Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ኧረ መተንፈሻ በሉልን!

ሰላም! ሰላም! አንድ የጎረቤታችን ልጅ አለ። ማንጠግቦሽ ስለምታቀብጠው ከእሷ ሥር አይጠፋም። እና ሰሞኑን ደብተሩን ይዞ ይመጣና ጥናቱን እስኪጨርስ ይቆያል።  ሰሞኑን እንደለመደው ደብተሩን እያገላበጠ ማንጠግቦሽን ጥያቄ መጠየቅ ጀመረ። ‹‹ማንጠግቦሽ፤›› ብሎ ጠራት። ‹‹አቤት?›› ትለዋለች በስስት እያየችው፡፡ ‹‹ሦስት አራተኛው የዓለም ክፍል ውኃ መሆኑን ታውቂያለሽ?›› ጓጉቶ ጠየቃት፡፡ ‹‹ወይ ጉድ!›› ትላለች? ማንጠግቦሽ። ‹‹የሰውነታችን 75 በመቶ ውኃ ነው፤›› አላት። ‹‹ግሩም ነው›› ብላ ዝም ስትለው ቆይቶ ቆይቶ፣ ‹‹ሳድግ ምን መሆን እንደምፈልግ ታውቂያለሽ?›› ሲላት፣ ‹‹ምን?›› ማንጠግቦሽ ቁሌቷን እየከደነች ወደ እሱ ዞረች። ‹‹እኔ ሳድግ መሆን የምፈልገው ውኃ ነው፤›› ሲላት እኔ አላስችል ብሎኝ ጥርሴ እስኪረግፍ ሳቅኩ። ማንጠግቦሽም አላስቻላትም ሳቅ በሳቅ ሆነች፡፡ አይ ልጅነት።

ይኼ ልጅ እንግዲህ ነገ ከነገ ወዲያ ‹ውኃ ሆነህ ቅር፣ ውኃ ሆነሽ ቅሪ› ጎረቤቱ ሲባባል ሲሰማ ህልሙን መጠራጠር ይጀምር ይሆናል። ወይም እንደ ብሩስሊ ጠላትህ ፊት እንደ ውኃ ሁን። ቅርፅም ሽታም አይኑርህ። ‹ያኔ አያገኝህም፤› ያለውን ተገንዝቦ ውኃ ሳይሆን ከውኃ ባህሪ መማር ከቻለ ምናልባት ህልሙ ፋይዳ ይኖረው ይሆናል። አይመስላችሁም? ለመሆኑ እናንተ ሠፈር ውኃ አለ? አሥር ጊዜ ውኃ ውኃ የምላችሁ እኮ በሠፈሩ ውኃ ጠፍቶ ነው። ‹በልጅ አመካኝቶ ይበሏል አንጉቶ› እንዲሉ መሆኑ ነው። ለነገሩ  ምኑን በላነው? የምናበላው ሰውና የምንበላውን ገንዘብ አለማንሳት ነው። አንዲት ቱቦ ፈንድታ እሷን ለማስቀየር እኔና ባሻዬ ለስንቱ ሸጎጥን መሰላችሁ? እንግዲህ ሸጓጭ እንደ ውኃ ካልጠፋ መቼም የዚህ አገር ሙስና ንቅንቅ የሚል አይመስልም። አይዞን ዋናው መተማመኑ ነው!

