አሥራ አንደኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅ) ጉባኤ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል አደጋ ያንዣበባቸው ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ይገኝበታል፡፡ ኅዳር 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መካሄድ በጀመረው የአምስት ቀናት ጉባኤ ከበርካታ አገሮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከመወያያ ነጥቦቻቸው ውስጥ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ነባራዊ ሁኔታ ተጠቃሽ ነው፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ዕለት፣ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊም አደጋ በባህላዊ ቅርሶች እያጠላ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ዩኔስኮ በመዝገቡ ያሰፈራቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ ከለላ ቢያደርግም ቅርሶቹ በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ መውደቃቸው አልቀረም፡፡
የዩኔስኮ ተባባሪ ዋና ዳይሬክተር ፍራንሴስኰ ባንዳሪን እንደገለጹት፣ እንደ ጦርነት ያሉ ሁኔታዎች የባህላዊ ቅርሶችን ህልውና አደጋ ውስጥ ከተዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ከሚጠቀሱ አገሮች ሶሪያ አንዷ ናት፡፡ አገሪቷ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶቿን ለመጠበቅ ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ‹‹አብዛኞቹ የአገሪቱ ዜጎች በስደትና በውጥረት ባሉበት ሁኔታ ባህላዊ ቅርሶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ የማሸጋገር ነገር ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ዩኔስኮ ከሁለት ዓመታት በፊት ‹‹ዘ ኢመርጀንሲ ሴፍጋርዲንግ ኦፍ ዘ ሲሪያን ካልቸራል ሔሪቴጅ ፕሮጀክት›› በሚል ለአገሪቱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ የሚያደርግበት ፕሮጀክት መዘርጋቱ ይታወሳል፡፡ ከዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ኮንቬንሽን አንዱ ክፍል አደጋ ያንዣበበባቸው ቅርሶች የሚመዘገቡበት ሲሆን፣ እንደ ሶሪያ ሁሉ ተቋሙ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ሌሎች አገሮችም አሉ፡፡
ፍራንሴስኮ እንደገለጹት፣ በመካከለኛው ምሥራቅና ሌሎችም የዓለም ክፍሎች በግጭት ሳቢያ አደጋ ውስጥ የወደቁ ባህላዊ ቅርሶች ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ ዩኔስኮ እነዚህን ቅርሶች ለመጠበቅ የሚያደርገው የገንዘብ ድጎማ እንዳለ ሆኖ፤ የመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች እገዛም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዮናስ ደስታ የሚመራ 24 አባላት ያሉት ኮሚቴ በአሥራ አንደኛው ጉባኤ በአፋጣኝ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የተጠየቁ ባህላዊ ቅርሶችን ይመዝናል፡፡ ኮሚቴው የሁሉም አኅጉሮች ተወካዮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ ዘንድሮ አምስት ባህላዊ ቅርሶች ‹‹ሊስት ኦፍ ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅ ኢን ኒድ ኦፍ ኧርጀንት ሴፍጋርዲንግ›› በሚል እንዲመዘገቡ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
አንደኛው የከበሮ ጨዋታና ሌሎችም ሥርዓቶችን ያካተተ የቦትስዋና ባህላዊ ክንውን ሲሆን፣ ‹‹ዘ ዩዝ ኦፍ ሞሮፓ ዋ ቦጃሌባ ባካጋታላ ባ ካፍላ ኤንድ ኢትስ አሶሽየትድ ፕራክቲስስ›› በሚል ቀርቧል፡፡ ‹‹ቻፒ ዳንግ ቬንግ›› የተባለ የካምቦዲያ የሙዚቃ ጨዋታ፣ የፖርቱጋል የጥቁር ሸክላ ሥራ ሒደት (ቢስሀሌስ)፣ የዩጋንዳ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንስ ክንውን (ማዲ ቦል ሊሬ) እና ከዩክሬን የኰሳክ ማኅበረሰብ ሙዚቃ ይገኙበታል፡፡
ከነዚህ ባህላዊ ቅርሶች መካከል ኮሚቴው በአፋጣኝ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ብሎ የተስማማባቸው በዝርዝሩ ይካተታሉ፡፡ ፍንሴስኰ እንደተናገሩት፣ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በአንድ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወቱ ጠንካራ ጥበቃ ያሻቸዋል፡፡ በርግጥ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በከተሜነት መስፋፋትና ሌሎችም ዘመን አመጣሽ ሁነቶች የቀደመ ይዘታቸው ሊቀየር ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ዩኔስኮ አንድ ማኅበረሰብ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ያለበት ባህላዊ ቅርስ አንዳች ቅርፅ ሊኖረው ይገባል ባይልም ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ‹‹ለማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ሲደረግ፣ የቅርሶቹ ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ ክንውኖቹን እንዲያካሂድ በማስቻል ነው፡፡ በጦርነት፣ ከመኖሪያ አካባቢ በመፈናቀልና በሌሎችም ምክንያቶች ሳቢያ ባህላዊ ቅርሱ እንዳይጠፋ እገዛም ይደረጋል፤›› ሲሉ ፍራንሴስኰ አስረድተዋል፡፡
በባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ረገድ ያለፉት ዓመታትን ተሞክሮ በመመርኮዝ ለቀጣዩ ትምህርት እንደሚወስድም አመልክተዋል፡፡ ባህላዊ ቅርሶቹን የመጠበቅ ሒደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈታኝ እየሆነ ቢሄድም የዩኔስኮን ኮንቬንሽን ተግባራዊነት በማስጠበቅ ጥረቶች እንደሚቀጥሉ አክለዋል፡፡
የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ኮንቬንሽን (ከ195 አገሮች 171 ያፀደቁት) መተግበር ከጀመረ አሥር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታትም 43 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በአፋጣኝ ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ በዝርዝሩ የተካተቱ ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት አገሮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም በቅርሶቹ ጥበቃ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችም ተተግብረዋል፡፡ እስካሁን በ106 አገሮች የተተገበሩ 133 ፕሮጀክቶች ከ21 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶባቸዋል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ፣ አደጋ ያንዣበባቸው ቅርሶችን ለመታደግ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ እየተረደገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የአባል አገሮች የገንዘብ መዋጮ እየጨመረ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ መዋጮው ቢጨምርም ጥቅም ላይ ሳይውል የሚቀር ገንዘብም አለ፡፡ እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ፣ ባለፈው ዓመት ዩኔስኮ አደጋ ውስጥ ላሉ ባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ከመደበው ገንዘብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላሩ ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት የተባለው ደግሞ ከሥራ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ መሰናክሎች መኖራቸው ነው፡፡
አቶ ዮናስ፣ ባህላዊ ቅርሶች በአፋጣኝ ድጋፍ የሚደረግላቸው ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ አስቀድሞ መንከባከብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶቹን የሚጠብቅበትን መንገድ በማመቻቸት ረገድ መንግሥት ትልቁን ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ የባህላዊ ቅርሱ መገለጫ ለሆኑ ክንውኖች እንዲሁም ለተፈጥሯዊ ወይም ግዑዝ ነገሮችም ጥበቃ ያሻል ብለዋል፡፡
‹‹ባህላዊ ቅርሶች ከለላ ካልተደረገላቸው ይጠፋሉ፡፡ በጥበቃው ሒደት መንግሥታት ሕጋዊ ከለላ መስጠት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥም በልማት ሥራዎች መስፋፋት በባህላዊ ቅርሶች አደጋ እንዳይጋረጥባቸው ከለላ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የዩኔስኮ ኮንቬንሽን፣ የባህላዊ ቅርሶችን ጥበቃ የሚያረጋግጥ ፖሊሲ አገሮች መተግበር እንዳለባቸው ያትታል፡፡ አገሮች ለባህላዊ ቅርሶቻቸው የሚያደርጉትን ጥበቃ በተመለከተ ለዩኔስኮ ኮሚቴ አባል አገሮች በየጊዜው ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡
በዩኔስኮ አሠራር መሠረት፣ በአመርቂ ሁኔታ ጥበቃ እየተደረገላቸው ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው እየተሸጋገሩ ያሉ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች እንደ ተምሳሌት ይመዘገባሉ፡፡ በዩኔስኮ ‹‹ቤስት ሴፍጋርዲንግ ፕራክቲስስ›› መዝገብ የሚሰፍሩት ባህላዊ ቅርሶች፣ በቅርስ ጥበቃ ረገድ ለዓለም እንደ ማስተማሪያ ይሆናሉ ተብለው የታመነባቸው ናቸው፡፡ የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ኮንቬንሽን ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ 12 ባህላዊ ቅርሶች በተምሳሌትነት ተመዝግበዋል፡፡ በዘንድሮው ጉባኤ ደግሞ ሰባት የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በተምሳሌትነት የይመዝገብልን ጥያቄ ቀርቦባቸዋል፡፡
ኮሚቴው ከሚመዝናቸው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል የኖርዌይ ባህላዊ የጀልባ አሠራር የመማር ማስተማር ሒደትና የፉጂ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚያግዝ ባህላዊ የካርታ ዝግጅት ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ 37 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ (ሪፕረዘንታቲቭ ሊስት ኦፍ ዘ ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅ) እንዲሰፍሩ ተጠይቋል፡፡ የገዳ ሥርዓትን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ባህላዊ ቅርሶች በኮሚቴው ከተመዘኑ በኋላ፣ በድምፅ ብልጫ እንዲመዘገቡ የተወሰነላቸው ቅርሶች ይፋ ይደረጋሉ፡፡
ባለፉት አሥር ዓመታት 366 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከመላው ዓለም ተመዝግበዋል፡፡ ቅርሶቹን ያስመዘገቡ አገሮች የኮንቬንሽኑን ድንጋጌዎች መከተላቸው በጉባኤው ይፈተሻል፡፡ ባህላዊ ቅርሶቹን ለመጠበቅ ዩኔስኮ የመደበው በጀት አጠቃቀምም ይመዘናል፡፡
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ባህላዊ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ በዩኔስኮ መዝገብ መስፈራቸው አስተዋጽኦ አለው፡፡ እስካሁን ከአፍሪካ 21 የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች በወካይ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ሰፍረዋል፡፡ ከአፍሪካ ተምሳሌት ይሆናሉ ተብለው የተመዘገቡ ባህላዊ ቅርሶች የሉም፡፡ ዘጠኝ ባህላዊ ቅርሶች በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በሚል ተመዝግበዋል፡፡
እሑድ ኅዳር 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የተጀመረው የዩኔስኮ ጉባኤ ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያምና የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳ በተገኙበት የተከናወነው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል የሚያንፀባርቅ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜና ሌሎችም ጥበባዊ ትርዒቶች ቀርበዋል፡፡