Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምፊደል አሌሃንድሮ ካስትሮ ሩዝ (1926-2016)

ፊደል አሌሃንድሮ ካስትሮ ሩዝ (1926-2016)

ቀን:

ከሦስት ወራት በፊት ኩባውያኑ የሚያከብሯቸውን የቀድሞው መሪያቸው ፊደል ካስትሮን 90ኛ የልደት በዓል ለማክበር ሽር ጉድ እያሉ ነበር፡፡ የልደታቸው ቀን በሚውልበት ነሐሴ 7 ቀን ለፊደል ካስትሮ ልዩ ስጦታ ለማበርከት ሲታትሩ ከቆዩት መካከል፣ የኩባ ሲጋራ አምራቹ ጆሲ ካስትለር አንዱ ነበር፡፡ ካስትለር ከረዳቶቹ ጋር በመሆን ለ10 ቀናት በቀን 12 ሰዓት እየሠሩ 90 ሜትር የሚረዝመውን ሲጋራ ሠሩ፡፡ ፊደል ካስትሮ ሲጋራ ማጨስ ያቆሙት በ1980ዎቹ ቢሆንም፣ የወጣላቸው አጫሽ እንደነበሩ ለማስታወስ ሲጋራው ተሠርቶ ለልደት በዓላቸው ተበርክቶላቸዋል፡፡

ካስትሮ አብዝተው የሚወዱትን ሲጋራ ለማቆም የወሰኑት ሕዝባቸው ሲጋራ በማጨስ ከሚመጡ በሽታዎች ራሱን እንዲጠብቅ ለማስተማር ሲሉ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1985 ገደማ ከአንድ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፣ ‹‹ሲጋራ ከለኮስኩ ብዙ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ከዚህ ውሳኔ የደረስኩት አንድ ለሕዝቤ የምከፍለው የመጨረሻው መስዋዕትነት ሲጋራ ማጨስ ማቆም ስለሆነ ነው፡፡ ራሴን ከሲጋራ መነጠል ለኩባውያን ጤና የከፈልኩት መስዋዕትነት ነው፤›› ብለው ነበርና የቢዝነስ ኢንሳይደር ጋዜጠኛ ክርስቶፈር ውድ ለካስትለር አንድ ጥያቄ አቀረበለት፡፡

‹‹ካስትሮ ማጨስ ያቆሙት በ1980ዎቹ ነው፡፡ አንተ ደግሞ 90ኛ ዓመታቸውን ለሚያከብሩት ካስትሮ 90 ሜትር ርዝመት ያለው ሲጋራ ስጦታ አበርክተሃል፡፡ ትርጉሙ ምንድነው?›› አለው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ካስትለርም፣ ‹‹ካስትሮ እንደማያጨስ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ለልደቱ ሲጋራውን ለማበርከት ምን ያህል እንደለፋን ለማሳየት ነው፤›› ሲል ከፊደል ካስትሮ አገዛዝ ጠንካራ ሠራተኝነትን መማሩን ገለጸለት፡፡

እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 2006 ጀምሮ ሕመም ላይ የነበሩት ካስትሮ ለ49 ዓመታት የያዙትን ሥልጣን በይፋ የለቀቁትና ለወንድማቸው ራውል ካስትሮ ያስረከቡት እ.ኤ.አ. በ2008  ነበር፡፡ ከዚህ ጊዜ ወዲህ ብዙም በሕዝብ ፊት ያልታዩት ካስትሮ 90ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ለማክበር በሃቫና ካርል ማርክስ ቴአትር ማዕከል በተዘጋጀው ድግስ ከወንድማቸውና ከሌሎች ወዳጆቻቸው ጋር ተገኝተው ነበር፡፡

በዕለቱ የታደለውን መልዕክት ጠቅሶ ቢቢሲ እንዳሰፈረው ካስትሮ ሕዝባቸውን ሲያመሰግኑ፣ የአሜሪካ ተሰናባች ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጃፓንን በጎበኙበት ወቅት አሜሪካ በሔሮሺማ ላይ ለፈጸመችው በደል ይቅርታ አለመጠየቃቸው ትክክል አለመሆኑን ነቅፈዋል፡፡

ሕዝባቸው ላሳያቸው ክብርና ላበረከተላቸው ስጦታ ምሥጋና ያቀረቡት ካስትሮ፣ ‹‹ሕዝቤ ከጎኔ መሆኑን ለፓርቲ አባላትና ለወሳኝ ድርጅቶች ያሉኝን ሐሳቦች እንዳካፍል ጥንካሬ ሰጥቶኛል፤›› ሲሉም ለሕዝባቸው ያላቸውን ክብር አስተላልፈዋል፡፡

በአብዛኞቹ ኩባውያን ልብ ውስጥ የፍትሐዊነትና የማኅበራዊ እኩልነት ተምሳሌት የሆኑት ካስትሮ፣ 90ኛ የልደት በዓላቸውን ካከበሩ ከሦስት ወራት በኋላ ኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

በቁማቸው እያሉ በአልበገር ባይነታቸውና በሶሻሊዝም ጽንሰ ሐሳብ አቀንቃኝነታቸው የሚታወቁት ካስትሮ፣ በኩባ ትምህርትና ጤናን ሙሉ ለሙሉ ነፃ በማድረጋቸው የደሃ አባት ይባላሉ፡፡ ለደሃና ደሃ አገሮች ደጋፊ እንደነበሩም ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ‹‹ለደሃ አገሮች ከፊደል ካስትሮ የበለጠ የሠራ የለም፤›› የሚሉ አስተያየቶችም በሞታቸው ማግሥት እየተሰነዘሩ ነው፡፡

ለኩባውያንም ሆነ ለዓለም የካስትሮ ሌጋሲ የማይረሳ ነው፡፡ በሥልጣን በቆዩባቸው ዓመታት በስደት ያሉ ኩባውያን የሰብዓዊ መብት ይጥሳሉ ብለው ቢወነጅሏቸውም፣ በአገር ውስጥ እኩልነትንና ማኅበራዊ ፍትሕን አንግሠዋል፡፡ መንግሥታቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዶክተሮችና መምህራን አፍርቷዋል፡፡ በኩባ የሕፃናት ሞትና መሃይምነት በጣም ጥቂት ነው፡፡ ሆኖም መንግሥት መር የሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ኩባውያን ሀብታም እንዳይሆኑ አግዷል የሚል ትችት አለ፡፡

ካስትሮ ባደረጉት ድጋፍ ከኩባ ወታደሮች ጋር የኢትዮጵያ ጦር የዚያድ ባሬ መደበኛና ሰርጎ ገብ ወራሪ ወታደሮችን ከኢትዮጵያ ጠራርጎ ካስወጣ በኋላ፣ በ1971 ዓ.ም. በጅግጅጋ በተከናወነው የድልና የመልሶ ማቋቋም በዓል በመገኘትና ከወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ከሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር በመሆን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች የተስተናገዱበትን ኤግዚቢሽን በጋራ የከፈቱት ካስትሮ፣ በኢትዮጵያ በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ የነበራቸው ድጋፍም አይዘነጋም፡፡

በወቅቱ ከጅግጅጋ የአሥር ደቂቃ በረራ በማድረግም የኢትዮጵያና የኩባ ወታደሮች ‹‹የልምምድ አንበሳ›› በሚል መጠሪያ ያካሄዱትን የውጊያ ልምምድ መመልከታቸው ይታወሳል፡፡

የወቅቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ጋዜጠኛ እንደሚያስታውሱት፣ ካስትሮ ንግግር አላደረጉም፡፡ ሆኖም ከጋዜጠኛው በቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ ‹‹በታሪክ የማውቃትን ኢትዮጵያ በአካል በማየቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ሁለቱ አገሮች በጤናውና በትምህርቱ ዘርፍ አብረው የሚሠሩ ይሆናል፤›› ብለው ነበር፡፡ ቃላቸውን የጠበቁት ካስትሮ በወቅቱ በኢትዮጵያ ያደረጉት የጤናና የትምህርት ድጋፍም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ወረራ በኋላ ታይቶ የማይታወቅ አደገኛ ወረራ ሲካሄድባት ቀድመው የደረሱት ካስትሮ እንደነበሩ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም፡፡

ካስትሮ ከባላንጣቸው አሜሪካ ጋር በነበራቸው አሉታዊ ግንኙነት ሳቢያ፣ አሜሪካ ካስትሮን ከሥልጣን ለማስወገድ ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም፡፡ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከመጣል እስከ ግድያ ሙከራ ደርሳም ነበር፡፡ ሆኖም የኩባ የቀድሞ ዋና ደጋፊ ሶቪየት ኅብረት ከተበታተነች በኋላ እንኳን፣ አሜሪካ ኩባን ማንበርከክ ወይም አጋር ማድረግ አልቻለችም ነበር፡፡

ካስትሮን ለመግደል ከ600 በላይ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፣ አሜሪካም በብዙዎቹ እጇ እንዳለበት ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ ዘገባዎች፣ አሜሪካ ካስትሮን ለማስገደል ወይም ከሥልጣን ለማውረድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጋለች፡፡ ሆኖም አልተሳካላትም፡፡

የአሜሪካ ባለሀብቶች ከኩባ ጋር ያላቸውን ንግድ ሙሉ ለሙሉ ቢያቋርጡ፣ የአሜሪካ መንግሥት ደግሞ በኩባ የዴሞክራሲ አራማጅና የካስትሮ ተቃዋሚ የሆኑ ድርጅቶችን ቢረዱም ለውጥ አልተገኘም፡፡ ከባራክ ኦባማ በፊት በነበሩ አሥር ፕሬዚዳንቶች ዘመን ኩባን ለማንበርከክ የተከናወኑ ሽፍጦችም አልተሳኩም፡፡

የአሜሪካው 44ኛ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እ.ኤ.አ. በ2014 ያልተጠበቀ ንግግር ማድረጋቸው በኩባና አሜሪካ መካከል የነበረውን የሻከረ ግንኙነት አርግቦታል፡፡ ኦባማ አሜሪካ ከኩባ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማደስ እንደምትፈልግና በኩባ ላይ ተጥሎ የነበረው የንግድ ልውውጥና የጉዞ ማዕቀብም መላላት ለሁለቱ አገሮች መልካም አጋጣሚ ነበር፡፡ በአንድ በኩል በኩባ ላይ የተጣለ ገደብ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ በመናገራቸው፣ በሌላ በኩል በኩባ ዴሞክራሲን እናሰፍናለን የሚሉና ካስትሮን የሚቃወሙ ድርጅቶችን መደገፋቸው ያስተቻቸው ኦባማ፣ ከኩባ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረትም በአሜሪካ የታሰሩ ሦስት የኩባ ሰላዮችን ለቀዋል፡፡ ኩባም በምትኩ የአሜሪካ የልማት ሠራተኛ ተብለው ለሲአይኤ ሲሰልሉ የተገኙትን ሦስት አሜሪካውያን ለቃለች፡፡ ይኼ በኩባ ታሪክ ትልቅ ድል ቢሆንም ሥልጣናቸውን እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ ለወንድማቸው ራውል ካስትሮ ያስተላለፉት ካስትሮ ዝምታን ነበር የመረጡት፡፡ ‹‹አሁን ጦርነቱን አሸንፈናል፤›› ሲሉም መግለጫ የሰጡት ራውል ነበሩ፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን የላቲን አሜሪካ ታሪክ ሲነሳ ያለፊደል ካስትሮ አይሆንም የሚል አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን፣ የተለያዩ አገር መሪዎችም የካስትሮን ሞት ተከትሎ የሐዘን መግለጫ ልከዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ አጋር በነበሩት ካስትሮ ሞት የተሰማውን ሐዘን ለኩባ መንግሥት መግለጹን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ገልጿል፡፡ 

የአሜሪካው ተሰናባች ፕሬዚዳንት ኦባማ ‹‹ካስትሮ የሚዳኙት በታሪክ እንጂ በእኛ አይደለም፤›› ሲሉ፣ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አምባገነኑ ፊደል ካስትሮ ሞቷል፤›› ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ ‹‹ነፃና ገለልተኛ፣ ኩባን ከአጋሮቹ ጋር የገነባ፣ የሩሲያ ታማኝ ወዳጅ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተፅዕኖ ፈጣሪና ለሌሎች አገሮች አርአያ የሆነ የአንድ ክፍለ ዘመን መሪ፤›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡

የሜክሲኮው ፕሬዚዳንት፣ ‹‹የሜክሲኮ ጓደኛ፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በመከባበርና በንግግር ያሰፈነ መሪ፤›› ሲሏቸው፣ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናራንድራ ሞዲ ‹‹ፊደል ካስትሮ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ፈርጥ ነበር፡፡ ህንድ ታላቅ ጓደኛዋን በማጣቷ አዝናለች፤›› ብለው በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውን አሶቪየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

 የቫቲካን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ለፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ በላኩት ቴሌግራም ለቤተሰቡ መፅናናትን ሲመኙ፣ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዲዮ፣ ‹‹ታሪክ የማይረሳው አንደበተ ርቱዕ፤›› ብለዋቸዋል፡፡ የቻይናው ፕሬዚዳንትን ጂንፒንግ በበኩላቸው፣ ‹‹በዓለም ለሶሻሊዝም ዕድገት ታሪክ የማይረሳው አስተዋጽኦ ያደረገ መሪ፤›› ማለታቸውን ሲሲቲቪ ዘግቧል፡፡

የዩናይትድ ኪንግደም ሌበር ፓርቲ መሪ ጀርሚ ኮርባይን፣ ‹ካስትሮ የሕይወታችን ትልቅ ነፀብራቅ ነው፤›› ማለታቸውን ቢቢሲ አስፍሯል፡፡

ኮርባይን እንደሚሉት ካስትሮ የቱንም ያህል ስህተቶች ቢኖሩባቸውም፣ ከደቡብ አፍሪካ አፓርታይድን ለማስወገድ በነበራቸው ወሳኝ ሚና፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ፍትሕን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፈን ባበረከቱት አስተዋጽኦ ሁሌም ዓለም እንደማይረሳቸው ተናግረዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ፣ ‹‹አከራካሪ ሰው ቢሆንም ታሪካዊ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል፡፡

‹‹የፊደል ካስትሮ ሞት የኩባ የረዥም ጊዜ አገዛዝ ማብቂያና ለኩባውያን አዲስ ሕይወት መጀመርያ ነው፤›› ሲሉም ጆንሰን አክለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. ነሐሴ 13 ቀን 1926 በብሪያን ኩባ የተወለዱት ካስትሮ፣ የስድስት ዓመት ሕፃን ሳሉ ነው ሳንቲያጎ ከሚኖሩ መምህራቸው ጋር እንዲኖሩ የተላኩት፡፡ በስምንት ዓመታቸው በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተጠመቁት ካስትሮ እ.ኤ.አ. በ1945 የሐቫና ዩኒቨርሲቲን እስከተቀላቀሉ ድረስ ልዩ ትኩት የሚሰጡት ለስፖርት እንደነበር ይነገራል፡፡

በሐቫና ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍልን ሲቀላቀሉ የተጀመረው የፖለቲካ ሕይወታቸው ብዙ ፈተናን አስተናግዷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለመሆን ካደረጉት ያልተሳካ ቅስቅሳ ጀምሮ በኩባ ፍትሕ እንዲሰፍንና ሙስና እንዲጠፋ የታገሉት ካስትሮ፣ እ.ኤ.አ. በ1946 በኩባ ስለተሠራው ሙስናና በወቅቱ አገሪቱን ይመሩ የነበሩት ራምን ግራውስ መንግሥት ሥርዓት አልበኝነት የተናገሩት የብዙ ጋዜጦች የፊት ገጽ ሽፋን አግኝቶ ነበር፡፡ አብዮት አስነስተው የባቲስታን መንግሥት ለመገልበጥ ሙከራቸው ቢከሽፍም፣ በኋላ ግን በሽምቅ ውጊያ ባቲስታን ገልብጠው የፖለቲካና የወታደራዊ ሥልጣኑን መቆጣጠር ችለዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ሕይወታቸው ጀምሮ አሜሪካ በካሪቢያን ያላትን ጣልቃ ገብነት ሲነቅፉ የነበሩትና ኢምፔሪያሊዝምን የሚያወግዙት ካስትሮ፣ በኩባ የሶሻሊዝም ንድፈ ሐሳብን የተገበሩ መሪ ነበሩ፡፡ በአቋማቸው በምዕራባውያኑ ብዙም ተቀባይነት ያልነበራቸው ካስትሮ ለ47 ዓመታት በነበራቸው የሥልጣን ቆይታ በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡

እኝህ ዓለም የማይዘነጋቸው አብዮታዊ መሪ የ11 ልጆች አባት የነበሩ ሲሆኑ፣ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...