Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የስድስቱ ባንኮች ጥምረትና የቦርድ ሊቀመንበሩ ስንብት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በፕሪሚየም ስዊች ሶሉዊሽን 5.4 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቅሷል

ፕሪሚየም ስዊች ሶልውሽን አክሲዮን (ፒኤስኤስ) በመባል የሚታወቀውን ስድስት ባንኮች በጥምረት የፈጠሩትን ኩባንያ ላለፉት ስድስት ዓመታት የቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት የቀድሞ የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ኃላፊነታቸውን በፈቃደኝነት ለቀቁ፡፡ ኩባንያው ሥራ ከጀመረ ወዲህ ባሉት አራት ዓመታት በአጠቃላይ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር በፕሪሚየም ስዊች በኩል መካሄዳቸው ተገልጿል፡፡

ለኩባንያው መፈጠር ሐሳብ አመንጪና አደራጅ በመሆን የአስተባባሪነት ሥራውን በመውሰድ ጭምር የሚታወቁት አቶ ብርሃኑ፣ ከፕሪሚየር ስዊች የቦርድ ሊቀመንበርነታቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት ባለፈው ሐሙስ የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡ በዕለቱ ኩባንያውን በቦርድ አባልነት በሊቀመንበርነት ለማገልገል ምርጫ ከመደረጉ ቀደም ብሎ ድጋሚ ላለመመረጥ በማሳወቅ አዲስ አመራር እንዲተካቸው በመግለጽ ከመድረክ የወረዱት አቶ ብርሃኑ፣ ድጋሚ እንዲወዳደሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልተቀበሉትም፡፡ ከዚህ ውሳኔ የደረሱት በአሁኑ ወቅት ኩባንያው በሁለት እግሩ የቆመና በተተኪዎች እንዲመራ በመሻታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታቸው ናና በተገኙበት የምሽት ፕሮግራም ላይም አቶ ብርሃኑ ባደረጉት ንግግር ኩባንያው በአዲስ አሠራር እንዲቀጥል በመፈለጋቸው ጭምር በድጋሚ ላለመመረጥ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ሥራ ሲጀምር በኅብረት፣ አዋሽና ንብ ባንኮች ጥምረት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ በአሁኑ ወቅት ግን ብርሃን፣ አዲስ ኢንተርናሽናልና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ኩባንያውን በመቀላቀላቸው የተጣማሪ ባንኮቹ ስድስት ደርሰዋል፡፡ እስካሁንም ከ5.3 ቢሊዮን በላይ የገንዘብ ልውውጥ በፕሪሚየም ስዊች ሶልዊሽን አክሲዮን ማኅበር በኩል የተፈጸመ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ ይህም አሁን ኩባንያው የደረሰበትን ደረጃ የሚያመለክትና መሠረት የያዘ በመሆኑ ቀጣይ ተግባሮቹን አዳዲሶቹ አመራሮች ይወጡታል የሚል እምነታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፒኤስኤስ በስድስት ባንኮች መካከል የሚከናወኑ የገንዘብ ልውውጦችን በማሳለጥ ለእነዚህ አባል ባንኮች ደንበኞች የአገልግሎት እርካታንና ምቶችን የፈጠረ በመሆኑም፣ በቅርቡ ሥራ በጀመረው አገር አቀፋዊ ስዊች (Et-Switch) በሚደረገው እንቅስቃሴ ወሳኝ ሚና በመጫወት በቁጥር በርከት ያሉ የገንዘብ ልውውጦችን በማስተላለፍ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

የፒኤስኤስ አባል ባንኮች የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ላይ የተመሠረተ የገበያ ውድድር ለዘለቄታ ስኬት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ቀድሞ በማገናዘብ የተጀመረ ሥራ ነበርም ተብሏል፡፡ የግል ባንኮቹ በየግላቸው በመጓዝ የፋይናንስና ሌሎች ሀብቶችን ከማባከን ይልቅ ትብብርን በማስቀደም ዘመናዊ የክፍያ ቴክኖሎጂውን ዘርፍ በመገንባት ረገድ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚል እምነትታቸውንም አንፀባርቀዋል፡፡

