Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሥራ ያጣው ሥራ ተቋራጭ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በደረጃ አንድ ተቋራጭነት ከሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች መካከል  በተለይ በሕንፃ ግንባታዎች መስክ በአብዛኛው ከሚጠቀሱት ውስጥ አንዱ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ታኮን) ነው፡፡ ከ1,700 በላይ ሠራተኞችን ሲያስተዳድር የቆየው ታኮን፣ አሁን ላይ በግዙፍነቱ የሚጠቀሰውን ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በትግራይ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ስታዲየም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታና መገናኛ አካባቢ የተገነቡትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንጻዎች፣ የዳኞች መኖሪያ ቤት (አራት ባለ ጂ+18 ሕንፃዎች) ጨምሮ በመቀሌ፣ በጂማ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍም ይጠቀሳል፡፡ የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የማሪታይም ሕንፃ ማጠቃለያ፣ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሕንፃ ግንባታዎችን አጠናቆ ማስረከቡም ሳይወሳ አይታለፍም፡፡ 650 መጋዘኖችና ሱቆች ያሉትን ትልቅ የገበያ ማዕከል ጨምሮ ከአፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሕንፃዎች አንዱን ገንብቶ ሲያጠናቅቅ፣ ሁለተኛውን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ከጤና ኬላዎች እስከ ትልልቅ ግንባታዎች ላይ ተሳታፊ የሆነው ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት የ18 ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራዎች በእጁ ቢኖሩም አብዛኛዎቹን ወደማጠናቀቁ መቃረቡን አስታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭም በሶማሊያ የበርበራ ተርሚናል ግንባታ ላይ ተሳትፏል፡፡ ሰሞኑን ግን ከታኮንና ከሌሎች እህት ኩባንያዎችን ከሚያስተዳድረው ታፍ ኮርፖሬት ሥር ከሚገኙ ኩባንያዎች 442 ሠራተኞችን ቀንሷል፡፡ ኩባንያው አትራፊና ውጤታማነቱ እየጎላ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ለምን ቅነውን አደረገ? የሚለው ጥያቄ ቀድሞ ያቃጭላል፡፡ ታኮንን ጨምሮ ከሰባት ያላነሱ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው ታፍ ኮርፖሬት እንዳስታወቀው ከሆነ ለሠራተኞቹ መቀነስ ምክንያታዊና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ቅዳሜ፣ ኅዳር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሠራተኞቹ በተዘጋጀ የስንብት ፕሮግራም ወቅትም ይኸው ተንፀባርቋል፡፡ በሠራተኞች ቅነሳና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ የታፍ ኮርፖሬች ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን አቶ ሰይፉ አምባዬን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ጀምሮ በታፍ ኮርፖሬት ሥር በሚተዳደሩ ኩባንያዎቻችሁ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች ቅነሳ አድርጋችኋል፡፡ ይህንን ማድረግ ለምን አስፈለገ? የተቀነሱትስ ምን ያህል ናቸው?

አቶ ሰይፉ፡- ከታኮን 324፣ ከይበል ኢንዱስትሪ 102፣ ከታፍ ኮርፖሬት ዋና መሥሪያ ቤት ደግሞ 16 ያህል ሠራተኞችን ቀንሰናል፡፡ ከሦስቱ ድርጅቶች በአጠቃላይ የተቀነሱት 442 ሠራተኞች ናቸው፡፡ ሠራተኞቹን ለመቀነስ የተገደድንባቸው ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ፡፡ አንዱ በእጃችን ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ወደ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ የገቡ በመሆናቸው ነው፡፡ የግንባታ ፕሮጀክቶች ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ ሲደርሱ በርካታ ቁጥር ያለው ትርፍ ሠራተኛ ይኖርሃል ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ የደረሱ ፕሮጀክቶችን ለማስቀጠል በመቸገራችን ነው፡፡ ይህም ማለት ለማጠናቀቂያ ሥራው የሚሆኑ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልገንን የውጭ ምንዛሪ ባለማግኘታችን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከዛሬ ነገ እናገኛለን በሚል ተስፋ ከስድስት እስከ ስምንት ወራቶች ይህን ያህል ቁጥር ያለው ሠራተኛ ይዘን ስነጠብቅ ቆይተናል፡፡ ይህንን ተሸክሞ መቀጠል ከባድ እየሆነ መጥቷል፡፡ የውጭ ምንዛሪው ከዛሬ ነገ ይፈቀዳል ይባላል ግን ሊፈቀድልን አልቻለም፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የምንጠቅሰውና ለሠራተኞች መቀነስ ምክንያት የሆነን ትርፍ ቁጥር ያላቸውን ሠራተኞች ይዘን ለመቀጠል የሚያችሉን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ማግኘት አለመቻላችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ታኮን እንደ ቀድሞው አዳዲስ ፕሮጀክቶች ማግኘት ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ሰይፉ፡- ለዚህ ምክንያቱ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዱ መንግሥት የሚያወጣቸው ጨረታዎች ጋር የሚያያዝ ሊሆንም ይችላል፡፡ ብዙውን ጊዜ ጨረታዎች የሚወጡት በዓመቱ አጋማሽ ወቅት ጥር ወይም ታኅሳስ ላይ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አዲስ ሥራ ብናገኝ የቀነስናቸውን ሠራተኞች ልንመልሳቸው እንችላለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ሠራተኞች ተሸክመን መሄድ አስቸጋሪ እየሆነብን መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኮርፖሬቱ ዋነኛ ገቢ ታኮን ነው፡፡ በመሆኑም እሱ ሥራ አላገኘም ማለት ነገሩን ሁሉ አስቸጋሪ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡ የታኮን ሥራ አለማግኘት በኮርፖሬሽኑም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ምክንያቱም ዋናው ገቢ ከኮንስትራክሽን ዘርፉ (ከታኮን) የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡ በኮርፖሬቱ ሥር ያለው ሌላው ተቋም ይበል ኢንዱስትሪያል የተባለው ድርጅታችን ሲሆን፣ በኮርፖሬቱ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ የገቢ ምንጭ ኩባንያ ነው፡፡ ነገር ግን በጣም በርካታ ሥራዎች በእጁ ይዞ የነበረው ይኸው ይበል ኢንዱስትሪም በተመሳሳይ መንገድ በእጁ የነበሩ ሥራዎችን በአብዛኛው አጠናቆ አስረክቧል፡፡ ይበል ኢንዱስትሪያል በጣም የተቸገረበት ሌላው ነገር ማግኒዚየም ኦክሳይድ ያቀርብለት የነበረ አንድ ተቋም ሥራ ማቆሙ ነው፡፡ ይበል ኢንዱስትሪ ማግኒዥየም ቦርድ ለማምረት የሚጠቀምበት ጥሬ ዕቃ የሚያቀርበው ይህ ኩባንያ በመሆኑ እኛ በማናውቀው ምክንያት ሥራ ማቆሙ ለይበል ሥራ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የማግኒዢየም ግብዓት ከሌለ ደግሞ ማግኒዥየም ቦርዱንም ሆነ ሌሎች ምርቶችን ማምረት ስለማይቻል ከይበል ኢንዱስትሪያልም ሠራተኞችን ለመቀነስ ተገደናል፡፡ ወደዚህ ዕርምጃ ከመግባታችን በፊት ለበርካታ ወራት ሥራ እናገኛለን ብለን በተስፋ በመጠባበቅ ሥራ ያልነበራቸውን ሠራተኞች ሳንቀንስ ቆይተናል፡፡ ምናልባት ካለን የሥራ አኳያ መጠን አኳያ እነዚህን ሠራተኞች ከስድስት ወይም ከሰባት ወራት በፊት መቀነስ ነበረብን፡፡ ነገር ግን ከዛሬ ነገ ሥራ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ ስለነበረን እንዲቆዩ አድርገናል፡፡ ሠራተኞች እንዳይቀነሱ የነበረን ፍላጎት ብርቱ ነበር፡፡ ሠራተኞቹ ብዙ ሥልጠና ያገኙና ያበቃናቸው፣ በዓመት ብዙ ሥልጠና የወሰዱና በብዙ የሥራ ግምገማ ሒደቶች ውስጥ ያለፉ፣ በየጊዜው ተገምግመውም ብቃታቸው የተመሰረከላቸው አሉ የተባሉ ሠራተኞች ናቸው፡፡ በዚህ ደረጃ ብቃት የነበራቸው ሠራተኞች በመሆናቸው ላለመልቀቅ ስንንገታገት ቆይተናል፡፡ በመጨረሻ ግን በእንዲህ ያለ አካሄድ መጓዙ አስቸጋሪ ሆነብን፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሠራተኞች ለጊዜው እንቀንስና ሥራ ማግኘታችን ስለማይቀር ቅድሚያ እንደምነሰጣቸው በማሰብ ጭምር የወሰድነው ዕርምጃ ነው፡፡ ሥራ ስናገኝ እነሱን እንመልሳለን ያልነውም በምንፈልገው ደረጃ ሥለሰለጠኑ ነው፡፡ ከድርጅታችን ጋር ብዙ  ሠርተዋል፡፡ ለሥራውም ለድርጅቱም ፍቅር አላቸው፡፡ ይህንን እናውቃለን፡፡ ስንብቱ በይፋ ከተገለጸ በኋላ ከሠራተኞች ያገኘነው ምላሽም ይህንኑ ነው፡፡ ሥራ መልቀቅ ጥሩ ስሜት ባይፈጥርም በመተማመንና በመግባባት የተፈጸመ ነው፡፡ ይህንን ቃል ገብተን ነው የምንሸኛቸው፡፡ ሌላው ሕጉ በሚፈቅደውና እነሱ ደስ በሚላቸው መንገድ ትክክለኛ ሕጉን ተረድተው ነው እንዲቀነሱ ያደረግነው፡፡ አብዛኛው ሠራተኛ የተቀነሰው ከኮንስትራክሽን ኩባንያው ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ሥራ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ልታሰናብት ትችላለህ የሚል ሕግ አለ፡፡ እኛ ግን በዚያ መልኩ አልሄድንም፡፡ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት፣ ግን ደግሞ በማያሻማ መንገድ፣ ሠራተኛውንም በማይጐዳ ሁኔታ ነው የምንቀንሳቸው፡፡ ስናሰናብታቸው የአራት ወር ደመወዝና የአገልግሎታቸውን ክፍያ ጨምረን ነው የምንሸኛቸው፡፡     