ዛሬ እንግዲህ በልጅ ህልም ጨዋታየን ስለጀመርኩ በጉደኛ ጥያቄው ባሻዬን ሰሞኑን ዓይናቸውን ስላስፈጠጠው ፀጉራቸውን ስላቆመው ልጅ ላጫውታችሁ። ታዲያላችሁ ይኼን ሳምንት እንዲሁ ‹አንድ ሕፃን ልጅ ምን አለ መሰለህ? አንድ ልጅ እንዲህ ብሎ እያልኩ ወሬ ያበዛሁበት የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አንበርብር ብለህ ብለህ የሕፃናትን ድምፅ ያላግባብ መጠቀም ጀመርክ?›› ብሎ ሲፎግረኝ ነበር። እኔ ግን እየፎገርኳችሁ እንዳይመስላችሁ። ሪል ነው ብሏል የተማረ። የስ። እና ባሻዬ የሠፈሩን ውሪ ሰብስበው ቅዳሜና እሑድ ከሰዓት በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀምረዋል። ‹‹ባሻዬ አዲሱ ሥራው እንዴት እየሄደ ነው?›› ስላቸው፣ ‹‹ደግ ነው። ልጆች ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ይላል አይደል እንዴ ቃሉ? እነዚህ ልጆች እኮ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ብዙ ነገር እየከለከልናቸው ነው። ኳስ መጫወቻ የላቸው፣ መሮጫ የላቸው፣ ንፁህ አየር መተንፈሻ የላቸው፣ ምን የላቸው፣ ምን የላቸው፣ ባይሆን በሰማዩ ሥፍራ ቦታ ይኑራቸው ብዬ እኮ ነው፤›› አሉኛ፡፡

 አይ ባሻዬ። አይታወቃቸውም እንጂ እኮ ይናገራሉ። ግን አያችሁ አገሬ እንደሳቸው ያሉ ሰዎችን ንግግር መስሚያ የላትም። አገሬ ጆሮዋን የምትከፍተው ለሚያጣብባት፣ ለሚያስተፋፍጋትና ለሚያጨናንቃት ወዘተ፣ ወዘተ ነው። ይኼ ምንም ከፖለቲካ ጋር አይገናኝም። እንዴ ተው እንጂ ምን ነካችሁ? ቆይ ለምድነው ሁሉ ነገር ፖለቲካዊ ጥያቄና መልስ የሚሆነው? ለምሳሌ አንዱ ባለፈው ዓመት በአንዱ የተቃውሞ ሠልፍ ውስጥ ተቀላቅሎ እጁን በኪሱ ከቶ ይጓዛል አሉ። እና የሚያውቀው ሰው አግኝቶት፣ ‹‹እንዴ አንተም ተቃዋሚ ነህ?›› ሲለው ምን ቢለው ጥሩ ነው? ‹‹ኧረ እኔ ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ብቻ ብዙ ተቀማጭ ሰው ስለበዛ ብዙ ጊዜ ወክ የማደርገው ብቻየን ነው። ዛሬ እስኪ ከሰው ጋር ልጓዝ ብዬ ነው፤›› አለው አሉ። እና ይኼ አሁን ምኑ ፖለቲካ ነው?

 የእኔ ነገር። ስለባሻዬ ክውታ አወራለሁ ብየ የትም ስሄድ ዝም ትላላችሁ? እና ባሻዬ እነዚያን በከተማና ከተሜነት ስም መድረሻ ያጡ፣ ልጅነታቸውን ማስተንፈሻ የተከለከሉ ሕፃናት ሰብስበው ሲያስተምሩ አንድ ቅብጥብጥ እያለ የሚያስቸግራቸው ልጅ እጁን አወጣ። ‹‹ምንድነው?›› አሉት። ‹‹ጥያቄ አለኝ፤›› አላቸው። ‹‹በል እኮ. . .›› ሲሉት፣ ‹‹ነብር ዢንጉርጉርነቱን ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱን ሊለውጥ አይቻለውም ሲል ምን ለማለት ነው?›› አላቸው። ‹‹አንተስ ምን ለማለት ይመስልሃል?›› አሉት ባሻዬ ተገርመው። እኔ? ‹‹እኔ እንደሚመስለኝ እግዚአብሔር ዓለማትን ሁሉ በቅራኔና በለውጥ ሕግ ፈጥሮ ፈጥሮ ኢትዮጵያውያንና ነብሮችን ግን እንዳይለወጡ አድርጎ የሠራቸው ይመስለኛል። ሳይንስ አስተማሪያችን ሁል ጊዜ ሲያስተምረን የማይለወጥ ነገር የለም ብሎናል። ሁሉም በሒደትና በለውጥ ሕግ ይመራል ብሎናል። እኔ እንደሚመስለኝ ነብሮችና ኢትዮጵያውያን  ለዚህ ሕግ ተገዥ አይደሉም፤›› ሲላቸው የሚሉት ጠፍቷቸው፣ ‹‹በሉ ለዛሬ ይብቃን፤›› ብለው በተኑዋቸው።

ኋላ ሲያጫውቱኝ፣ ‹‹ይገርምሃል እኮ አንበርብር። የዛሬ ልጆች አዕምሮ እንዴት ስል እንደሆነ ታያለህ? እንደ ካርቦን እንዴት በግልባጭ እንደሚያትምና እንደሚያነብ ታያለህ? ነገሩ እኮ እውነት አለው። ከእንስሳ ቆዳ ጋር የሰው ልጅ ውስብስብ ባህሪና አስተሳሰብ ተመሳስሎ ሲሳል ጥያቄ ያስነሳል እኮ?›› ብለው እሳቸው ራሳቸው የሚይዙት የሚጨብጡት ጠፍቶባቸው ዋሉ። ልጃቸው በበኩሉ ይኼን ነገር ሰምቶ ጥያቄውን ያነሳውን ልጅ እያደነቀ ስለዓለምና ‹ዳይናሚዝም› ሲያጫውተኝ ዋለ። ‹‹ውኃ እንኳ ረግቶ ቅርፁን ይቀያይራል። ንፋስ ከወዲህ ይሄዳል ከወዲያ ይመጣል። የማይወጣና የማይወርድ የማያብብና የማይረግፍ ነገር የለም። እንዴት ሰው ተሁኖ ያለ ለውጥ ይኖራል?›› ሲለኝ እኔም እሱም ሳናስበው የሦስት ሺሕ ዘመን ህልውናችንን በትንሿ ጭንቅላታችን መጠራጠር ጀመርን። ምነው? መጠራጠርም እኮ ኢትዮጵያዊነት ነው!

በዚህ ሁሉ መሀል ከሳምንት በፊት ኤግዝኪውቲቭ ያጋዛሁት ደንበኛዬ ደወለ። ‹‹ሃሎ?›› ስለው፣ ‹‹ስማ አንበርብር መኪናዬ እኮ ታረደች፤›› አለኝ። ‹የምንድነው ሚያወራው ብዬ፣ ‹‹ምን አልክ?›› ስለው ‹‹በሉኝ። ወይኔ አራት መቶ ሺሕ ብሬ. . .›› እያለ ቀውጢ አደረገው። ‹‹ቆይ ተረጋጋ የት ነው ያለኸው?›› ብዬ ያለበትን አጣርቼ ስከንፍ ወደ ጎተራ ሄድኩ። ወደ ጠቆመኝ ሠፈር ዘልቄ ወደ ቀኝ ስታጠፍ ደንበኛዬ መኪናው ውስጥ ተቀምጦ ስልክ ያወራል። ጨዋታ ነው የያዘው እያልኩ በሆዴ ስልክ እስኪጨርስ እኔም ስልኬን ያዝኩ። ለካስ እንደ ትናንት የደስደስ ተብሎ ሲጠጣ ተመሽቶ፣ ታድሮ ጠዋት ሲነሳ መኪናውን ዘወትር የሚያቆምበት ቦታ አጥቷታል። በስካር መንፈስ የት እንዳቆማት? እንዴት እንደነዳ? በየት በየት አድርጎ እንደመጣ አያስታውስም። ይኼውላችሁ እንግዲህ። እኔም ጊዜዬ መቃጠሉን እያሰብኩ ከመናደድ እጄ ላይ ይኼው ደንበኛዬ የሚፈልጋቸው ነገሮች ነበሩና መደለሌን ጀመርኩ።

ኋላ ከባሻዬ ልጄ ጋር ስናወራ ታሪኩን ሰምቶ፣ ‹‹እኔ እኮ ምን ዓይነት ቫይረስ እንደወረረን አላውቅም። ፋሽን ብለን የምንይዘው ነገር ሁሉ ኋላ ቀር ሆኗል። ቆይ እንዴት በምን ሒሳብ ሞት ለእኛ ብርቅ ይሆናል? አይገርምህም ግን? መኖር ነው እኮ ብርቃችን መሆን የሚገባው. . .›› እያለኝ ኧረ ተወኝ ተወኝ ስንባባል ቆየን። ይኼን እያወራን ድንገት አንዱ ወጣት ይቅርታ ብሎ መንገድ እንድንመራው ጠየቀን። መምራትን ሳይሆን ማሳሳትን ከአያት ቅድመ አያቶቻችን በደም የወረስን ብንሆንም፣ ራሳችንን ቆንጥጠን ራሳችንን ያሳደግን ነንና የጠየቀንን መንገድ አሳየነው፡፡ ‹‹ቴንኪው. . .›› ብሎን ሲሄድ ሁለታችንም በፊት ያላስተዋልነውን አስተዋልን። ወጣቱ እንብርቱ እስኪታይ አጭር ካናቴራ ለብሷል፡፡ የውስጥ ሱሪው እስኪታይ ሱሪው ዝቅ ብሏል። ባቱ ዕብድ ብሎ በሎሽን ታሽቶ እያብረቀረቀ እንዲታይ ሱሪው አጥሯል። ‹‹አውሮፓ ለሥራ የሚመላለሱ እንደነገሩኝ እንዲህ ያለው አለባበስ ያለምንም የማያሻማ ጥያቄ መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው፤›› ስለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ጠጥቶ ማሽከርከሩንስ መንጃ ፈቃድ እየነጠቅክም ቢሆን ሰውን አስደንግጠህ ታስቆመዋለህ። እንዲህ ያለ የሰከረ ፋሽን ምን ብለህ ማንን አይተህ ታርመዋለህ?›› ሲለኝ መልስ አልሰጠሁትም። መልሱ አልተሰጠም!

በሉ እንሰነባበት። እኔና የባሻዬ ልጅ አንድ አንድ እያልን ጨዋታችን ሲደራ ተያይዘን ወደ ግሮሰሪያችን አዘገምን። አገሩ እንደሆነ በመጠጥ ማስታወቂያና በሰካራም ሾፌር አብዷል። የት ይኬዳል? እየተባባልን ስንገባ በዓይን የምናውቃቸው የግሮሰሪያችን ታዳሚዎች ሰምተውን ኖሮ፣ ‹‹እውነት ነው ፓርክ የለን?›› አለ አንዱ። ‹‹ፓርኩን ተወው የጓሮ አትክልት መቼ አለን?›› አለ ሌላው። ‹‹የጓሮ አትክልት ትላለህ እንዴ አንተ የደላህ። መቼ ቤት አለን?›› ቀጠለ ሌላው። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ምን ዓይነት ሰደድ እሳት ነው ያስነሳነው?›› እያለ ይቆነጥጠኛል። አንዱ ደግሞ ተነስቶ፣ ‹‹ቤት ትላላችሁ እናንተ የደላችሁ። መቼ አየር አለን። አየር! አየር አጣን እኮ፤›› ብሎ ሲደነፋ መጀመርያ ፓርክ የለን ያለው ሰውዬ ለቀም አድርጎ፣ ‹‹እኮ እኔ ምን አልኩ? ዞራችሁ ዞራችሁ ወደ እኔው ሐሳብ መጣችሁ። አየር ሲኖር ነው ሁሉ ነገር የሚኖረው። የተዛባብንን በሰከነ አዕምሮ መዝነን ለመረዳት አየር ያስፈልጋል። መተንፈስ አለብን። ፋሽን ያልነውን ጊዜው ካለፈበነት ወይም አጓጉል ቅጥያ ያለበትን አረማመድ ከጨዋው ለማስማማት አየር ያስፈልጋል። አየር በሌለበት አገር ሰው በአልኮል ብቻ እየተነፈሰ እንኳን ሰክሮ መሪ አይደለም እሳት ቢጨብጥ ይገርማል?›› ሲል ‹‹ጭብጫቦ ጭብጫቦ›› ብሎ አንዱ ዋዘኛ ቤቱን በጭብጨባ አናጋው። ኧረ መተንፈሻ በሉልንማ ጎናችሁ ያለውን። መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት