ለዓመታት በእስራኤል በጥገኝነት የቆዩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ወደ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ተሸኙ፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ካላቸው የአፍሪካ ስደተኞች ውስጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት ሕጋዊ የመኖርያ ፈቃድ የተሰጠው ለአራት ሰዎች (0.7 በመቶኛ) ብቻ መሆኑን የአልጄዚራ ዘገባ ገልጿል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ከ42 ሺሕ በላይ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞች እንደሚኖሩም አመልክቷል፡፡
በቅርቡ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ማሻገሯን የሚጠቁመው ይህ ዘገባ፣ ስደተኞቹን ወደ ኪጋሊ (ሩዋንዳ) እና ካምፓላ (ኡጋንዳ) እንዲሸኙ ከመደረጉ በፊት ሦስት አማራጮች እንደቀረበላቸው ያስረዳል፡፡
አማራጮቹ በስደተኞች ካምፕ መቆየት፣ ወደ ሦስተኛ አገር መሻገርና ወደ ኤርትራ ተገደው እንዲመለሱ መደረግ ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ምርጫቸው ወደ ሦስተኛ አገር መሻገር ሆኖ ተገኝቷል፡፡
እያንዳንዳቸው ሦስት ሺሕ ዶላር ይዘው ወደ ሁለቱም የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተሸኙት ኤርትራዊያን ስደተኞች፣ ብዙዎቹ በሰሃራ በረሃ በማቆራረጥ ለወራት ተጉዘው እስራኤል ውስጥ ገብተው ለብዙ ዓመታት ሲኖሩ የቆዩ ናቸው፡፡ አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን ጥያቄ ቢያነሱበትም፣ የእስራኤል ባለሥልጣናት ይህ የተደረገው በስደተኞቹ ፍፁም ፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ነው ብለዋል፡፡
የቢቢሲና የአልጄዚራ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ስደተኞቹን ከእስራኤል ተቀብለው የሚያስተናግዱት ቀድመው ከአገሪቱ ጋር በገቡት ውል መሠረት ነው፡፡
የኡጋንደና የሩዋንዳ ባለሥልጣናት ቢክዱም የእስራኤል ሥነ ሕዝብና ኢሚግሬሽን ቃል አቀባይ ሰቢን ሃዳድ ከሁለት የአፍሪካ አገሮች ጋር ስደተኞችን ለማፈናቀል እስራኤል ስምምነት እንዳላት ተናግረዋል፡፡ የሚዲያዎቹ ዘገባ እንደሚለው፣ እስራኤል ከሁለቱ አገሮች ጋር ያደረገችው ስምምነት በምላሹ የጦር መሣርያ እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