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የአራት ወር ደመወዝ ከፍላችሁ በተጨማሪም የአገልግሎት ዘመን ክፍያ አክላችሁ መሸኘታችሁ ግድ ከሆነ አዲስ ሥራ እስኪገኝ ድረስ ቢያንስ ለአራት ወራት ከሥራ ገበታቸው ሳይለቁ ማቆየት አይቻልም ነበር? ምክንያቱም የአራት ወር ደመወዝ ከፍላችኋል፡፡

አቶ ሰይፉ፡- አራት ወር አቆየናቸው ማለት እኮ ለእነሱ አገልግሎት ማቅረብ አለብን ማለት ነው፡፡  እነሱን ማኔጅ ማድረግ አለብህ፡፡ እነሱ ያለሥራ መቀመጣቸው ሥራ እየሠራ ባለው ሠራተኛ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ የብቃት ችግር ነው የሚጨምረው፡፡ ስለዚህ ለእነሱ የአራት ወርና የአገልግሎት ክፍያ ጨምረህ ሸኝተህ ያለውን ሠራተኛ ውጤታማ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነው ያሰናብታናቸው፡፡ ሥራ ሲገኝ ደግሞ የሄዱትን መመለስ ይቻላል፡፡ እናቆያቸው ቢባል እንኳ ለእነሱ የሚሆን ሥራ እኮ የለም፡፡ ያደረግነው የቅነሳ ሒደት ግን ቀሪውንም ሆነ የተቀነሰውን ሠራተኛ ስሜት በማይነካ መልኩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደዚህ ዕርምጃ ከመግባታቸው በፊት ስለሁኔታው ከሠራተኞች ጋር መክራችኋል? ለምሳሌ ቅነሳው በትክክል እርስዎ እንዳሉት ከፕሮጀክት መጠናቀቅና አዳዲስ ሥራ ከመጥፋት ጋር መሆኑን ነግራችኋል? ቅሬታ አልፈጠረም ትላላችሁ?

አቶ ሰይፉ፡- ከሠራተኛው በሚገባ ጋር ተመክሮበታል፡፡ በያንዳንዱ ሳይት ላይ በዚሁ ጉዳይ ውይይቶች አድርገናል፡፡ ለምሳሌ ያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ድረስ በመሄድ ስለሁኔታው አስረድተናል፡፡ የየኩባንያዎቹ የሥራ ኃላፊዎች ሠራተኞቹን በጋራ አወያይተዋል፡፡ በግል እየጠሩም ጭምር በማነጋገር ስላለው ሁኔታ በማነጋገር በሁኔታው ላይ ተማምነዋል፡፡ ሠራተኞቹ በምላሹ የሰጡት አስተያየትም የሚያስደስት ነው፡፡ አስተያየታቸውም በመግባባት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ለስንብት በተዘጋጀው የምሳ ፕሮግራም ወቅት ሠራተኞቹ በፍቅር ነው የተሸኙት፡፡ ስለዚህ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተሟላ መግባባት የተሠራ ሥራ ነው፡፡ እንዲያውም ወደ ዕርምጃው ከመግባታችን በፊት ከማኔጅመንቱ ጋር ተማምነን ነው፡፡ የተቀነሱት ሠራተኞች ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መሆኑን መግለጻቸው ብቻ ሳይሆን አምነውበትም ነው፡፡ በአጠቃላይ ስናየው ከየኩባንያዎቻችን የሚቀርበው አቤቱታ ከአቅማችን በላይ ሠራተኞች ተሸክመናል ምን እናድርግ የሚሉ ነበሩ፡፡ በዚህ መሠረት መቀነስ አለበት የምትሏቸውብ የሠራተኞች ብዛት አቅርቡና በሕጉ መሠረት ፈጽሙ ነበር ያልነው፡፡ በቅነሳው ዙሪያ አስተዳደሮቻችን እንዳይሳሳቱ አራት የሕግ ባለሙያዎችን በመያዝ በጉዳዩ ላይ ሦስት ወይም አራት ጊዜ ውይይት አድርገናል፡፡ ስለዚህ በሁሉም አቅጣጫ የሕግ ባለሙያዎቹ ያላቸውን ሐሳብ አቅርበው ሐሳቡን ወደ አንድ በማምጣት በዚያ መልኩ ነው ወደ ዕርምጃው የሄድነው፡፡ ሌላ ምንም ችግር የለም፡፡ ሌላው ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የቆመ ነገር የለም፡፡  

ሪፖርተር፡- ኩባንያችሁ የዚህን ያህል ሠራተኛ ሲቀንስ አብሮ የሚታየው የገቢው መቀነስ ጋር አይያያዝም? የሠራተኛ ቅነሳ ሲባል የድርጅቱ እንቅስቃሴ መቀነሱንም ያመለክታልና፡፡

አቶ ሰይፉ፡- በፍፁም የድርጅቱ ገቢ በመቀነሱ አይደለም፡፡ ድርጅቱ የተሻለ ገቢ አለው፡፡ ካለፈው ዓመትም የበለጠ ገቢ እያገኘ ነው፡፡ ጥያቄው በምንም መልኩ ከዚህ ጋር አይገናኝም፡፡ ዘንድሮ ግን እንሠራዋለን ያልነውን ሥራ ለመሥራት የሚያስችል የሰው ኃይልና ማሽነሪ ነበረን፡፡ አዳዲስ ሥራዎች ስላላገኘን በእጃችን ካሉትም ወደ 18 ፕሮጀክቶች ውስጥ ወደ ሦስት አራተኛው ማጠናቀቁ ላይ ደረስን፡፡ ሥራዎቹ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ በኋላ አብዛኛው ሥራ የሚሠራው በሰብ ኮንትራት ነው፡፡ የእኛ ሰው ሥራ እነዚህን ሰብ ኮንትራክተሮች ማስተባበርና መቆጣጠር ነው፡፡ እኛ ፍሬሙን ከጨረስን፣ ኮንክሪቱን ካጠናቀቅን በኋላ የእኛ ሰው የሚሠራው ሌላ ሥራ አይኖረውም፡፡ ከዚህ ወዲያ ያለው በሰብ ኮንትራክተር የሚሠራ ነው፡፡ የአሉሚኒየም፣ የወለል፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ፣ የሳኒተሪና የመሳሰሉት በሰብ ኮንትራክተሮች የሚሠሩ ሥራዎች በመሆናቸውና እነዚህ ሥራዎችም በፕሮጀክቶቻችን መጠናቀቂያ ላይ በመድረሳቸው ምክንያት ሥራ የፈታውን ሠራተኛ አዲስ ሥራ ካገኘህ ወደዚያ ማዛወር አለብህ፡፡ ካልሆነ ግን ትቀንሳለህ፡፡  

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ ፕሮጀክቶቻችሁ ሦስት አራተኛው የማጠናቀቂያ ሥራዎች ላይ ከደረሱ፣ እርስዎ እንዳሉትም ተጨማሪ አዲስ ሥራ ከሌለ ቀጣዩ ጉዞዋችሁ ምን ሊሆን ነው? በዘርፉስ አሸንፈን ልንረከበው እንችላለን ብላችሁ የምትጠብቁት ሥራ አለ?

አቶ ሰይፉ፡- ለሠራተኞች ቅነሳ ምክንያት የሆነው አንዱ ጉዳይ ጨረታዎችን ለማሸነፍ እየተቸገርን መሆናችን ነው፡፡ ጨረታዎችም በብዛት አልወጡም፡፡ ከውጭ ኮንትራክተሮች ጋር ያለው ፉክክርም በጣም በርትቷል፡፡ ስለዚህ አብዛኛውን ሥራ የውጭ ኮንትራክተሮች እየወሰዱት ስለሆነ ይህ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ይህንን ችግር ከመንግሥት ጋር በመነጋገር መፍታት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትም ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የሚደግፉ ሕጎች እያወጣ ነው፡፡ ይህ ተስፋ ሰጪና መልካም ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን የሚደግፉ ሕጎችን እያወጡ ነው ሲሉ ለምሳሌ የትኛው ሊጠቀስ ይችላል?

አቶ ሰይፉ፡- ለምሳሌ በኤሌክትሪክ ኃይል ዙሪያ በሚወጡ ጨረታዎች ወቅት የውጭ ኮንትራክተሮች ሲጫረቱ፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች 40 በመቶ የእሽሙር ወይም የጆነት ቬንቸር አጋርነት መፍጠር አለባቸው የሚል አንቀጽ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ሕጎች ካሉ በሁለት መንገድ ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡ አንዱ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሥራ እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ በጆይንት ቬንቸር መሥራታችን ደግሞ ለዕውቀት ሽግግር ይጠቅመናል፡፡ አሁን ግን ሥራ የማግኘት ከፍተኛ ችግር አለ፡፡ በጨረታው ሥርዓት ውስጥ እንዲህ ያሉ ሕጎች መኖራቸው መልካም ነው፡፡ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ደግሞ እኛው ራሳችን መዘጋጀት ስለሚኖርብን ነው፡፡ በምን መልኩ ነው ሥራ ማግኘት ያለብን? ለሥራችን የምንጠይቀው ዋጋ ከፍ ብሎ ከሆነም ሁኔታውን ማየት ወይም የአቅም ችግር ከሆነም ራሳችንን ማደርጀትና ማብቃት ይጠበቅብናል፡፡ ተወዳዳሪ ለመሆን በሁሉም ረገድ ራሳችንን ማብቃት አለብን፡፡ በሁለቱም ወገን መንግሥት የሚሠራውን ሥራ አጠናክሮ ከቀጠለና በእኛ በኩል ያለውን ክፍተትም ከሞላን አሁን ያሉትን ችግሮች ለዘለቄታው መፍታት እንችላለን፡፡ ይህ መሆን ከሆነ ችግሮቻችን ጊዜያዊ ይመስሉኛል፡፡ እኛም እያየን ያለነው ነገር ስላለ በእኛ በኩል እየተዘጋጀን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ታኮን) በብዛት የሚታወቀው በሕንፃ ግንባታ ነው፡፡ ወደ መንገድ ሥራ የመግባት ዕቅድ የለውም?

አቶ ሰይፉ፡- መንገድ ሥራ ላይ ገብተናል፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መሥራት ጀምረናል፡፡ በጣም የምንታወቅበት ባይሆንም መንገድ ላይ ሠርተናል፡፡ እርግጥ የሠራናቸው ትንንሽ ናቸው፡፡ አሁን ግን ጨረታ ውስጥ ገብተን ትንንሽ ቢሆኑም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ልናሸንፍባቸው እንችላለን ብለን የምናስባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ሆኖም በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ከመሳተፍ የሚገድበን ነገር አለ፡፡ እኛ ብዙውን ጊዜ በሕንፃ ግንባታ ላይ ስለሆነ ያሳለፍነው ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ እንደ ቅድመ ሁኔታ እየቀረቡ ያሉት እንደ ተርን ኦቨር ያሉትን መጠይቆችን ለማሟላት እንቸገራለን፡፡ ይህንን ችግር መንግሥት ያጤነው ይመስለኛል፡፡ ለማስተካከልም የተጀመሩ ነገሮች አሉ፡፡ ለእኛ ብቻ ሳይሆን በርካታ የአገር በቀል ኮንትራክተሮች መንገድ ሥራ ላይ ያላቸው ተርን ኦቨር ትንሽ ስለሆነ ይህ እንዲታይልን ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበናል፡፡ እንደምንሰማው ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ሆነ ከግዥ ኤጀንሲ አወንታዊ ነገር መኖሩን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለመጫረት የሚጠየቀው ተርን ኦቨር የአገር በቀል ኮንትራክተሮችን አቅም ያገናዘበ እንዲሆን አንዳንድ መሻሻሎች ይደረጋሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ ይህ ከሆነ ትልልቅ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እንገባለን፡፡ አሁን ትልቅ ችግር እየሆነ ያስቸገረን የሚጠየቀውን መስፈርት የሚያሟሉ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ጥቂት መሆናቸው ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኛውን የመንገድ ግንባታ ሥራ የሚወስደው የውጭ ኮንትራክተር ሆኗል፡፡ አንድ ጊዜ ወደ ስምንት ፕሮጀክቶች ጨረታ ወጥተው ሁሉንም የውጭ ከንትራክተሮች ወስደዋቸዋል፡፡ ይህ አሳሳቢ ነው፡፡ እንዲህ መቀጠል አለበት ብለን አናምንም፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ እንደሚባለው የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የጨረታ መስፈርት ጠንካራ በመሆኑ ሊያሟሉ የሚችሉት ዓይነት መስፈርት ይቀረጻል ሲባል ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ በተመለከተ በማኅበራችሁ በኩል ያደረጋችሁት እንቅስቃሴ አለ?

አቶ ሰይፉ፡- እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን በማኅበራችን በኩል ነው እያቀርብን ያለነው፡፡ መስፈርቱን በሚመለከት ማኅበሩ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጉዳዩን አቅርቧል፡፡ ባለሥልጣኑም ለግዥ ኤጀንሲ ጉዳዩን አቅርቧል፡፡ በተወሰነ ደረጃ የተሻሻለ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኋላ የሚኖሩ ጨረታዎች እንደ ቀድሞው ለአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ላይከብዱ ይችላሉ የሚል ተስፋ ይዘናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለአገር ውስጥ ኮንትራክተር ችግር ከነበረው ውስጥ የትኛው መስፈርት ላይ ነው ማሻሻያ ይደረጋል ብላችሁ የምትጠብቁት?

አቶ ሰይፉ፡- በመንገድ ላይ ለመጫረት አቅርቡ የምንባለው ተርን ኦቨር መጠንና ልምድ  ላይ የሚጠየቀው ነው፡፡ አቅርቡ የሚባለው ተርን ኦቨር መጠን ከቀነሰ የሚጠየቀውም ልምድ ከተሻሻለ ብዙውን መስፈርት የሚያሟላ ኮንትራክተር ይኖራል፡፡ ችግሩ የሚነሳው በኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ የቆየው አብዛኛው ተቋራጭ በመንገድ ሥራ ላይ ሳይሆን በሌላ ግንባታ መስክ ስለሆነ ለመንገድ የሚጠየቀውን መሥፈርት ሳናሟላ ይቀራል፡፡

ሪፖርተር፡- ትልልቅ ግንባታዎችን ለማካሄድ ጨረታ የሚያወጡ ኩባንያዎች አገር በቀል ኮንትራክተሮች ሊያሟሉ የማይችሏቸውን መሥፈርቶች ሆነ ብለው እያካተቱ የጨረታ ሠነድ ያዘጋጃሉ ይባላል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሊሠሯቸው የሚችሉ ሥራዎች ሆነው ሳለ የሚጠየቁት መሥፈርት ግን እነሱን የማያሳትፍ እየሆነ ነው ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንዲስተካከል ኮንትራክተሮች ይጠይቃሉ፡፡ ማኅበራችሁስ በዚህ ረገድ የሠራው ሥራ አለ? እርስ በርስ ትመካከራላችሁ?

