይታወቃል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲም በጨለንቆና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በተከሰቱ ግጭቶች የተሳተፉትን መንግሥት ተጠያቂ እንዲያደርግና የዜጎቹን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚደነቀውንና አብሮት የቆየውን ብዝኃነት የማክበር ልምድ እንዲጠብቅና ልዩነቱን በጋራ መፍታት ይችል ዘንድ ዘዴዎችን እንዲቀይስ በማሳሰብ ኤምባሲው መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