በአዳማ ከተማ ከአንድ ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አዲስ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታና በነበሩ ላይ ደግሞ የአቅም ግንባታና የማሻሻያ ፕሮጀክት በመከናወን ላይ መሆኑን የከተማው አስተዳደር መጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
ዋናው ሥራ አስኪያጁ አቶ ነጋሳ ለሚ ይህንን አስመልክተው ከሪፖርተር ጋር በስልክ ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ ለአዲሱ የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ 1.064 ቢሊዮን ብር፣ ለማስፋፊያው ፕሮጀክት ማከናወኛ ደግሞ 300 ሚሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል፡፡
አዲሱ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የትኩረት አቅጣጫ ከሞጆ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ በአንድ የገጠር አካባቢ 26 ጉድጓዶችን ቆፍሮ ውሃ ማውጣትና የተመረተውንም ውሃ በቧንቧ በመሳብ ለአዳማ ከተማ ነዋሪዎች እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡
ይህ የሞጆ አዳማ ፕሮጀክት የረጅም ጊዜ ዕቅድ ቢሆንም፣ ከወዲሁ ግን ልዩ ልዩ መሠረተ ልማቶች መከናወናቸውን ሥራ አስኪያጁ ይገልጻሉ፡፡
እሳቸው እንዳሉት፣ የማስፋፊያው ፕሮጀክት የሚከናወነው በ1990ዎቹ ቆቃ ከሚገኘው አዋሽ ወንዝ ተጠልፎ ለአዳማ ከተማ አገልግሎት እየሰጠ ባለው የውሃ ተቋም ላይ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ይኸው ተቋም በቀን የሚያመርተውን 26 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ውሃ ወደ 40 ሺሕ ሜትር ኪዩብ ከፍ የማድረግና የውሃ ማጣሪያውን (ወተር ትሪትመንት ፕላን) የማሳደግ ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመካከለኛ ጊዜ ዕቅድ ውስጥ የተካተተው ይህ የቆቃ አዳማ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሥራ 97 ከመቶ ያህሉ እንደተጠናቀቀ፣ ለሙከራ ያህል ውሃ እንዳመረተ፣ በሙሉ አቅሙ የማምረት ሥራውን ሲጀምር ግን የሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ድረስ ያገለግላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋናው ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ለሞጆ አዳማ ፕሮጀክት የተመደበው ገንዘብ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በብድር የተገኘ ሲሆን ለቆቃ አዳማ ፕሮጀክት የዋለውን ገንዘብ የመደበው ደግሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መሆኑን ከአቶ ነጋሳ ማብራሪያ ለመደረጉ ተችሏል፡፡
ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ዓመተምሕረት ተቋቋሞ የነበረው ይህ የውሃ ተቋም እስከ 20 ዓመት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ነበር የተሰራው ነገር ግን የጊዜው ገደብ ከመድረሱ አስቀድሞ የከተማው ነዋሪዎች ቁጥር በመጨመሩ የውጪ አቅርቦት እጥረት እንደተከሰተ ማወቅ ተችሏል፡፡