አቶ ሰይፉ፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በማኅበር ተደራጅተን ወደ የመሥሪያ ቤቱ ሄደናል፡፡ አማካሪ ቀጥረን የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ይመስላል የሚለውን ሁሉ አስጠንተናል፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድ ምን እንደሚመስል አይተናል፡፡ ከዚህ አንፃር በመንግሥት አካላት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ሠርተናል፡፡ የግል ዘርፉም የራሱ ድርሻ አለው፡፡ መንግሥት የመሪነት ሚናውን ከተጫወተ የምንጠብቀው ነገር ይኖራል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ገበያውን የሚገዛው ውድድር ነው፡፡ የግል ዘርፉ ተዋናዮች በዚያ መልኩ መሄድ መብታቸው ቢሆንም፣ እዚህ አገር ያልተሠራ ነገር፣ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ሠርቶት የማያውቀውን ሥራ እንደ መሥፈርት እየቀረቡ ነው፡፡ ያልተሠራ ሥራ መሥራት አለባችሁ ተብሎ መስፈረት መውጣት የለበትም፡፡ በሌላ መልኩ መካካስ ነበረበት፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለአገር ውስጥ ኮንትራክተር አደገኛ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ባሉ መሥፈርቶች የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሥራ እንዳያገኙ ማድረግ ኮንትራክተሩን ብቻ የሚጎዳ አድርገን መውሰድ የለብንም፡፡ ነገሩን እንደ አገር ካየኸው የኮንትራክተሩ ጉዳት ትንሽ ነው፡፡ ለውጭ ኮንትራክተር የሚሰጡ ሥራዎች እየበዙ በመጡ ቁጥር በኮንስትራክሽን ዙሪያ ያሉ አገር በቀል ኩባንያዎችን በጠቅላላ ይጐዳል፡፡ ምክንያቱም አንድ ፕሮጀክት በውጭ ኮንትራክተር ተሠራ ማለት ሥራውን የተረከበው የውጭ ኩባንያ የትኛውንም የግንባታ ግብዓት ከውጭ ኩባንያ በመግዛት በብዛት ውደ አገር ውስጥ ያስገባል፡፡ የሰብ ኮንትራክት ሥራዎችንም የሚሰጠው ለውጭ ኮንትራክተር እንዲሆን ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ሠራተኛውንም ከውጭ ያስመጣል፡፡ ባለሙያውም ከውጭ ያመጣል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ነገሮች አገር በቀል የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅራቢዎች ላይም ተፅዕኖ ስለሚያሳርፉ በመጨረሻው የሚጎዳው የአገሪቷ ሕዝብና በዚያ  የሥራ መስክ የተሠማሩትን ባለድርሻዎች ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ይሳተፍ ሲባል ለራሱ አስቦ ብቻ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ጉዳዩን እንደ አገር ጉዳይ ማየት አለብን፡፡ በውጭ ኮንትራክተሮች የሚሠሩ ፕሮጀክቶች የሚፈልጉትን ነገር ከውጭ እንዲመጣ ያደርጋሉ እንጂ እዚሁ ባለ ነገር ላይ እሴት ጨምረው አይሠሩም፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተር ሥራውን ቢያገኝ ግን የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን አሠማርቶ ነው የሚሠራው፡፡ ስለዚህ ይህ ሁኔታ ሊያሳስበን ይገባል፡፡    

ሪፖርተር፡- ታኮን ኩባንያ እንደ አዲስ ራሱን ለማደራጀት በማሰብ አዲስ መዋቅር መዘርጋቱን አስታውቆ ነበር፡፡ በዚህ አሠራር ለውጥ አመጣ?

አቶ ሰይፉ፡- ውጤቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ታኮን በአማካይ በዓመት 106 ከመቶ እያደገ ነው፡፡ የለውጥ ሥራውን በአዲስ አሠራር ከጀመርን በኋላ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በምሳሌ ሊገለጽ ይችላል?

አቶ ሰይፉ፡- በገቢ፣ በትርፍና በጥራት ሥራን አጠናቆ በማስረከብና በመሳሰሉት መሻሻሎች አሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልቅ እመርታ እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ለውጥ አንፃር ተመጣጣኝ ሥራዎች አልነበሩንም፡፡ ስለዚህ ሥራ መፍጠሩ ላይ እኛም በራሳችን መሥራት አለብን፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች