Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹አካል ጉዳተኞችን በልማት ለማካተት በመንግሥት መዋቅር መሄዱ ሥራዎችን ቀጣይ ያደርጋቸዋል››

አቶ ጌታቸው አበራ፣ የላይት ፎር ዘ ወርልድ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር

ላይት ፎር ዘ ወርልድ የሰባት አገሮች ማለትም የኦስትሪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድስ፣ ጀርመንና ዩናይትድ ኪንግደም ስብስብ ሲሆን፣ ዋና ቢሮው ቬና ኦስትሪያ ይገኛል፡፡ አሜሪካ ደግሞ የላይት ፎር ዘ ወርልድ አባል ለመሆን በሒደት ላይ ትገኛለች፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያና ምሥራቅ አውሮፓ ውስጥ በሚገኙ 15 አገሮች በአካል ጉዳተኝነትና በልማት ላይ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ ከ15ቱ አገሮች ኢትዮጵያ የፕሮግራም ቅድሚያ የተሰጣት አገር ስትሆን፣ ድርጅቱ ከሚሠራባቸው አገሮች ለ2016 ብቻ ከሰባት ሚሊዮን ዩሮ በላይ ዕርዳታ በማግኘት ከቀዳሚዎቹ ትመደባለች፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ፣ በሞዛምቢክ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በቡርኪናፋሶ ቢሮ ከፍቶ የሚሠራ ሲሆን፣ በኡጋንዳ በከፊል ይንቀሳቀሳል፡፡ ከትራኮማ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ዓይነ ስውርነትን በመከላከልና አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ትምህርት ለማዳረስ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራም ይገኛል፡፡ አቶ ጌታቸው አበራ የላይት ፎር ዘ ወርልድ የኢትዮጵያ ቢሮ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር ናቸው፡፡ በድርጅቱ ሥራዎች ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቱ ላይት ፎር ዘ ወርልድ የሚለውን ስም ይዞ ከመምጣቱ በፊት በኦስትሪያ ክሮቶፎር (ክርስቲያን) ብላይንድ ሚሽን (ሲቢኤም) በመባል ይታወቅ ነበር፡፡ በወቅቱ ድርጅቱ ይሠራ ከነበረው የአሁኑ ላይት ፎር ዘ ወርልድ በምን ይለያል?

አቶ ጌታቸው፡- እ.ኤ.አ. በ1984 ሲቢኤም ኦስትሪያ ሲቋቋም የሚሠራው በቀጥታ ሳይሆን የሲቢኤም ዓለም አቀፍ ኔትወርክ አባል ሆኖ ነበር፡፡ በጀርመን ቤንሳይን የሚገኘው ዋና ቢሮ ዕርዳታ አሰባስቦ የዓይን ጤና ላይ ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች እንዲውል ለሲቢኤም ዓለም አቀፍ ቢሮ በማስተላለፍ ይደግፉ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ፕሮጀክቶችን በአካል ተገኝቶ ለመገምገም እንዲሁም ከውጭ ዕርዳታ ለሚያደርጉ ፋውንዴሽኖችም ሆነ ግለሰቦች ወይም ሌሎች ገንዘባችሁ የዋለው እዚህ ነው ብሎ ለማሳየት አይቻልም ነበር፡፡ በመሆኑም ሲቢኤም ኦስትሪያ ባደረገው ጉባኤ ስም ለመቀየርና ራስን ችሎ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ከስምምነት በመደረሱ፣ እ.ኤ.አ. በ2004 ላይ ላይት ፎር ዘ ወርልድ ኦስትሪያ ተብሎ ተቋቋመ፡፡ ስያሜው ላይት ፎር ዘ ወርልድ ቢሆንም፣ የክርስቶፈር ብላይንድ ሚሽንን ፊሎሶፊ በመከተል ሥራው ይከናወናል፡፡ ክርቶፈል የዓይን ሐኪም ሲሆን፣ እንደሚሽነሪም በኢኮኖሚ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች እየተዘዋወረ ዓይነ ስውርነትን ለመከላከል ይሠራ ነበር፡፡ ላይት ፎር ዘ ወርልድም ከ2004 ጀምሮ ኦስትሪያ ቬና ላይ ሆኖ ፕሮጀቶክችን ይረዳ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የዕርዳታው መጠን እያደገ፣ ፕሮጀክቶችም እየበዙ ሲመጡ፣ ከርቀት ከመርዳትና ሥራዎችን ከመከታተል ይልቅ፣ በኢትዮጵያ ቢሮ ቢቋቋም የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል በሚል እ.ኤ.አ. በ2010፣ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቢሮ ከፍቷል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ቢሮውን በኢትዮጵያ ለመክፈት ከማማከር ጀምሮ እስካሁን በድርጀቱ ይሠራሉ፡፡ ምን ዓይነት ፕሮጀክቶችን ይዛችሁ ነው ሥራውን የጀመራችሁት?

አቶ ጌታቸው፡- በወቅቱ የዓይን ጤና፣ የማኅበረሰብ አቀፍ መልሶ ማቋቋም በተለይ አካል ጉዳተኝነትን ቀድሞ መከላከልና አካል ጉዳተኞችን መልሶ ማቋቋምን ጨምሮ ስድስት ያህል ፕሮጀክቶች ነበሩን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ምን ያህል ፕሮጀክቶች አሉ?

አቶ ጌታቸው፡- አሁን ላይ ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆኑ ፕሮግራሞችም አሉን፡፡ 32 ያህል የዓይን ጤና፣ ማኅበረሰብ አቀፍ መልሶ ማቋቋም እንዲሁም የአካቶ ልማት ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኒግሌክትድ ትሮፒካል ዲሲዝ (ኤንቲዲ) ላይ ሙሉ የትግራይ ክልልን እንዲሁም ምዕራብ ኦሮሚያን የሚሸፍን ፕሮግራም አለ፡፡ በዚህ ውስጥ ከጤና ቢሮ ጋር ተፈራርመን የምንሠራቸው ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ኤንቲዲ በ2014 ላይ ነው የተጀመረው፡፡ በ2016 ደግሞ የአካቶ ትምህርት ተጀምሯል፡፡ የአካቶ ትምህርት “One Class for all” ማለትም በአንድ ክፍል ሁሉንም ዓይነት ተማሪዎች ለማስተማር የሚያስችል አሠራር ለማስፈን እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ትምህርት ለሁሉም ልጆች ማዳረስ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አንድ ሕፃን የአካል ጉዳት ካለበት የትምህርት ዕድል ማጣት የለበትም፡፡ በኢትዮጵያ ከአሥር አካል ጉዳተኛ ሕፃናት ዘጠኙ አካላዊ ብቃታቸው ትምህርት ቤት ለመድረስ፣ ከደረሱ በኋላም ግቢው ለመግባትና በግቢው ያሉ መሠረተ ልማቶትን ለመጠቀም ባለመቻላቸው፣ በአካባቢያቸው ላይ ባለ አሉታዊ አመለካከት፣ በመምህሩ የሥልጠና ብቃት፣ በአቅም ማነስና በሌሎች ምክያቶች ከትምሀርት ቤት ይቀራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካል ጉዳት ያለበት ሰው ከ15 እስከ 17 በመቶ ይደርሳል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዋናውን ድርሻ የሚይዙት በመማር ዕድሜ ክልል ያሉ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት በዓለም የአካል ጉዳተኝነትን 15 በመቶ ሲያደርገው፣ በኢትዮጵያ 17 በመቶ እንደሆነ አስፍሯል፡፡ ብዙውም በመማር ዕድሜ ክልል ላይ ያለ ከመሆኑ አንፃር፣ የተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸውን አካቶ ማስተማር ግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ትምህርትን ለሁሉም ለማዳረስ ባላት ፖሊሲ መሠረት፣ አካል ጉዳተኞችን ካላካተትን ፖሊስውንም ሆነ ሁለተኛውን የሚሊኒየም ልማት ግብ ማሳካት አይቻልም፡፡ በመሆኑም አካቶ ትምህርት በአገሪቱ እንዲተገበር ከመንግሥት ጋር በመተባበር የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የአካል ጉዳተኛውን አላካተትንም ማለት ኢኮኖሚውን ከመጉዳት ባለፈ የጉዳተኞቹም ሕይወት ያልተሻለ እንዲሆን መተው ነው፡፡ በአንድ ክፍል ሁሉንም ማስተማር የሚለውን የምንሠራው በአማራ ክልል፣ አዲስ አበባንና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአካቶ ትምህርትን በምን ዓይነት መልኩ ነው የምትተገብሩት?

አቶ ጌታቸው፡- ላይት ፎር ዘ ወርልድ በራሱ ፕሮግራም አይተገብርም፡፡ ለአጋሮቻችን የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጽያ ቢሮ ስላለውም የፕሮጀክትና የፕሮግራም ትግበራን ሞኒተር እናደርጋለን፡፡ የአካቶ ትምህርትን ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር ስንሠራ፣ ያነጣጠርነው ሦስት ክልል ላይ ቢሆንም፣ በተግባር የጀመርነው በአማራና በደቡብ ክልሎች ነው፡፡ ከትምህርት ቢሮዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመን የክልሉን ትምህርት ቢሮ የሚደግፉ ባለሙያዎች ቀጥረናል፡፡ የመምህራን ሥልጠናንም እንደግፋለን፡፡ ከመምህራን ማሠልጠኛ ተቋማት ጋር ውል ተፈራርመን የሥርዓተ ትምህርት ክለሳ እየተሠራ ነው፡፡ ምክንያቱም አካቶ ትምህርት ልዩ ክህሎት ይፈልጋል፡፡ በምልክት፣ በብሬልና በሌሎችም አጠቃላይ ግንዛቤው እንዲኖር በኮሌጅ ደረጃ የመምህራን ሥልጠና አካል ሆኖ እንዲሰጥ ሥርዓተ ትምህርቱን በጋራ ለማሻሻል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተደርጓል፡፡ የዚህ ፕሮግራም ባለቤትም ትምህርት ሚኒስቴር በመሆኑ እኛ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የመምህራን ሥልጠናው የተጀመረ ሲሆን፣ ይህንን ቀጣይ ለማድረግ ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ወደፊት የምንሄድበት ነው፡፡ ከትምህርት ቤቶች ጋር በትምህርት ቢሮ አማካይነት ለመምህሩ የትምህርት ሥርዓቱ ሳይስተጓጎል የሥራ ላይ ሥልጠና መስጠትም የድጋፋችን አካል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመምህሩና በሥርዓተ ትምህርቱ በኩል ያሉ ክፍተቶችን በሥልጠናና በሙያ ስታግዙ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው ልጆችን የሚያስተናግድ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማቶች እንዲኖሩ የምታደርጉት እገዛ ምን ይመስላል?

አቶ ጌታቸው፡- የአካል ጉዳተኞች ትምህርት ክፍል፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቢሮዎች፣ መፀዳጃ ቤት መግባት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መረማመጃዎች መገንባት አለባቸው፡፡ የአካል ጉዳተኞችን የሚያካትቱ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት ጅምር ያለባቸው ሥፍራዎች ላይ እያገዝን ነው፡፡ አጠቃላይ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግም በሚሠሩ ሥራዎች ላይ እናግዛለን፡፡ የትምህርትና የሥልጠና መርጃ መሣሪያዎች ማቅረብና የመሳሰሉትን በማስፋፋት በአጠቃላይ አካቶውን ለማጎልበት በተለይ መንግሥታዊ ተቋማትን እያገዝን ነው፡፡ በዚህ የአካል ጉዳት ያለበት ልጅ ትምህርት ቤት እንዲገባ እየሠራን ነው፡፡ የዓይን፣ የመስማት፣ የመናገር፣ የመስማትና መናገር፣ የመራመድ ችግር ያለባቸውን፤ ሙሉ አካል አላቸው ከሚባሉት ጋር አካቶ ለማስተማር የመምህሩ ክህሎት ላይ ያተኮረ ሥልጠናንም እንደግፋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሙሉ አካል ያላቸውንና ሁሉንም ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸውን አብሮ ለማስተማር የማስተማር ዘዴው ይለያያል፡፡ እዚህ ላይ ለመምህሩ የሚሰጠው ሥልጠና እንዴት ነው?

አቶ ጌታቸው፡- አንድ መምህር በክፍል ውስጥ የተለያየ ፍላጎትን ማስተናገድ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ አሁን ላይ ያለው ልምድ የአካል ጉዳት ያለባቸው ተማሪዎች አራተኛ ክፍል እስከሚደርሱ  የተለየ ክፍል ተዘጋጅቶላቸው ማስተማር ነው፡፡ አምስተኛ ሲደርሱ ከሌሎች ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ እስካሁን የአካል ጉዳት ያለባቸው ላለው የትምህርት አሠራር ነበር ራሳቸውን ሲያዘጋጁ የነበሩት፡፡ የአካቶ ምልከታ ደግሞ አሠራሩ አካል ጉዳተኞችን ያካት የሚል ነው፡፡ ይህ የትምህርት ሚኒስቴር ፖሊሲም ነው፡፡ ፈታኝ ሊሆን ይችላል ብለንም አንፈራም፡፡ ደቡብ ላይ የአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል አለ፡፡ ቀድሞ በአገር ውስጥ ግብረሰናይ ድርጅት ይመራ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን የክልሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መደበኛ በጀት መድቦለት እየሠራ ነው፡፡ ላይት ፎር ዘ ወርልድም ገንዘብ እየረዳን ከመንግሥት ጋር እየተባበረ ጋሞጎፋ ዞንና ወላይታ ሶዶ ዞን ላይ በስፋት እየሠራ ነው፡፡ እዚህ ያለው ፕሮጀክት የአካቶ ፅንሰ ሐሳብ ስላለው፣ ሁሉም ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚማሩበት ላይ እየተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁሉም ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸውን ከሌለባቸው ጋር በአንድ ላይ በማስተማሩ ለውጥ እያያችሁ ነው? የምትሰጡት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ከመሆኑ አንፃርስ መሬት ላይ የተሠራውን እንዴት ትገመግሙታላችሁ?

አቶ ጌታቸው፡- ለውጦች አሉ፡፡ ድጋፉን በተመለከተ ፕሮግራሞቹ ስለሰፉ ብዙ ባለሙያዎች አሉን፡፡ ፕሮጀክት መተግበሩን በየጊዜው እንከታተላለን፡፡ ታች ወርደንም ተጠቃሚውን ጭምር እናነጋግራለን፡፡ ከቀበሌ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ላይ ደርሰን እናያለን፣ እንገመግማለን፡፡ ከእኛ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በየሦስት ዓመቱ ሲታደስ የውጭ ገምጋሚዎች የፕሮጀክቱን ተፈጻሚነት ያያሉ፡፡ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቢሮ የከፈተውም ሥራውን ለመከታተል ነው፡፡ ከጡረታቸው የሚለግሱ ግለሰቦችን ጨምሮ ትላልቅ ተቋማት ድርጅቱን በገንዘብ ስለሚደግፉ ለእነሱ የደረስንበትን ማሳወቅ ግድ ነው፡፡ ከተለያየ ቦታ ተለምኖ የሚመጣው ገንዘብ ለተጠቃሚው መዋሉን ማረጋገጥ አለብን፡፡ በሥራችን ዙሪያ ዋና አጋሮቻችን የመንግሥት ተቋማት ናቸው፡፡ በአካቶ ትምህርቱም ሆነ በጤናው ከመንግሥት ተቋማት ጋር በብዛት እንሠራለን፡፡ የሥራውን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በመንግሥት መዋቅር ከተሄደ፣ መንግሥት ቀስ በቀስ ወደ ፕሮግራሙ አስገብቶትና መደበኛ በጀት መድቦለት ያስቀጥለዋል፡፡ ምክንያቱም የእኛ ድርጅት በፈንድ የሚንቀሳቀስ ስለሆነ፣ ይህ ሲታጣ ፕሮግራሙ ይቋረጣል፡፡ በያዝነው የገንዘብ አቅም ከመንግሥት ጋር በመጣመር ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከአካቶ ትምህርት ድጋፍ በተጨማሪ የዓይን ጤና ላይ ትሠራላችሁ፡፡ የዓይን ጤና እክል በተለይ ከትራኮማ ጋር የተያያዘ ዓይነ ስውርነትን እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ጌታቸው፡- የዓይን ሕመም ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ በቀደሙት ዓመታት ያለው የዓይን ሐኪምም በጣት የሚቆጠር ነበር፡፡ በዘርፉ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ አጋሮችም ኦርቢስና ሲቢኤም ብቻ ነበሩ፡፡ ስለዚህም ችግሩን ለመቅረፍ ድጋፍ ያስፈልግ ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለው የዓይን ሐኪም ከቀድሞ ሲነፃፀር እየጨመረ ነው፡፡ ሆኖም በቂ ስላልሆነ እኛ የሰው ኃይሉን መገንባት አለብን ብለን እየሠራን ነው፡፡ የግሎባል ትራኮማ ማፒንግ ፕሮጀክት ወይም ሰርቬይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2013 ሲሠራ፣ ኢትዮጵያ (ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር) በተሳካ መልኩ ሰርቬይ አስረክባለች፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲዞር ዕድል ፈጥሯል፡፡ እኛም ዕድሉን ተጠቅመን ትግራይ ክልል ሙሉ ለሙሉና በምዕራብ ኦሮሚያ በትራኮማ የሚከሰት ዓይነ ስውርነትን ለማጥፋት እያገዝን ነው፡፡ ዝሆኔ በሽታን ለማጥፋት የሚሠራውን ሥራም እንደግፋለን፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት እየሰጠ በመምጣቱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም እየተባበሩ ነው፡፡ ላይት ፎር ዘ ወርልድ በኦሮሚያ ትራኮማን ለመከላከል የመድኃኒት ስርጭት ላይ ሲሠራ፣ በክልሉ ችግሩን ለመቅረፍ እንዲተባበር ሥራው የተሰጠው ፍሬድ ሆሎውስ ፋውንዴሽን ድርጅት ቀሪዎቹን ያከናውናል፡፡ የእኛ ድርጅት መድኃኒቱን ሲደግፍ፣ ሥልጠናውን፣ ቀዶ ሕክምናውንና ሌሎች ድጋፎችን ፍሬድ ሆሎውስ ይዞታል፡፡ በዚህም ድርጅቱ ከእኛ ጋር በመተባበር በሌላው ክልል የሚሰጠውን ሙሉ ፓኬጅ በኦሮሚያም ይተገበራል፡፡ የተለያዩ ድርጅቶች ፕሮግራሞች እንዳይደራረቡም  ድርጅቶች ተናበው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፡፡ ይህም አቅምን አቀናብሮና ተባብሮ ችግርን ለመፍታት ያስችላል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...