አባል ባንኮቹ በፒኤስኤስ ሲስተም ተጠቅመው ከሚሰጧቸው ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከልም በካርድ አማካይነት ለደንበኞች ተደራሽ በሆኑ ቦታዎች በተቀመጡ ኤቲኤም ማሽኖች መገልገል አንዱ ነው፡፡ ነጋዴዎች ክፍያቸውን በፖይንት ኦፍ ሴል እንዲቀበሉ ማድረግ፣ ሲሲተሙ ሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ እንዲሠራና የገንዘብ ልውውጦች መልዕክቶችን እንዲያስተላልፍ የማሽኖቹን የመከታተል ኃላፊነት ወስዶ የሚሠራም ነው፡፡ በዚህም አገልግሎቱ የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓቱን ሒደት የተቀላጠፈ እንዲሆን የድጋፍ አገልግሎት በመስጠት ባንኮች በመተባበር ተወዳዳሪ መሆን የሚቻልበትን መንገድ የጠረገ ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በተጠናቀቀው 2008 የበጀት ዓመትም ከ370 በላይ ከሲስተሙ ጋር በተገናኙ ኤቲኤሞችና ከ620 በላይ ፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናሎች 2.9 ሚሊዮን የኤቲኤሞችና ከዘጠኝ ሺሕ በላይ ፒኦኤስ የገንዘብ ልውውጦች መልዕክቶችን ለአባል ባንኮቹ ያስተላለፈና ያቀነባበረ ስለመሆኑ በዕለቱ የቀረበ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ይህም ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያስተላለፈውን የገንዘብ ልውውጦች መልዕክቶች ጠቅላላ ብዛት ከ5.3 ሚሊዮን በላይ እንዲሆን እንዳደረገውና ከእነዚህም ውስጥ 37 በመቶ የአንዱ ባንክ ደንበኛ በሌሎች ባንኮች ክፍያ ማሽኖች ላይ ያካሄዷቸው ግብይቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ፒኤስኤስ ከዓለም አቀፍ ማኅበራት ጋር በተደረገ ስምምነት አባል ባንኮች የቪዛ፣ የማስተር ካርድና የዩኒየን ፔይ ካርዶችን በኤቲኤሞቻቸው ላይ እንዲቀበሉ ማስቻሉ የኩባንያው ተግባራት የሚገለጽበት ሌላው ማሳያ መሆኑን የኩባንያው ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ በ2008 የበጀት ዓመት እነዚህ ካርዶች በፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናል ላይ ተቀባይነት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ ይህም ባንኮች እነዚህን ካርዶች በመቀበል ሊያገኙ የሚችሉትን የውጭ ምንዛሪ ከፍ እንዲል አስተዋጽኦ እየበረከተላቸው እንደሆነ በዕለቱ ከቀረበው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደኩባንያው መረጃ ፒኤስኤስ በ2008 የበጀት ዓመት ብቻ 173,216 ካርዶችን ለባንኮቹ በማተም አሰራጭቷል፡፡ ይህም በገበያ ላይ የሚገኙትን የፒኤስኤስ መለያ ያላቸውን ካርዶች ብዛት ወደ 400,000 ማድረስ መቻሉን የኩባንያው ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፒኤስኤስ የተዘረጋውን ሲስተም በመጠቀም የተወሰኑት ባንኮች ከወለድ ነፃ የሆነ ካርድና ቅድሚያ ክፍያ ካርድ (Pre-paid Card) ለደንበኞቻቸው መስጠት እንዲጀምሩ በማድረግ የካርድ አገልግሎት እንዲስፋፋ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ኩባንያው እንዲህ ያለውን ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች ሲሰጥ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የተለያዩ ዕርምጃዎች ስለመውሰዱ ተብራርቷል፡፡ በዚህም መሠረት ዓለም አቀፍ የክፍያ ሥርዓቱ ያስቀመጠውን ስታንዳርድ በማሟላት ሲሆን፣ የባንኮች ደንበኞችን መረጃ በጥንቃቄ ከመያዝ አንፃር የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ በ2007 ዓ.ም. የPCIDSS (Payment Card Industry Data Security Standard) ሰርተፊኬት ወስዷል፡፡ በ2008 በጀት ዓመትም የዕድሳት ፍተሻ አሟልቶ በመገኘቱ ሰርተፊኬቱን ማግኘቱ፣ ደኅንነቱ የጠበቀ አገልግሎት መስጠቱን ያመለክታል፡፡ የደንበኞች መረጃ ሲያስተላልፍ፣ ሲያቀነባብርና ሲያከማች በማንኛውም መልኩ ላልተፈቀደለት ሦስተኛ ወገን እጅ እንደማይወድቅ ማረጋገጫ ነውም ተብሏል፡፡ የ2008 በጀት ዓመት የፋይናንስ እንቅስቃሴውን በተመለከተ የተገኘው መረጃ የኩባንያው ገቢ ወደ 34 ሚሊዮን ብር መድረሱን ያመለክታል፡፡ ይህም ከቀደሚው ዓመት በ23 በመቶ ማደጉን ያሳያል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታትም በኩባንያው በኩል የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 5.4 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአራት ዓመት ውስጥ ከተንቀሳቀሰው 5.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ በ2008 በጀት ዓመት የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ከፍተኛ መጠን ያለው ሆኗል፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ብቻ የተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን 3.1 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

በገንዘብ ዝውውር መጠንም ቢሆን በ2008 በጀት 2.9 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ይህም በቀደሙት ሦስት ዓመታት በድምር ከተካሄደው የገንዘብ ልውውጥ በ2008 ዓ.ም. የተደረገው ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡

ኩባንያው ወደ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ትርፍ ማግኘቱን የሚጠቁመው መረጃ በ2008 በጀት ዓመት ለታየው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ዋነኛው ምክንያት ተጨማሪ ኤቲኤሞች መተከላቸው፣ ደንበኞች በካርድ ባንኪንግ የመጠቀም ልምዳቸው ማዳበራቸውና ተጨማሪ ካርዶች መሠራጨታቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡

ኩባንያውን በቦርድ አባልና በሊቀመንበርነት ለመምራት በዕለቱ ምርጫ የተደረገ ሲሆን፣ በምርጫው ውጤት መሠረት አራት ባንኮችና የሦስት ባንኮች ፕሬዚዳንቶች ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የቦርድ አባል ሆነው ተመርጠዋል፡፡ አቶ ብርሃኑን በመተካት የሚሠሩት የቦርዱ ሊቀመንበር የሚመረጡት ግን ሰባቱ የቦርድ አባላት በሚያደርጉት ስብሰባ ይሆናል፡፡

ከሰባቱ የቦርድ አባላት ውስጥ ሦስቱ በግለሰብ ደረጃ በመመረጥ የቦርድ አባል ሲሆኑ፣ የኩባንያው ቦርድ ሊቀመንበርም የሚመረጠው ከሦስቱ ግለሰብ ተመራጮች መካከል አንዱ ነው፡፡

በዚህ ስሌት ቀጣዩ የኩባንያው ፕሬዚዳንት ሊሆኑ የሚችሉት የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው፣ የንብ ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ክብሩ ፎንጃ ወይም የኅብረት ባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ናቸው፡፡

የቦርድ ሊቀመንበርነታቸውን ለአዲሱ ተመራጭ የሚያስረክቡት አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ከፕሪሚየም ስዊች የቦርድ ሊቀመንበራቸው ከፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ከማሳወቃቸው በፊት፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱ ተቋማት ይዘውት የነበረውን የኃላፊነት ቦታ በተመሳሳይ መንገድ መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ብርሃኑ የኅብረት ባንክ ፕሬዝዳንትነታቸውን የለቀቁት በፈቃዳቸው ነው፡፡ ከዚያም ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርን ለሁለት የምርጫ ዘመን በፕሬዚዳንትነት ካገለገሉ በኋላ ይህንንም ኃላፊነት በፈቃዳቸው ለቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች በአባልነት ያቀፈውን ኢትስዊች የተባለውን ኩባንያም በመሥራችነትና የመጀመሪያው ቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ያገለገሉት አቶ ብርሃኑ፣ ከዚህም ኩባንያ በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡

ይህም አቶ ብርሃኑ ከፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የነበራቸውን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች በሙሉ መልቀቃቸውን አሳይቷል፡፡

‹‹ይህ ለምን?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ብርሃኑ፣ ‹‹እንዲህ ያሉ የኃላፊነት ቦታዎች ለተተኪዎች ወይም ለወጣቶች መለቀቅ ስላለባቸው ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ፕሪሚየም ስዊች ከስድስት ዓመት በፊት በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ አሁን ካፒታሉን ወደ 160 ሚሊዮን ብር አሳድጓል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች